
ከ 4 ሰአት በፊት
በአራት መዝገብ 91 ክሶች ያሉባቸው ዶናልድ ትራምፕ በችሎት ዳኛን አንጓጠጡ።
ትናንት በኒው ዮርክ ማንሐተን ባስቻለው ችሎት ዶናልድ ትራምፕ ችሎቱን በመዳፈራቸው ዳኛ ካፕለን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ተገደው ነበር።
“እርስዎ ሰውዬ ሥነ ሥርዓት የማይዙ ከሆነ ከችሎቱ አባር’ዎታለሁ” ሲሉ የተናገሩት ዳኛ ካፕለን ከትራምፕ ያገኙት መልስ “ደስ ይለኛል” የሚል ነበር።
“ራስዎን መቆጣጠር አይችሉም፤ ምናልባት ከችሎቱ እንዳባርርዎ እየሻቱም ይመስለኛል” ሲሉ ዳኛ ካፕለን በብስጭት ተናግረዋል።
ትራምፕ ከችሎቱ መጠናቀቅ በኋላ ዳኛውን “አስቀያሚ ሰውዬ ነው” ሲሉ ዘልፈዋል።
የአየዋ ካውከስን ምርጫ በከፍተኛ ድል አጣጥመው ወደ ማንሐተን ያቀኑት ትራምፕ ትናንት የተገኙበት ችሎት በቀድሞዋ አምደኛና ደራሲ ኢ ጂን ካረል የቀረበባቸውን የመድፈር፣ የስም ማጥፋትና ጾታዊ ትንኮሳ ክስ ለመከላከል ነበር።
ኢ ጄን ካረል በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ ዶናልድ ትራምፕ ኒው ዮርክ፣ መንሐተን በሚገኝ አንድ መደብር ውስጥ ጾታዊ ትንኮሳ አድርሰውብኛል የሚል ክስ ካቀረቡ ሰነባብቷል።
ጋዜጠኛና ደራሲ ኢ ጂን ካረል በዚህ ክስ በማሸነፋቸው 5 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንደተበየነላቸው ይታወሳል።
የዚህን ክስ ተከታይ ለመስማት ነበር የትናንቱ ችሎት የተሰየመው።
የዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ የሆኑት አሊና ሐባ ከሳሽ (አሁን 80 ዓመት ሆኗቸዋል) ጋዜጠኛ ኢ ጂን ካረል ይህን ክስ ዝናን ለማካበት እየተጠቀመችበት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በዚህ ችሎት ትራምፕ ከዳኛው ጋር የተካረረ የቃላት ልውውጥ በማድረጋቸው ከችሎት ሊባረሩ ጫፍ ደርሰው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕን በጾታ ትንኮሳ የከሰሷቸውን ደራሲና ጋዜጠኛ ኢ ጂን ካረልን “ቀጣፊ’’ ሲሉ ተሳድበዋል።
ክሱንም ‘የተጭበረበረና ሐሰተኛ’ ብለው አጣጥለውታል።
ጋዜጠኛና ደራሲዋ ጂን ካረል በበኩላቸው ለ50 ዓመታት የገነባሁት መልካም ስምና ዝና በዶናልድ ትራምፕ ቅጥ ያጣ ዘለፋ ጠፍቷል ሲሉ ለፍርድ ቤት አቤት ብለዋል።
“አሁን አገሩ በሙሉ የሚያውቀኝ ዉሸታም፣ አጭበርባሪና ዝና ፈላጊ አድርጎ ነው” ያሉት የ80 ዓመቷ ሴት በዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የሚደርስባቸውን ተከታታይ ዘለፋና ዛቻ ለፍርድ ቤቱ አብራርተዋል።
“አሁን እዚህ የተገኘሁት የጠፋውን ስሜን ለማደስ ነው” ሲሉም ለችሎቱ ተናግረዋል።
የኢ ጂን ካረል ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው የሚደርስባቸውን የዛቻ መልእክቶች ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።
በዶናልድ ትራምፕ ከሳሽ ላይ የእንገድልሻለን፣ የእንደፍርሻለን እና ተከታታይ የስድብ ዛቻዎች እንደሚደርሱባቸው በዝርዝር አቅርበዋል ጠበቃዋ።
