ዳዊት ታዬ

January 17, 2024

የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው የረቂቅ አዋጅ ቀርቶ ንግዱንና ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለሁለት ከፍሎ ለየብቻ የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጆች መሰናዳቱ ተጠቆመ፡፡ 

አሁን ሥራ ላይ ያለውን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዋጅ ለማሻሻል በመጀመርያ የተረቀቀው አዋጅ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ሁለቱም የንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፎች በአንድነት እንዲዋቀሩ ያለመ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ረቂቅ አዋጅ ቀሪ ተደርጎ ሁለቱን ዘርፎች ከፍሎ ለየብቻቸው እንዲተዳደሩ የሚያስችሉ ሁለት ረቂቅ አዋጆች በሁለት ማኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መሰናዳታቸው ታውቋል።በዚህም መሠረት የንግዱ ዘርፍ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን ረቂቁ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀና የሚቀረውም ማፀደቅ ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በተመሳሳይ በቀድሞ አዋጅ ‹‹ዘርፍ›› በሚል መጠሪያ ኢንዱስትሪውን የሚወክለው ደግሞ ለብቻቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በሚል መጠሪያ ራሱን ችሎ እንዲወጣ ተወስኗል፡፡ በዚሁ መሠረት የአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ረቂቅ የተዘጋጀ ሲሆን በረቂቅ ሰነዱ ላይም ባለፈው ቅዳሜ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መካሄዱን ሪፖርተር አረጋግጧል።በመሆኑም ሁለቱ ረቂቅ አዋጆች በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያለውን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አዋጅ በመተካት ለበርካታ ዓመታት አንድ ላይ የቆዩትን የንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለሁለት የሚከፍል ይሆናል፡፡ የንግድ ዘርፉን የሚመለከተው ረቂቂ አዋጅ ሲሰናዳ የቆየው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት እንደሆነ የሚታወስ ሲሆን፣ ለመጀመርያ ጊዜ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በመነጠል የአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤትን ለማቋቋም በተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበት ተደርጓል።ረቂቆቹ ንግድም ሆነ ኢንዱስትሪ ምክር ቤቶቹ አደረጃጀትና አሠራርን የሚያመለክቱ አንቀፆችን ያካተቱ ሲሆን የኃላፊነት ድርሻና ተግባራቶቻቸውንም የያዙ ናቸው ተብሏል፡፡ ንግድና ዘርፉን ለየብቻ ነጣጥሎ ከታች እስከ አገር አቀፍ ድረስ በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ማድረጉ ጥቅምና ጉዳቱ በተለያዩ መንገድ እየተገለጸ ሲሆን ብዙዎች ኢንዱስትሪውንና ንግዱን ለየብቻ ማድረጉ ለየዘርፉ ነፃነትን የሚሰጥ እንደሆነ ያምናሉ። አሁን ባለው አዋጅ በዘርፉና በንግዱ መካከል ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ከማስቀረቱም በላይ የአባላት ተጠሪነት ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወይም ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚል ይፈጥር የነበረውን ብዥታ የሚያፀዳ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተለይም ኢንዱስትሪ ዘርፉ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ይህ አደረጃጀት ጠቃሚ መሆኑንም የሚልጹ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢንዱስትሪም ሆነ ንግድ ተመሳሳይ የቢዝነስ ባህሪ የሚታይባቸው በመሆኑ መነጣጠሉ ተገቢ አለመሆኑንና ከዚህ ቀደም በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ እንደበረው የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል ረቂቁ በጥምረት ቢዘጋጅ የተሻለ መሆኑን የሚገልጹም ይደመጣሉ። እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው የንግድ ምክር ቤት አባላት በሌላው ዓለምም ብዙዎቹ አገሮች ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በሚል የተቋቋሙ በመሆናቸውን በመጥቀስ በኢትዮጵያም በዚሁ አግባብ መቀጠሉ ይመረጣል ይላሉ፡፡ ሁለቱን ዘርፎች ለሁለት ከፍሎ በተናጥል ለማቋቋም የተረቀቁትን አዋጆች የሚደግፉ ወገኖች ደግሞ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉበትን በርካታ ተግድሮቶች ለመቅረፍና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረውን እምቅ አቅም ለማውጣት ራሱን ችሉ መደራጀቱ ጠቃሚ እንደሆነ ይገልጻሉ።ይህ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁ ለመጀመርያ ጊዜ እንደመዘጋጀቱ መጠን ወደ ትግበራ ሲገባ ችግር እንዳይኖረው በቂ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚጠበቅበትን አገራዊ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ለማጉላት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አደረጃጀትም በዚሁ አግባብ እንዲደራጅ በማስፈለጉ ረቂቅ አዋጁ በዚሁ መልኩ መዘጋጀቱን በውይይት መድረኩ ላይ የሚገኙት የንግድ ሚኒስቴር አማካሪ ገልጸዋል፡፡ አማካሪው አቶ አስፋው አበበ የኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ዕድገት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንዲህ ያለው አደረጃጀት አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ማብራሪያ መስጠታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ እስካሁን በነበረውና የኢንዱስትሪ ምክር ቤቶች ከንግድ ምክር ቤቶች ጋር አብረው እንዲደራጁ መደረጉ አምራች ኢንዱስትሪ ጎልቶ እንዳይወጣ የማድረግ ዕድሉ ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ ይህንን ክፍተት ለመድፈን በኢንዱስትሪው ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ጠንካራ የአምራች ኢንዱስትሪ ምክር ቤት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ መሆኑን ተናግረዋል።የንግድ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ከ80 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ሲሆን የአገሪቱን የንግድ ኅብረተሰብ በመወከል በተለያዩ መጠሪያዎች ሲቀሰቀስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