በጋዛ ጉዳት ከደረሰባቸው መስጂዶች አንዱ
የምስሉ መግለጫ,በጋዛ ጉዳት ከደረሰባቸው መስጂዶች አንዱ

ከ 6 ሰአት በፊት

ጋዛ የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እና መስጂዶች መገኛ ናት።

ነገር ግን እኒህ የእምነት ሥፍራዎች የእስራኤልን ድብደባ መቋቋም የቻሉ አይመስሉም።

ቢቢሲ ባለፈው መስከረም መጨረሻ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በግቱጭ ምክንያት የተጎዱ አሊያም የወደሙ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ሲመዘግብ ቆይቷል።

ይህን ያደርግነው ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎችን፣ ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ መልዕክቶች እና የሳተላይት ምስሎችን በመጠቀም ነው።

በቆጠራችን መሠረት ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ውስጥ 117 ሥፍራዎች ተጎድተዋል አሊያም ወድመዋል።

ከእኒህ መካከል 72 መስጂዶች እና ሁለት አብያተ ክርስቲያናት በከፊል እና ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ማረጋገጥ ችለናል።

እርግጥ ነው ሐማስ ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ የላቀ ነው ይላል።

ቢሆንም እኒህን የተጎዱ ቤተ-እምነቶች ቆጥሮ መመዝገብ ቀላል ሥራ አይደለም።

የሳተላይት ምስሎች ሙሉ በሙሉ የወደሙ እንጂ በከፊል የተጎዱ ሕንፃዎችን አያሳዩም። አንዳንድ ሕንፃዎች ስለመወድማቸው ሙሉ መረጃ ማግኘት ከባድ ሆኖ ይገኛል።

ሐማስ ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ 378 መስጂዶች እና ሦስት አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል ይላል።

“የእስራኤል ወራሪ ኃይል መስጂዶችን በቦምብ ሲደበድብ የመጀመሪያው ባይሆንም የዘንድሮው ውድመት ግን ከሁሉ የከፋ ነው” ይላል መግለጫው።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ደግሞ ሐማስ የእምነት ሥፍራዎችን እንደ መጠለያ እና የጥቃት መሰንዘሪያ እየተጠቀመ ነው ሲል ይከሳል።

በጋዛ የሚገኘው የወደመው የቅዱስ ፖርፊሪየስ ቤተ ክርስቲያን
የምስሉ መግለጫ,በጋዛ የሚገኘው የወደመው የቅዱስ ፖርፊሪየስ ቤተ ክርስቲያን

“ፈጣን ሞት ነበር”

ቅዱስ ፖርፊሪየስ በዓለማችን ካሉ ጥንታዊ ቤተ-ክርስቲያናት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል። በጋዛ ሰርጥ ከተሰደሩ ቤተ-እምነቶች አንዱ ነው።

የጋዛ ክርስቲያኖች ቁጥራቸው እምብዛም አይደለም። ከጦርነቱ በፊት አንድ ሺህ ገደማ ነበር።

እኒህ የጋዛ ክርስቲያኖች በቤተ-ክርስቲያኑ ዙሪያ ካለው መሬት ጋር ትልቅ ቁርኝት አላቸው። ቤተ-ክርስቲያኑ ስያሜውን ያገኘው በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩ ጳጳስ ሲሆን፣ የመቃብር ስፍራቸውም እዚያው ይገኛል።

እንደ አብዛኞቹ የጋዛ ክርስቲያኖች ማሪያን ሳባ እና ቤተሰቦቿ በጦርነቱ ጊዜ የተጠለሉት በዚህ ቤተ-ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ነው።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 19 አመሻሽ ገደማ ከእስራኤል የተወነጨፈ ሚሳዔል አንዱን የቤተ-ክርስቲያኑን ሕንፃ መታው። በጥቃቱ 18 ሰዎች ተገደሉ፤ በርካቶች ቆሰሉ።

ማሪያን እንደምትለው የ34 ዓመቱ የባሏ ወንድም ሶሊማን ልጆቹን ከሕንፃው ፍርስራሽ ሲከላከል ሕይወቱ አልፏል።

“በጣም አስፈሪ ነው። የሞተ ሰው አይቼ አላውቅም። ምን ማለት እንዳለበኝ አላውቅም። በጣም ፈጣን ሞት ነበር።”

ራሚ ታራዚ ደግሞ ሕንፃው በሚሳዔል ሲመታ በሥፍራው የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “ከባድ ሚሳዔል ነው። በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በሌላኛው ሕንፃ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አቧሯ ለብሰው ነው የወጡት” ይላል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቤተ-ክርስቲያኑ በአቅራቢያው በነበረ የሐማስ ይዞታ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት እንደተጎዳ አምኗል።

