ከመከላከያ ሚኒስቴር ፈንጂ ማምከን የቢሮ ኃላፊዎች ጋር ጉብኝት በተደረገበት ወቅት

ዜና የተቀበሩ ፈንጂዎችና የጦርነት ቅሪቶች የሚገኙባቸው ሥፍራዎችን ለማወቅ ጥናት ሊደረግ ነው

ሳሙኤል ቦጋለ

ቀን: January 17, 2024

በኢትዮጵያ ተቀብረው ሊገኙ የሚችሉ ፈንጂዎችና የጦርነት ቅሪቶች ሊገኙባቸው የሚችሉ ሥፍራዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለማወቅ፣ በአሜሪካ መንግሥት ትብብር ጥናት ሊደረግ መሆኑ ታወቀ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ያደረሰውና ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነትና ሌሎች ግጭቶች ተካተው በርካታ ተቀብረው ያሉ ፈንጂዎች ሊኖሩ እንደሚችል ይገመታል፡፡

ፈንጂዎቹ በተለያዩ ጊዜያት እንደተገለጸው፣ በንፁኃን ላይ ሞትና አደጋ ማድረሳቸውን፣ አርሶ አደሮች ወደ ማሳቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ከሰኞ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. እስከ ዓርብ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ፈንጂ ማምከን ቢሮ፣ የአሜሪካ መከላከያ ዲፓርትመንትና በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ደኅንነት ትብብር ቢሮ ጥናቱን ለማስጀመር እየተዘጋጁ ሲሆን፣ ጥናቱም በኢትዮጵያ የሚገኙ ፈንጂዎችና የጦርነት ቅሪቶች በምን ያህል መጠን እንደሚገኙ ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የንፁኃንን ደኅንነት የመጠበቅና በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የግብርና ምርትን ማሳደግ ዋነኛ ግብ ያደረገውን ይህንን ፕሮጀክት፣ የአሜካው መከላከያ ዲፓርትመንትና የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ የደኅንነት ትብብር ቢሮ፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴሩ ፈንጅ ማምከን ቢሮ ጋር በትብብር እንደሚያከናውኑት ታውቋል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ ‹‹ታሪካዊ›› ባለው ይህ ትብብር፣ በኢሜይል በላከው መግለጫ የዚህ ሥራ ቀዳሚ ዓላማ ለመከላከያ ፈንጂ ማምከን ቢሮ መሥፈርቶችን መቅረፅና የአሜሪካ ተባባሪ ቢሮዎቹ ካላቸው ሀብት ጋር ማመሳከር እንደሆነ ገልጿል፡፡

‹‹በመጪዎቹ ስድስት ወራት ለፕሮጀክቱ የሚያግዙ መሣሪያዎችን በተከታታይ የማቅረብ፣ የማሠልጠን፣ እንዲሁም ተጨማሪ ሀብቶችን የማቅረብ ሥራዎች ይካሄዳሉ፤›› ሲል ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ ጦር ሜዳ በነበሩ ሥፍራዎች የተለያዩ ፈንጂዎች የሚገኙ መሆናቸውን፣ እነዚህ የሆኑ የጦርነት ቅሪቶች የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንደሚከቱ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ከማኅበረሰቡ ጋር መልሶ የመላቀለሉ ሥራ ላይ (Disarmament, Demobilization, Reintegration-DDR) እንቅፋት እንደሚፈጥሩ የኤምባሲው መግለጫ አክሏል፡፡