ቺያራ ፌግራኒ

ከ 5 ሰአት በፊት

የጣሊያ ማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ይዘታቸውን በሚለጥፉበት ጊዜ ልክ እንደ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን በተመሳሳይ ህጎች ሊገዙ ይችላሉ ተብሏል።

የተፅዕኖ ፈጣሪዎች እንቅስቃሴ በጣሊያን ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ቁጥጥር ስር ሊገባ ነው ሲል ተቋሙ ተናግሯል።

ደንቦቹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ባሏቸው የይዘት ፈጣሪዎች ላይ ቀድመው ተፈጻሚ ይሆናሉ።

የባለስልጣኑ ኃላፊ ጂያኮሞ ላሶሬላ “የተፅዕኖ ፈጣሪዎች እንደፈለጉ መሆን አብቅቷል” ብለዋል።

“እኛ ከትላልቆቹ ነው የምንጀምረው። ነገር ግን ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪዎችም መላመድ አለባቸው” ሲሉ ለላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ታዋቂ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ማስታወቂያ እየሠሩ እንደሆነ በግልጽ ካላስቀመጡ ወይም የንግድ ግንኙነታቸውን ይፋ ካላደረጉ ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

መመሪያዎቹ ህጻናትን ለመጠበቅ ያለሙ ሲሆኑ በአዲሱ የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከተቋማት እና ከንግድ ጥቅማቸው ጋር ያላቸውን ትብብር በትክክል ማስተዋወቅ ያልቻሉ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች 250 ሺህ ዩሮ የሚደርስ ቅጣትን ጨምሮ እስከ ከባድ ቅጣቶች ይጠብቃቸዋል።

ባለስልጣኑ በመግለጫው እንዳስታወቀው እርምጃዎቹ “የንግድ ግንኙነቶችን፣ የሰዎችን መሠረታዊ መብቶችን፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን እና የስፖርት እሴቶችን መጠበቅን ይመለከታሉ” ብሏል።

ምርት በማስቀመጥ የሚደረግን ማስታወቂያ በተመለከተ ደግሞ ”ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስለማስታወቂያው ይዘት ማስጠንቀቂያ ማስገባት አለባቸው” ብሏል መግለጫው።

ብዙዎች የባለስልጣኑን ውሳኔ ከጣሊያን ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ቺያራ ፌራግኒ ጋር የተገናኘ እንደሆነ አድርገው ቢመለከቱትም ላሶሬላ ግን ውድቅ አድርገውታል።

ባለፈው ታህሳስ በኢንስታግራም ላይ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሏት ፌራግኒ “ከዲዛይነር” ሮዝ የገና ኬክ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በቱሪን የሚገኘውን የሕጻናት ሆስፒታል ይደግፋል በማለቷ 1.075 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጥታለች። የኬኩ አዘጋጅ ኬኩ ለሽያጭ ከመዋሉ ከወራት በፊት ገንዘቡን ለሆስፒታሉ ሰጥቷል።

በኋላም ለተከታዮቿ ባሰራጨችው መግለጫ “የንግድ እንቅስቃሴን ከበጎ አድራጎት ጋር በማያያዝ…በቅን ልቦና የተሠራ ስህተት ነው” ስትል ተናግራለች።

የጣሊያን ፖሊስ በበኩሉ ባለፈው ሳምንት ፌራግኒ በገና ኬክ ወይም በፓንዶሮ ጉዳይ ላይ በማጭበርበር ወንጀል ምርመራ እንደሚደረግባት አስታውቋል።

ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ላይ ጥብቅ ህጎች የሚያሳርፈው አሠራር ባለፈው ዓመት ነው በሌሎች የአውሮፓ አገራት የወጣው።

ባለፈው ሰኔ ፈረንሳይ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አዲስ የማስተዋወቂያ ደንቦችን ጥሰው ከተገኙ የእስራት ጊዜ ሊጠብቃቸው እንደሚችል የሚገልጽ ህግ አውጥታለች። ይህም በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የአውሮፓ ኮሚሽን በበኩሉ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች “ፍትሃዊ የንግድ ልምዶችን መከተል እና ተከታዮቻቸው ግልጽ እና አስተማማኝ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው” በመግለጽ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴዎችን እና የተፅዕኖ ፈጣሪዎችን መከታተሉን እንደሚያጠናክር አስታውቋል ።