የኻሊድ አል-ዋሊድ መስጂድ
የምስሉ መግለጫ,ኻን ዩኒስ ውስጥ የሚገኘው የኻሊድ አል-ዋሊድ መስጂድ በእስራኤል ሠራዊት እንደተመታ ይነገራል

በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ሕግ መሠረት ሆነ ብሎ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር የጦርነት ወንጀል ነው። ነገር ግን እኒህ ሥፍራዎች ለወታደራዊ አገልግሎት ጥቅም ላይ ውለው ከሆነ ላያስጠይቅ ይችላል ይላል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ የእስራኤል መከላከይ ሠራዊት ቪድዮዎች፣ የእስራኤል ሠራዊት ወደ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ሲገቡ እና የሐማስ ናቸው ያሏቸውን የቤተ-እምነቶቹ የምድር ቤቶችን ሲያስመለክቱ ያሳያሉ።

አንዳንድ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች ደግሞ የእስራኤል ወታደሮች ሃይማኖታዊ ሥፍራዎችን ሲያንቋሽሹ እና ውድመቱን ሲያደንቁ አሳይተዋል።

በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ላይ የተለጠፈ ቪድዮ፣ አንድ የእስራኤል ወታደር የወደቀ ሃይማኖታዊ ሕንፃን በእብራይስጥ ቋንቋ ሲያቆሽሽ አስመልክቷል።

ቢቢሲ ለእስራኤል መከላከያ ይህን ቪድዮ ልኮ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአርኪዮሎጂ ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ጆርጂያ አንድሪው፣ በጋዛ ሰርጥ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕንፃዎች ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ፕሮፌሰሯ እኒህ ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች በጣም ትልቅ ታሪካዊ ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ።

“[ጥቃቱ] ሰዎች ከእነዚህ ሕንፃዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማጥፋት እንደተደረገ ሙከራ ነው መታየት ያለበት” የሚሉት ምሑሯ መሰል ውድመት አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

ካርታ

“የፀሎት ድምፅ ይናፍቀኛል”

በጋዛ በርካታ መስጂዶች ወድመዋል። የፍልስጤም ሙስሊሞች በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከሚጠለሉ ይልቅ ከእምነት ሥፍራዎች ራቅ ብለው ነው ከጥቃቶች እየተሸሸጉት የሚገኙት።

ኻን ዩኒስ በተሰኘችው ሥፍራ ኻሊል አል-ራህማን መስጂድ በአየር ድብደባ መውደሙን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

ሬናድ አላ አል-ባታ ይህን መስጂድ ታዘወትር ነበር። ቁራን የቀራችውም እዚህ ነው። ነገር ግን ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ወደዚህ ስፍራ መጥታ አታውቅም።

ባለፈው ኅዳር አንድ ሳምንት በቆየው የተኩስ አቁም ወቅት አዛን ሲባል የነበረው ከኻሊል አል-ራህማን ፍርስራሽ እንደነበር ታስታውሳለች።

ኻን ዩኒስ በነበረው ጦርነት ወቅት ብቅ ብለው ከነበሩ ምስሎች መካከል አንዱ የኻሊል አል-ራህማን መስጂድ መውደም ነው።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፈውን ምስል ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አይተውታል።

ቢቢሲ መውደማቸው አሊያም መመታቸውን ካረጋገጣቸው ሕንፃዎች መካከል ምን ያህሉ በእስራኤል ጦር ኃይል እንደተመቱ ወይም ደግሞ በሐማስ ጥቅም ውለው እንደነበር ማጣራት አልቻለም።

ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ ሕግ ተከትዬ የሐማስን ወታደራዊ ክንፍ ለመስበር እየተንቀሳቀስኩ ነው ይላል።

የኻሊድ ቢን አል-ዋሊድ እና የኻሊል አል-ራህማንን መስጅዶች ውድመት በተመለከተ የእስራኤል ጦር አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ምንም እንኳ በጋዛ ያሉ በርካታ የእምነት ሥፍራዎች ቢወድሙም ጋዛውያን ያላቸው መጠለያ እምነታቸው ነው።

ማሪያን ሳባ እና ቤተሰቦቿ እንዲሁም ሌሎች 300 ገደማ ሰዎች አሁን በቅዱስ ፖርፊሪየስ ቤተ-ክርስቲያን ተጠልለው ዘወትር ሰንበት አምላካቸውን ይማፀናሉ።

ሬናድም እንዲሁ በየቀኑ ቁራን ታነባለች። “የምሽቱን ክብደት ይቀንስልኛል። በጋዛ ምሽቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማን በነገረልኝ” ትላለች።

ካርታ