
ከ 5 ሰአት በፊት
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ እያቀኑ ነው። እየገሰገሱ ነው ማለት ይቀላል።
በተለይ በሪፐብሊካኖች ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተወዳጅ ሆነዋል።
ጠላትም ወዳጅም እየመሠከረ ያለው ይኸው ነው።
እስካሁን ያለው ተደማምሮ ትራምፕ 91 ክስ አለባቸው። ፍርድ ቤት በቀረቡ ቁጥር ታዲያ ተወዳጅነታቸው ይጨምራል።
አሁን አሁን ሰውዬው ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠላትም ወዳጅም እየጠረጠረ ነው።
ከሰሞኑ በአይዋ ግዛት የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ለመምረጥ የተሰጠው ድምጽ ስለ ትራምፕ የዋይት ሐውስ ጉዞ ብዙ ይናገራል።
ያገኙት ድምር ድምጽ 56 ሺህ 200 ነው። የፍሎሪዳው ሮን ዴሳንቲስ ያገኙት ድምጽ ከትራምፕ በእጥፍ ያንሳል።
ይሄ ብቻ አይደለም አስገራሚው፤ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ፣ ወጣቱ ቢሊየነር ቪቪክ ራማስዋሚ፣ የቀድሞው የትራምፕ ወዳጅ-የአሁኑ ተቀናቃኝ ክሪስ ክሪስቲ እና ሌሎች ሁሉም ተፎካካሪዎቻቸው ያገኙት ድምጽ ቢደመር ከትራምፕ አይበልጥም።
ይህ ይህ ሲታይ ምንም እንኳ ለምርጫው 10 ወራት ቢቀሩትም፣ ትራምፕ 60ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ይመስላል።
ለመሆኑ ትራምፕን ሪፐብሊካኖች ዘንድ ተወዳጅ ያደረጓቸው ነገሮች ምንድናቸው?
- የሐማስን የጥቃት ዝግጅት ቀድመው ሪፖርት ቢያደርጉም ሰሚ ያላገኙት የእስራኤል ‘ዐይኖች’17 ጥር 2024
- የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችሉ እንደሆነ ብይን ሊሰጥ ነው6 ጥር 2024
- ትራምፕን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያገዱት ዳኞች የግድያ ዛቻ እየደረሳቸው መሆኑ ተገለጸ27 ታህሳስ 2023
ነዳጅ ተወደደ
እሳቸው ከሄዱ በኋላ ነዳጅ በአሜሪካ ተወደደ። ምጣኔ ሃብቱ ተንኮታኮተ ይላሉ የትራምፕ ወዳጆች እና የጆ ባይደን ነቃፊዎች።
“ትራምፓችን ሲመጣ ነዳጅ ዝቅ-ምጣኔ ሃብቱ ከፍ ይልልናል” ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
እርግጥ ትራምፕ ፕሬዝዳንት በነበሩ ጊዜ ኢኮኖሚው ጥሩ ይዞ ነበር። ይሁንና በትራምፕ ጊዜ ብቻ አይደለም ይህ የሆነው። በኦባማ ጊዜም የበለጠ ጥሩ ነበር።
እርግጥ በትራምፕ ጊዜ የነበረው ኢኮኖሚ በኮቪድ ተመሳቀቃሎ ነበር።
በጆ ባይደን ዘመን የዩክሬን ጦርነት የነዳጅ ዋጋን አናረ። የዋጋ ንረቱ በ40 ዓመት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ምጣኔ ላይ ደረሰ።
