

በትምህርት ላይ በተወሰዱ ዕርምጃዎች በጥናት እንጂ በኩረጃ አይታለፍም የሚል አመለካከት መፈጠሩ ተነገረ
ቀን:
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪና የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በተወሰዱ ዕርምጃዎች፣ በአገር ደረጃ በጥናት እንጂ በኩረጃ ፈተና አይታለፍም የሚል አመለካከት መፈጠሩን ተናገሩ፡፡ሚኒስትሩ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ምን ዓይነት የትምህርት ፖሊሲ ያስፈልጋል?›› በሚል ርዕስ እሑድ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ በትምህርት ምዘና ላይ የተደረጉ ለውጦች ኩረጃና ሌብነትን እያስቀሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡የትምህርት ምዘናው ትምህርት ቤቶች በጥራት እንዲያስተምሩ በጎ ጫና መፍጠሩን ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ገልጸው፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን አጥኑ ብለው እንዲከታተሉ በጎ ጫና መፍጠሩን በመጠቆም፣ ‹‹ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ወላጆችም በትምህርት ጉዳይ መቀለድ አቁመዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ሰፊ ውይይት የተካሄደበት የኢዜማ የትምህርት ፖሊሲ ጥናት መድረክ፣ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተወሰዱ ስላሉ ዕርምጃዎች ሚኒስትሩ ገለጻ ያደረጉበት ነበር፡፡በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ዘርፉን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለማሻሻልና የተሻለ ትውልድ ለመቅረፅ በካሪኩለም ቀረፃ፣ በትምህርት አሰጣጥ፣ በምዘናና በሌሎችም መስኮች ጠንካራ ለውጦች መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡‹‹ምን ዓይነት ልጆች ነው ማፍራት የምንፈልገው ተብሎ የዛሬ 25 ዓመታት የሚሆነውን አስቦ ትምህርትን የመቅረፅ ፍላጎት አለ፡፡ ስለእኛ ሳይሆን ስለልጆቻችን የሚል ዕቅድ አለ፡፡ እየተለወጠ ካለው ዓለም ጋር የሚፎካከር፣ በቴክኖሎጂም ሆነ በዕውቀት በዓለም መድረክ ለመፎካከር ብቁ የሆነ ትውልድ የሚፈጥር የትምህርት ሥርዓት ለመቅረፅ በትምህርት ሚኒስቴር ሥር ውይይት ተጀምሯል፤›› በማለት ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ በትምህርት ፖሊሲ ላይ የኢዜማና የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ልዩነት ካላቸው የጠየቁት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ መንግሥት ብትሆኑ ምን ዓይነት የትምህርት ፖሊሲ እንዲኖራችሁ ነው የምትፈልጉት ተብለው ተጠይቀዋል፡፡ኢዜማም ቢሆን የትምህርት ተደራሽነት አሁን ካለው በተሻለ እንዲሰፋ እንደሚፈልግ ያነሱት ፕሮፌሰሩ፣ በትምህርት ጥራት መሻሻል ጉዳይ ላይም ቢሆን በሁለቱ ድርጅቶች መሀል ልዩነት እንደሌለ ነው ያነሱት፡፡በውይይት መድረኩ ላይ የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ አባሉና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የትምህርት ባለሙያው አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ትምህርት ዘርፍ የገጠሙትን ችግሮች የተመለከተ ሰፊ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር፡፡ጃፓን ሄደው ትምህርት መውሰዳቸውን የተመለከተ የግል ተሞክሯቸውን ያቀረቡት አወቀ (ዶ/ር) የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በኢትዮጵያ ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱን እንደ ትልቅ ችግር አንሰተዋል፡፡ ‹‹በጃፓን ግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠራውን የኢኮኖሚው ወሳኝ አንቀሳቃሽ ሞተር በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ያለፈው ባለሙያ ነው፡፡ እዚህ ግን ለይስሙላ ብቻ የሚሰጥ እየሆነ ነው፤›› በማለት ነው አወቀ (ዶ/ር) የትምህርት ዘርፉን ችግሮች የዘረዘሩት፡፡