የደጋ ሰው የድምጻዊት የማርያም ቸርነት (የማ) የመጀመርያ የሙዚቃ ሰንዱቅ

ከ 6 ሰአት በፊት

ከሦስት አህጉራት የተውጣጡ 25 ሙዚቀኞች፤ አራት የግጥም ደራሲዎች እና አንዲት ድምጻዊት፤ የደጋ ሰው አልበምን እውን ያደረገው ጥምረት ነው።

57 ደቂቃ እርዝማኔ ያላቸው 12 የሀገረ ሰብ ሙዚቃዎች በአልበሙ ተካትተዋል።

በመድረክ ስሟ የማ (የማርያም ቸርነት) ሙዚቃዎቹን ተጫውታቸዋለች። የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ ኢዩኤል መንግሥቱ ደግሞ የአልበሙ ፕሮዲዩሰር ነው። ኢዩኤል ሁለት ሙዚቃዎች ላይም በግጥም ድርሰት ተሳትፏል።

ከአልበሙ 2/3ኛውን ግጥም የተደረሰው ‘ጎላ ጎሕ’ በሚል የብዕር ስም በሚጠራ ግለሰብ ነው።

አልበሙ “የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የሆነ የሙዚቃ ባህል ከሌሎች ሀገራት የሙዚቃ ባህል ጋር አዛምዶ የተሰራ” መሆኑን ኢዩኤል ለቢቢሲ ይናገራል።

ከሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪዎች መካከል ቱም፣ መሰንቆ፣ ማይራ እና ዲታ በአልበሙ ውስጥ ተካትተዋል። እነዚህ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንደ አኮርዲዮን እና ፖርቹጊዝ ጊታር ከመሳሰሉት የአውሮፓ ሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ተዋህደዋል።

በዚህ አልበም ላይ የተሳተፈው ዴንማርካዊው ጊታር ተጫዋች ኤልያስ ቤንዲክስ አልበሙን፤ “የዘመኑ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ድምጽ” ሲል አሞካሽቶታል።

ኤልያስ ለአልበሙ ይህን ውደሳ እንዲሰጥ ያደረገበትን ምክንያት ሲገልጽ “ይሄ ሙዚቃ የተሰራው፤ በተፈጠረው በእኛ በአዲስ ትውልድ ሙዚቀኞች ነው” ይላል።

ሌላኛው ምክንያት የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያ ከሌላ ሀገር ሙዚቃ ጋር በማዋሃድ “ጥሩ ድምጽ ማግኘት መቻሉ” መሆኑን ያነሳል።

“ባህሎች ተመሳሳይነት አላቸው፤ ልዩነቱም አላቸው። አንዳንዱ በጣም የተራራቀ ስሜት አለው” የሚለው ኢዩኤል፤ በደጋ ሰው አልበም ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከሌሎች ሀገራት ሙዚቃ ጋር የተዛመደበት መንገድ “ትልቅ ስኬት” መሆኑን ይናገራል።

ኢዩኤል ፕሮዲዩስ ባደረገው አልበም ማሳካት ስለፈለገው ግብ ሲናገር፤ “በእኛ ሀገር ሙዚቃ ላይ ሰፋ ባለ ኦርኬስትራ የመጫወት ባህል እየቀረ መጥቷል፤ እና ያንን እንደገና እንዲያንሰራራ፣ ወይንም እንዲመለስ፣ እንዲታደስ እፈልጋለሁ፤ ምኞትም አለኝ። በአብዛኛው ምኞቴ ተሳትክቷል” ይላል።

የደጋ ሰው አልበም ውልደት ምን ይመስላል?

