January 17, 2024 – Konjit Sitotaw 

አሜሪካ ኢትዮጵያና ራስ ገዟ ሶማሌላንድ የተፈራረሙት የባሕር በር መግቢያ ስምምነት እንዳሳሰባት ትናንት በኋይት ኃውስ በኩል ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

ኃይት ሃውስ በመግለጫው፣ የመግባቢያ ስምምነቱ አለመረጋጋትን እንዲኹም በዓለማቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል ብሏል።

የብሄራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዕውቅና ከሰጠች ከአልቃይዳ ጋር ትስስር ካለው አልሸባብ ጋር የሚደረገውን ውጊያ ሊያደናቅፍ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ኪርቢ፣ አሜሪካ የሱማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንደምትደግፍና መከበር እንዳለበትም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ ግጭት ሊሸከም ይችላል ብለን አናምንም ያሉት ኪርቢ፣ የመግባቢያ ስምምነቱ በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዘ አይመስለንም በማለት ተናግረዋል።

የዓረብ ሊግ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በኢትዮጵያና ሱማሊያ መካከል በተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ዙሪያ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የሱማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ንግግር አድርገዋል።

ባሬ፣ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን መግቢያ በር የመቆጣጠር ዕቅድ፣ በዓለማቀፍ የባሕር ንግድና ትራንስፖርት ላይ አደጋ ይደቅናል በማለት መናገራቸውን አስታውቀዋል።

ዓረብ ሊግ፣ ይህንኑ የኢትዮጵያ ዕቅድ ለማክሸፍ ከሱማሊያ ጎን እንዲቆም መጠየቃቸውንም ባሬ ገልጸዋል።

ዓረብ ሊግ በኢትዮጵያና ሱማሊያ ውዝግብ ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባውን የጠራው፣ ሱማሊያ ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት እንደኾነ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች መካከል፣ ሱማሊያ፣ ጅቡቲና ሱዳን የዓረብ ሊግ አባል ናቸው።