ይሁንና አሁን በአሜሪካ ዋጋ ንረቱ እየተረጋጋ ነው። ካለፈው ዓመት ዘንድሮ ምጣኔ ሃብቱም ጠንክሮ ነው ያለው። ብዙ ነገሮች የትራምፕ ደጋፊዎች እንደሚያስወሩት የከፉ አይደሉም።
ኢኮኖሚው በየወሩ በመቶ ሺዎች ሥራ እየፈጠረ ነው።
የትራምፕ ደጋፊዎች ግን አሜሪካ እና ኢኮኖሚዋ የሚበረታው በትራምፕ እና በትራምፕ ሲመራ ብቻ ነው ይላሉ።

“እንቅልፎ ጆ’’
የትራምፕ ደጋፊ ቢሊ ብላትራስ ትራምፕ ንቅት ያሉና ኃያል ናቸው ይላሉ። ያን ጉልበት ወደ ዋይት ሐውስ መመለስ እንሻለን ነው የሚሉት ብዙዎቹ።
ጆ ግን ዕድሜ ተጫናቸው። እጅ አልሰጥም ቢሉም ከደረጃ እየተደነቃቀፉ ተቸገሩ። አንዴ ቢሆን እሺ፤ ተደጋገመ። ይህ ለስም እና ለዝናቸው አሉታዊ ሚና ተጫወተ።
ትራምፕ ደግሞ ሁልጊዜም በጆ ባይደን ማፌዝ ይወዳሉ። ደጋፊዎች በሳቅ ያጅቧቸዋል። እርግጥ በሁለቱ ሰዎች መሀል ያለው የዕድሜ ልዩነት ትልቅ የሚባል አይደለም። ትራምፕ ግን ቢያንስ በካሜራ ፊት ተደነቃቅፈው አያውቁም።
አንዳንድ ደጋፊዎች ደግሞ አሜሪካ መመራት ያለባት በቢዝነስ ሰው እንጂ በፖለቲከኛ አይደለም ይላሉ። ትራምፕ በቢዝነሱ ዓለም መቆየታቸው እና የስክሪን ዝና ማግኘታቸው ድምጽ ሆኗቸዋል።
ትራምፕ በንግግራቸው ስል እና ቀጥተኛ ናቸው። ውስብስብ የፖለቲካ ትንታኔ አያውቁም። ንግግራቸው ፊደል ላልቆጠረ የሚዘልቅ ነው። ጠላቶቻቸውን በማንጓጠጥ ላይ ስለሚያተኩሩ ብዙኃኑን የማዝናናት፣ በሰፊው ሕዝብ የመሰማት ዕድል ሰጥቷቸዋል።
ጆ ባይደን በዚህ ረገድ አልታደሉም። ኮፕ 26 የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋቸው ካሜራ ቀብ አደረጋቸው። ከዚያ ወዲያ የትራምፕ እና የደጋፊዎቻቸው መሳቂያ ሆኑ። ‘እንቅልፎ ጆ’ የሚለው ቅጽል ከዚያ የጀመረ ዛሬም ድረስ አለ።

ስደተኞች እንደ ‘አደገኛ ቦዘኔዎች’
በዚህ ዓመት ምርጫ እንደ ስደተኞች ጉዳይ አከራካሪ ነጥብ የሚኖር አይመስልም።
በደቡባዊ ቴክሳስ ድንበር በቀን በአማካይ 10 ሺህ ስደተኛ ወደ አሜሪካ ይገባል።
ይህ ነገር ብዙ አሜሪካዊያንን አስቆጥቷል።
ትራምፕ ነገሩ ያበገናቸው ይምሰሉ እንጂ ድምጽ ለማግኘት የተመቻቸው ክስተት ነው እየሆነ ያለው።
የቴክሳሱ ገዥ አውቶቡስ ጭምር እያቀረበ ስደተኛን ዲሞክራቶች ወደ ሚመሯቸው ግዛቶች ይሸኛሉ። ኒው ዮርክ ነገሩ ከአቅሜ በላይ ነው፤ ፌዴራል መንግሥት ያግዘኝ ማለት ከጀመረች ሰነባብታለች።
ጆ ባይደን በስደተኞች ላይ ያሳዩት ዳተኝነት ዋጋ እያስከፈላቸው ነው።
ትራምፕ በበኩላቸው አገራችን የማንም ‘ወመኔ-ሌባ-ቀማኛ እና አደገኛ ቦዘኔ መናኸሪያ ሆነች’ እያሉ ነገሩን ከፍተኛ ደረጃ አደረሱት።
ይህ አልበቃ ብሏቸው የናዚዎችን ቃል በመጠቀም ‘ስደተኞችን የአገራችንን ደም በከሉት’ ብለው ተናግረዋል ትራምፕ። ይህ ንግግራቸው ብዙዎችን አስደንግጧል።
ትራምፕ አሁን ለደጋፊዎቻቸው ቃል እየገቡ ካሉት መካከል አንዱ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።