ቀኑን እና ሰዓቱን በውል ስለማናውቀው፣ ‘ከዕለታት አንድ ቀን’ ብለን እንጀምር።

ከዕለታት አንድ ቀን ኢዩኤል ካፖርቱን አድርጎ፣ እስካርፉን አንገቱ ላይ ጠምጥሞ፣ በፓሪስ ጎዳና እየተንሸራሸረ ነበር።

የሙዚቀኛ ቀልቡ በመንገዱ ላይ ወደተመለከተው የሙዚቃ ካሴት መሸጫ መደብር መራው።

ኢዩኤል በመደብሩ ያገኘው አንድ የሙዚቃ ሪከርዲንግ፣ የሙዚቃ ህይወቱን ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለውን እሳቤ እንደሚያስቀይረው አልገመተም።

የኢዩኤልን የኢትዮጵያ ሙዚቃ አተያይ የቀየረው፣ ‘Bernard Lortat Jacob’ የሚባል ፈረንሳዊ በመስክ ላይ የተቀዱ ሙዚቃዎች ናቸው።

ከፓሪስ መደብር የተሸመተው ሙዚቃ ‘Polyphonies Des Dorzé፤ ይሰኛል። በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ የዶርዜ ህብረ ዝማሬ ማለት ይሆናል።

የዶርዜ ህብረ ዝማሬን ሲሰማ ኢዩኤል “የኢትዯጵያ ሙዚቃ monophonies (ባለ አንድ ዜማ) ነው” የሚለው አረዳዱ መቀየሩን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በተለይ የሁለተኛ ዲግሪዬ መማር ስጀምር፣ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለኝ አረዳድ በጣም ተቀየረ” የሚለው ኢዩኤል፤ ለሙዚቃዊ ጥናት ወደ ጋሞ ያደረገው ጉዞ፣ ለደጋ ሰው አልበም ንሸጣ እንደሰጠው ያስታውሳል።

ኢዩኤል እና የማ ወደ ጋሞ ዞን ቦንኬ መንደር ከመሄዳቸው በፊት አንድ አልበም አገባድደው ነበር።

ሦስት ዓመታት የፈጀውን አልበም ሲያስታውስ “በሌላ ዘውግ ውስጥ ያለ ኮሜርሻል የሆነ ስራ ነው። እሱ ሰው ሊወደው የሚችል ብለን ያሰብነው እና የገመትነውን ዓይነት ስራ ነበር” ይላል።

ለአድማጮች ሊደርስ ጫፍ ደርሶ የነበረው አልበም፣ ለእሷ የአዛዚያም ስልት “ቀለል ያለ” እንደነበር የማ ለቢቢሲ ትናገራለች።

ወደ ጋሞ የተደረገው ጉዞ ግን የኢዩኤልን የኢትዮጵያ ሙዚቃ አረዳድ ብቻ ሳይሆን የተገባደደውን አልበም እጣ ፈንታም የቀየረ ነበር።

“በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል እና በመሀል ሀገር ውስጥ ያለው የሙዚቃ ባህል ነው ብዙ ‘dominate’ አድርጎ ያለው” የሚለው ኢዩኤል፤ “የእነሱ ግን እንደዛ አይደለም፤ ሦስት አራት ድምጽ እስከ ሰባት ድረስ ድምጽ ህብር ያለው ነው” ሲል በቦንኬ መንደር የሰማውን ህብረ ዝማሬ ያስታውሳል።

ኢዩኤል “ከዛ እሱን ማጥናት እንዳለብኝ ተሰማኝ” ሲል ከቦንኬው አጋጣሚ በኋላ የደረሰበትን ድምዳሜ ለቢቢሲ ይናገራል።

ከዚህ ድምዳሜ በኋላ፣ ኢዩኤል እና የማ ፊታቸውን አዲስ ሀገረ ሰብ አልበም ወደ መስራት ፊታቸውን አዞሩ።

ኢዩኤል እና የማ በዚህ ዘውግ አልበም ለመስራት ቢወስኑም “የሀገረ ሰብ ሙዚቃ ለመስራት ገጣሚ ማግኘት ከባድ ነበር” ይላል።

“በአንድ ስራ አጋጣሚ ከጎላ ጎህ ጋር ተገናኘን። ሃሳቤን ነገርኩት፤ ከዛ በኋላ እኛ ባሰብነው መንገድ ጻፈልን” በማለት የአብዛኛዎቹ የሙዚቃ ግጥሞች ደራሲ ጋር የተገናኙበትን አጋጣሚ ያስታውሳል።

