ሰላማዊት መንገሻ

January 17, 2024

አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ አንዱ (ፕሮፌሰር)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በሙሉ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡

ቢሮው በተለያዩ ባለሙያዎች እያደረገ ባለው የመስክ ሥራ አማካይነት በከተማዋ ሕገወጥ የነዳጅ ንግድ በመስፋፋቱ ምክንያት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የቢሮው ባልደረባ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ የሚገኝ ማንኛውም የነዳጅ ማደያ መመርያው በሚያዘው መሠረት ታሽጎ ክስ ይመሠረትበታል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ሱቆች፣ በመኖሪያ ቤት፣ በመንገድ ላይና ሕጋዊ የነዳጅ ማደያ ቦታ ባልሆኑ አካባቢዎች ነዳጅ በዕቃ በመቅዳት ሽያጭ እየተከናወነ በመሆኑ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

በቢሮው መመርያ መሠረት ሕጋዊ ደብዳቤ ከተጻፈላቸው ድርጅቶች ውጪ፣ በቀንም ሆነ በሌሊት ምንም ዓይነት የበርሜል ሽያጭ ማካሄድ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

‹‹መመርያውን መሠረት በማድረግ ለነዳጅ አዳዮች በተደጋጋሚ ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ እንዲሁም ደብዳቤ እንዲደርሳቸው በማድረግ ሕገወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ጥረት እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሕጋዊ ደብዳቤ ከሚጻፍላቸው የንግድ ድርጅቶችና ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በስተቀር፣ በዕቃና በበርሜል የነዳጅ ሽያጭ የተከለከለ ነው፡፡

የነዳጅ ማደያዎቹ በዕቃ እንዲሸጡ የሚፈቅደውን በየስድስት ወራት የሚታደሰውን ደብዳቤ መያዝ ግዴታ እንደሆነም የቢሮው ባልደረባ ተናግረዋል፡፡

ያለ ደብዳቤ ነዳጅ በመግዛት ሕገወጥ ሽያጭ የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ማደያ መግባት ለማይችሉ አነስተኛ ባጃጆች፣ እንዲሁም የነዳጅ እጥረት በሚኖርበት ወቅት በተጋነነ ዋጋ ለመሸጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የቤንዚን ዋጋ 77.65 ብር ሲሆን፣ በዕቃ በመቅዳት ውጪ የሚሸጠው እስከ 80 ብር ድረስ ነው ብለዋል፡፡

በዕቃ ተቀድቶ የሚሸጠው የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከመንግሥት ታሪፍ ውጪ ከመሸጥም በላይ፣ እንደ ቤንዚን ያሉ ምርቶች ደግሞ ወዲያውኑ አገልግሎት ላይ ማዋል እንጂ ማስቀመጥ ለደኅንነት አሥጊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ እየታወቀ የነዳጅ ማደያ ድርጅቶች ስህተት እንዳይፈጽሙ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ፣ እንዲሁም ቢሮው ባደረገው የመስክ ምልከታ በየመንገዱ ሲሸጥ የተገኘውን በመመልከት ሽያጭ እንዳያካሂዱ ክልከላ ብቻ ያደረገ በመሆኑና እስካሁን የቅጣት ዕርምጃ ባለመወሰዱ፣ ሕገወጥ ድርጊቱ ሳይስፋፋ ዕርምጃ ለመውሰድ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በሕገወጥ መንገድ የተገኙት ምን ያህል እንደሆኑ የተዋቀረው ግብረ ኃይል በሚያቀርበው ሪፖርት መሠረት ይፋ ይደረጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የንግድ ቢሮው ዕርምጃ መውሰድ የሚችለው በንግድ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶች ላይ ብቻ በመሆኑ፣ ሕገወጥ ድርጊት የሚከናወነው በመኖሪያ ቤት ከሆነ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ፣ ከሕገወጥና ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን ምርቱ እንዲወረስና ክስ እንዲመሠረት ይደረጋል ብለዋል፡፡