ምረጡኝ እንጂ በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አገራችን የገባውን ስደተኛ በሚሊዮኖች ጠራርጌ አስወጣለሁ፤ ወደመጣበት እመልሰዋለሁ ብለዋል።
ወጣት መራጮች ወደ ትራምፕ
ኒው ዮርክ ታይምስ በሠራው የዳሰሳ ጥናት ትራምፕ በወጣቶች ዘንድ በተለይም ከ18 እስከ 29 ባሉት ዜጎች ተወዳጅ ሆነዋል።
በ2020 ምርጫ በዚህ ዕድሜ ያሉት የጆ ባይደን ወዳጆች ነበሩ። ይህን ነገር ምን ገለበጠው የሚለው መጠናት ይፈልጋል።
አንዱ ግምት ግን ጆ ባይደን የእስራኤል ጋዛ ግጭትን ያስታመሙበት መንገድ ነው።
ሌላው ግምት ደግሞ ትራምፕ መድረክ ወጥተው የሚናገሩበት መንገድ፣ መድረክ አያያዛቸው እና ዋዛና ለዛቸው ከጆ ባይደን ልቆ መገኘቱ ነው።

በተከሰሱ ቁጥር መወደድ
ትራምፕ አራት ጊዜ በወንጀል ተከሰዋል። እጅግ በርካታ የፍርድ ቤት ቀጠሮዎች ይጠብቃቸዋል።
አስገራሚ የሆነው ግን በተከሰሱ ቁጥር፣ ፍርድ ቤት ደጅ በደረሱ ቁጥር ወዳጃቸው እየጨመረ መምጣቱ ነው።
ትራምፕ በኒው ዮርክ፣ በጆርጂያ፣ በፍሎሪዳ፣ በማንሃታን፣ በዋሺንግተን የክስ ፋይል ተከምሮባቸዋል።
አሁን የብዙዎች ጥያቄ እነዚህ ክሶች ትራምፕን ከዋይት ሐውስ ጉዞ ያደናቅፏቸዋል ወይ የሚለው ነው።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በዚህ ረገድ የሚጠበቅ ሆኗል።
ትራምፕ የወንጀል ተጠርጣሪ ሆነው ፖሊስ ጣቢያ የተነሱት ፎቶ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል።
በአሜሪካ ታሪክ እንዲህ ያለ ነገር ታይቶ አይታወቅም። ክስ የተመሠረተበት ፖለቲከኛ ችግር ውስጥ ይወድቃል እንጂ እያማረበት – እየተወደደ አይመጣም። ትራምፕ ግን ይለያሉ።
ፍራንክ ላንስ የፖለቲካ ትንበያ ባለሙያ ነው። ለቢቢሲ ሲናገር “ትራምፕ መጥፎ አጋጣሚን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ችሏል። ክሱ በዲሞክራቶች የተቀነባበረ የፖለቲካ ክስ እንደሆነ ደጋፊዎቹን በማሳመኑ ተሳክቶለታል” ይላል።
“በተከሰሰ ቁጥር ድጋፉ ይጨምራል፤ በሜይን እና በኮሎራዶ ግዛቶች ስሙን ከድምጽ መስጫ ሲፍቁት ደጋፊዎቹ ይበልጥ ጨመሩ። እንዲህ ዓይነት ነገር በአሜሪካ ታሪክ አይተንም አናውቅ” ይላል።
አሁን ትራምፕ የሪፐብሊካን ዕጩ ለመሆን በአይዋ ግዛት ያሳኩትን ድል በሚቀጥለው ሳምንት በኒው ሐምፕሻየር መድገም ነው የሚጠበቅባቸዋል።
አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ለደጋፊዎቿ “አሜሪካ ተጨማሪ ተመሳሳይ ነገር አያስፈልጋትም” በሚል ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ትራምፕ እና ጆ ባይደን ያረጁ ያፈጁ ናቸውና እኔን ምረጡ እያሉ ነው።
የፍሎሪዳው ዴሳንቲስ እና አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ለሁለትም ሆነው ትራምፕን ለመጣል የሚችሉ አይመስልም።