በአልበሙ ውስጥ ከተካተቱት ሙዚቃዎች ውስጥ የስምንቱን ግጥም የጻፈው ጎላ ጎሕ በሚል የብዕር ስም የሚታወቅ ግለሰብ ነው።

ከድምጻዊት የማ ጋር በአልበም ስራ ላይ የተሳተፉ አንጋፋ ሙዚቀኞች አክሊሉ ዘውዴ (ሳክስፎን) ጨምሮ

ከዘበናይ ጠጅ ቤት እስከ ሌቦ ሳህሌ

የደጋ ሰው አልበም ውስጥ የተካተቱት የሙዘቃ ግጥሞች ፍቅርን እና ተፈቃሪን የሚያወድሱ ናቸው።

አልበሙ ውስጥ መናፈቅን እንጂ መሰበርን አንሰማም። በሙዚቃዎቹ ውስጥ ለሚወዱት ሰው ስሱ መሆኑን እንጂ መጎዳትን አይደመጥም።

የሙዚቃዎቹ ግጥም ግን ፍቅርን ከማወደስ እና ከማሽሞንሞን በተጨማሪ ሥነ ጽሑፋዊ ውበት እና ለዛ አላቸው።

ለዚህም ምናልባት አብዛኛዎቹን ግጥሞች የደረሳቸው ጎላ ጎሕ ትልቅ ድርሻ አለው።

ጎላ ጎህ በሥነ ጽሑፍ እና በቴአትር ላይ ባሳየው ስኬት እና ዕውቀት የሚታወቅ አርቲስት መሆኑን ኢዩኤል ይናገራል።

የጎላ ጎሕ የሥነ ጽሑፍ እና ቴአትር ልምድ የሙዚቃ ግጥሞቹ ጥልቀት እና ኪናዊ ለዛን የተላበሱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

የደጋ ሰው አልበም የዘፈን ግጥሞች ትውፊታዊ፣ ባህላዊ እና ሥነ ጽሑፋዊ ይዘት አላቸው።

የደጋ ሰው አልበም “ትልቁ ሃቅ ከልብ የመነጨ ነው” የሚለው ኢዩኤል መንግሥቱ፣ በአልበሙ ውስጥ የተካተቱት ስምንቱ ግጥሞች ከጎላ ጎሕ እውነታ እና ከሚያውቃቸው ጉዳዮች የተቀዱ ናቸው ይላል።

በደጋ ሰው አልበም የሙዚቃ ግጥም ውስጥ እምብዛም አይታወቁም ከሚባሉ የደጋ አካባቢዎች እስከ ታሪካዊ ሰዎች (Historical figures) ድረስ ይወደሳሉ።

ከሮቢት ዘበናይ ጠጅ ቤት እስከ አለውሃ ወንዝ፤ ከዶሮ ግብር ቀበሌ እስከ ጎብዬ የራያ የአኗኗር ይትበሃል የሚያንጸባርቁ ስንኞች ይገኛሉ።

በዐጼ ምኒልክ ዘመን የአራዳ ገበያን ካስጨነቀው ሌቦ ሳህሉ እስከ ቃኘው ጦር ዘማቾች ታሪካዊ ሁነቶች እና ክስተቶች የአልበሙ የሙዚቃ ግጥሞች አካል ናቸው።

“ወይ አለመተዋወቅ አለ ሌቦ ሳህሉ” እያለ ዘመነኛው ሰው የሚጠቅሰው ሌቦ ሳህሉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በአታላይነት እና በሌብነት ስሙ የታወቀ ሰው ነበር።

መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በቁመናው እና በልብሱ “የጨዋ ሰው ግርማ ነበር” የሚሉት ሌቦ ሳህሉ፣ እምነት ባለማጉደል አደራ በመጠበቅ ይታወቃል።

ሌቦ ሳህሉ አንድ ክፍለ ዘመን ተሻግሮ፣ ከአራዳ ገበያ ወጥቶ ስሙን ወደ ሌቦ ሳህሌ ለውጦ በደጋ ሰው አልበም ላይ ተከስቷል።

የደጋ ሰው ላይ ያለው ሌቦ ሳህሌ የዘፋኟን ልብ እንጂ ከአራዳ የተገበየን ዕቃ አይደለም የሚጠብቀው።

በደጋ ሰው አልበም የደገኛ አኗኗር፣ የጥንዶች ፍቅር አገላለጽ፣ ለሚወዱት ሰው የሚያቀርቡት ውዳሴ ትውፊታዊ ይዘቱን ሳይለቅ በእያንዳንዱ ሙዚቃ ውስጥ ይሰማል። በደጋ ሰው አልበም ላይ የደጋ ሰውን ፍቅር፣ መውደድ እና እንስፍስፍነት እናደምጣለን።

ሙዚቃ አዋቂዎች፣ ሙዚቃን ሙዚቃ የሚያደርገው ዜማ (melody)፣ ምት (rhythm) እና ህብር (harmony) ነው ቢሉም የደጋ ሰው ሙዚቃ ግጥሞች ግን አልበሙን አንድ ደረጃ ከፍ እንዳደረጉት አይካድም።

የባህላዊ ተወዛዋዦች

የ“በረሃው ብሉዝ” በደጋ

ሰመመን ውስጥ የሚከት ምት (rhythm)፣ ‘እሳታማ’ የጊታር ጨዋታዎች፣ ቀስቃሽ ግጥሞች፣ ስለ ውበት እና ትግል የሚያንጎራጉሩ ጥልቅ ድምጾች የቱዋረግን ሙዚቃ መገለጫዎች ናቸው።

የደጋ ሰው አልበም አቀናባሪው ኢዩኤል በምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ የሚዘወተረው የቱዋረጎች የሙዚቃ ባህል ቀልቡን እንደሚገዛው ይናገራል።

ይህ የሙዚቃ ስልት Desert Blues (የበረሃ ብሉዝ) በሚል ይጠራል። የሙዚቃ ስልቱ ከኢዩኤል በተጨማሪ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድም ተወዳጅ ነው።

ኢዩኤል በምዕራብ አፍሪካ ሙዘቀኞች የሚዘወተሩትን የሙዚቃ መሳሪያዎች ባልተለመደ መልኩ በአልበሙ ውስጥ አካትቷቸዋል።

ከካላባሽ እስከ ኮራ ድረስ በደጋ ሰው አልበም ላይ የተካተቱ የምዕራብ አፍሪካ የሙዚቃ መሳሪያዎች ናቸው። ኢዩኤል እነዚህን መሳሪያዎች ብቻቸውን አላስጮኻቸውም። ከሀገረ ሰብ ሙዚቃ መሳሪያዎች እና ዜማዎች ጋር አዋህዶ ህብር ያለው ሙዚቃ ፈጥሯል።

በምዕራብ አፍሪካ በስፋት የሚታወቀውን እና ኮራ የተሰኘውን የክር የሙዚቃ መሳሪያ፣ ከሀገረኛው መሰንቆ እና ከራያ የ“አሃ አሃ አሃ” እንጉርጉሮ ጋር በአንድ ሙዚቃ ላይ ጥቅም ላይ አውሏቸዋል።