ለምሳሌ አንድ ለጂን ካረል የደረሳቸው መልእክት “ሽጉጡን አፍሽ ውስጥ ክተቺውና ቃታውን ሳቢው” የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “አንቺ ሴት ሰይጣን አምላኪ ናዚ ነሽ” የሚል ነው።
- የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በቀረበበት ጊዜ ዶናልድ ትራምፕ ለምን ተወዳጅ እየሆኑ መጡ?ከ 5 ሰአት በፊት
- የደጋ ሰው “የዘመኑ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ድምጽ”ከ 6 ሰአት በፊት
- በጋዛ ምን ያህል የእምነት ተቋማት ወደሙ? ምዕመናንስ የት ተጠለሉ?ከ 6 ሰአት በፊት
ይህን የመሰሉ መልእክቶች ወደ ከሳሿ ጂን ካረል መድረስ የጀመሩት ዶናልድ ትራምፕ ሴትዮዋን “ቀጣፊና አጭበርባሪ ናት” ብለው ከፍተኛ ማጥላላት ዘመቻ ከከፈቱ ወዲህ ነው።
በጂን ካረል የቀረቡ ዛቻዎች በስፋት ለችሎቱ ተሰምተዋል።
በዚህ ወቅት የትራምፕ ጠበቃ ተቃውሞ አለኝ ብለው በመነሳት ‘ይህ ስጋት ካለብሽ በቅርቡ በትራምፕ ታወር በኩል ስታልፊ ፈገግ ብለሽ ለምን ፎቶ ተነሳሽ-የዝና ጥማት ካልሆነ ማለቴ ነው” በሚል ተቃውሞ አቅርበዋል።
ጂን ካረል ለዚህ የሰጡት ምላሽ በዚያ በኩል በርካታ ፖሊስ ከላለ ስለተመለከትኩ የተሻለ ደኅንነት ተሰምቶኝ ነው እንጂ ሕይወቴ በስጋት የተሞላ ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ በብስጭት አንገታቸውን ሲነቀንቁ ታይተዋል።

የዶናልድ ትራምፕ ጠበቃ አሊና ሓባ፣ ከሳሽ የመደፈርም ሆነ ጾታዊ ትንኮሳ እንዳልደረሰባትና የምትፈልገው ዝና ብቻ እንደሆነ ፍርድ ቤቱን ለማሳመን ሞክረዋል።
ይህን ነጥብ ለመሞገትም በቅርብ ጊዜ ጂን ካረል ለበርካታ ቴሌቪዥንና ራዲዮ እንዲሁም ፖድካስቶች የሰጧቸውን ቃለ መጠይቅ እንዲሁም መጽሐፍ እየጻፉ እንደሆነና ይህንንም በስፋት እያስተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“ዝና የጠማሽ ሴት ነሽ፤ አይደለም እንዴ?” በሚል የትራምፕ ጠበቃ ለሳሽ ጂን ካረል ቀርቦ ነበር።
ደራሲና ጋዜጠኛ ጂን ካረል ለዚህ በሰጡት ምላሽ “በቃለ ምልልሶቻቸው ወቅት ስለ ትራምፕ በተደጋጋሚ ስለምጠየቅ ነው እንጂ ስሙን ባላነሳው እመርጣለሁ” ብለዋል።
ችሎቱ ከሰዓት በድጋሚ ሲሰየም በትራምፕና በዳኛው ሚስተር ካፕለን መካከል ፍጥጫው አይሎ ነበር።
የትራምፕ ጠበቃ ችሎቱ ለሌላ ጊዜ እንዲቀጠር የጠየቁ ሲሆን ምክንያቱም ደግሞ የትራምፕ አማች ስለሞቱ ደንበኛቸው ቀብር መሄድ እንዳለባቸው በማሳሰብ ነበር። ዳኛ ካፕለን “አይሆንም ብያለሁ አይሆንም” የሚል ቁርጥ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከችሎቱ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ ዳኛ ካፕለንን “አጸያፊ ሰውዬ ነው” ሲሉ ዘልፈዋቸዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በፍሎሪዳ፣ በዲሲ፣ በኒውዮርክና በጆርጂያ ተከታታይ ሌሎች ክሶች ያሉባቸው ሲሆን ክሶቹ ግን የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ወደ ዋይት ሐውስ የሚያደርጉትን ግስገሳ ሊገቱ አልቻሉም።
ትራምፕ በአየዋ ያገኙትን ድል በቀጣይ ሳምንት በኒው ሐምፕሻየር እንደሚደግሙት ይጠበቃል።