የአውሮፓውያኑ አኮርዲዩን፣ ከአባውዴ እንጉርጉሮ እና መሰንቆ ጋር ተዋህዷል።

ኢዩኤል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አልበም ውስጥ ብዙም ያልተለመዱትን የሙዚቃ መሳሪያዎች ተጠቅሟል። ይህን ያደረገበት ቀዳሚው ምክንያት መሳሪያዎቹ በራሳቸው “ውብ ስለሆኑ ነው” ይላል።

“አንዳንዶቹ [የሙዚቃ መሳሪያዎች] ሊጠፉ የተቃረቡ የሚጫወታቸው ሰውም እየጠፋ ነው” የሚለው ኢዩኤል ሌላኛው ምክንያት፤ “ሊጠፋ የተቃረበውን ባህል ለመጠበቅ እና ኢትዮጵያ እና የዓለም ሙዚቃ መድረክ እንዲመጣ ለማድረግ” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

በደጋ ሰው አልበም ከመሰንቆ እና ዋሽንት በተጨማሪ እንደ ቶም፣ ዲታ እና ፊላ የመሳሰሉ ሌሎች ሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች ተካትተዋል።

የሙዚቃ አጥኚው ተስፋዬ ለማ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በሚል መጽሐፋቸው ቶምን፤ በአንኝዋክ፣ ኑዬር፣ መዠንገር ብሔረሰብ የታወቀና “ለዛ ያለው የሙዚቃ መሳርያ ነው” ይሉታል።

በቀድመው ጊዜ ቶም ከጠፍጣፋ እንጨት እና ሸንበቆ ነበር የሚሰራው፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ የሙዚቃ መሳሪያ ከእንጨት እና ከዣንጥላ ሽቦ እንደሚሰራ ተስፋዬ ለማ በመጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

ሌላኛው የሙዚቃ መሳሪያ የደራሼ ብሔረሰብ ፊላ ነው።

የአንድ ጎረምሳ ክንድ ርዝመት ያለው ፊላ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ ነው። ባለ አምስት ክሩ እና በወላይታ እና ጋሞ አካባቢ የሚታወቀው የክራር ዓይነት ቅርጽ ያለው ዲታም እንዲሁ በሙዚቃ አልበሙ ውስጥ ተካትቷል።

ኢዩኤል ሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎችን ከሌሎች ሀገራት ሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ያዋሃደበትን ምክንያት ሲያብራራ፤ “ገና ሙዚቃውን [መስራት] ስጀምር አዕምሮዬ ውስጥ የዘረዘርኳቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች አሉ። የኢትዮጵያን ሀገር በቀል ሙዚቃ ብቻ መጠቀም ስላልፈለግኩ contemporaries ማድረግ (ማዘመን)፤ ከሌላ ባህል ጋር ማዛመድ እፈልግ ነበር” ይላል።

የማርያም ቸርነት (የማ) እና ኢዩኤል መንግስቱ

የኢዩኤል እና የማ የሙዚቃ ጉዞ ከራማዳ ሆቴል እስከ የደጋ ሰው አልበም

የደጋ ሰው አልበምን ዕውን ያደረገው የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ የግጥም እና የዜማ ውህደት ብቻ አይደለም፤ የየማ እና ኢዩኤል የስድስት ዓመት ትውውቅም ጭምር ነው።

ኢዩኤል እና የማ የተዋወቁት ኢትዮኳርቴት የተሰኘው የኢዩኤል ባንድ በራማዳ ሆቴል በሚጫወትበት ወቅት ነው። በጊዜው ከኢዩኤል ጋር የምትጫወት ሙዚቀኛ ወደ ሌላ ሀገር መሄዷን ተከትሎ ነበር የማ ባንዱን የተቀላቀለችው። የማ በወቅቱ ትጫወት የነበረው ሸራተን አዲስ ሆቴል ኦፊስ ባር ነበር።

የማ እና ኢዩኤል ከልጅነታቸው ለሙዚቃ የተለየ ስሜት እና ፍቅር እንደነበራችው ይናገራሉ። ሁለቱም የሙዚቃ አድባር ስትጠራቸው ‘የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ’ አላሉም። ለሙዚቃ ጥሪ አቤት ቢሉም ጉዟቸው ግን ለየቅል ነበር።

የማ አባቷ አቶ ቸርነት ከበደ የዜማላስታስ ባንድ ሙዚቀኞችን ማኔጅ ያደረጉ ነበር። እነ ኤልያስ መልካ፣ ዳግማዊ አሊ፣ ዳንኤል ክንደያን የመሳሰሉ ሙዚቀኞች ሲለማመዱ እያየች ነው ያደገችው።

“እሱ ወደ ሙዚቃ እንድሳብ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል አላሳደረብኝም አላውቅም” የምትለው የማ ይህ የልጅነት ትውስታ ለአሁኑ የሙዚቃ ጉዞዋ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን መናገር እንደማትችል ትገልጻለች።

የትንሿ የማ ነፍስ ከሆሊውድ እና ቦሊውድ ፊልሞች ለሙዚቃ የቀረበ ነበር፤ “ከልጅነቴ ጀምሮ ሙዚቃ ማዳመጥ በጣም ነው የምወደው” ትላለች። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላ ባንዶች ጋር መጫዋት እንደጀመረች ታስታወሳለች።

የኢዩኤል የሙዚቃ ህይወት ደግሞ ወዲህ ነው። ኢዩኤል ወደ ሙዚቃ ፊቱን ከማዞሩ በፊት በሆርቲካልቸር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ጭኗል። የሀዋሳውን ዲግሪ ቤቱ አስቀምጦ ሌላ ዲግሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመዘገበ።

ይህን ውሳኔውን፤ “በህይወቴ ውስጥ ከወሰንኳቸው ከባድ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ነው” ይላል።

ቀድሞው እኔ የተፈጠረኩት ለሙዚቃ ነው የሚለው ኢዩኤል “ሙዚቃ በቤተሰብ ደግሞ ብዙ አይደገፍም ነበር። ስለዚህ ግዴታ መጀመሪያ ሳይንስ የሆነውን ነገር ማጥናት ስለነበረብኝ እዛ ሂጄ ተምሬያለሁ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኢዩኤል ያሬድ ሲገባ የሚያውቀው የሙዚቃ መሳሪያ ፒያኖ እና ኪቦርድን ነበር። ስለዚህ ፒያኖ አስተምሩኝ አለ። የያሬድ መምህራን ግን ‘አይሆንም፤ ትራምፔት ነው የምትማረው’ አሉ።

ትራምፔት ስድስት ወር ተማረ፤ የያኔው መምህሩ እነ አቶ አለማየሁ ገብረጻዲቅ ኢዩኤል የተዋጣለት የትራምፔት ተጫዋች እንደሚሆን እርግጠኛ ነበሩ። እርሱ ግን “እውነት ለመናገር ፍቅሩ አልነበረኝም ያንን ለማድረግ” አለ።

ከስድስት ወር በኋላም ከትራምፔት ወደ ደብል ቤዝ ቀየረ። በዚሁ የሙዚቃ መሳሪያ ሁለተኛ ዲግሪውን ጫነ። በተማረበት ያሬድ መምህር ሁኖ ቀረ።

ኢዩኤል የቅዱስ ያሬድ አድናቂ ነው። በሚያደንቀው ሙዚቀኛ ስም የሚጠራውን የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በዳይሬክተርነትም ይመራል። ኢትዮኳርቴት የተሰኘ ባንድ አቋቁሞም ነበር።

ኢዩኤል እና የማ በራማዳ ሆቴል በኢትዮኳርቴት ባንድ ስር ሙዚቃዎችን ተጫውተዋል። እዩኤል በእነዚህ የባንድ ሙዚቃ ክዋኔዎች እና ልምምዶች ላይ “የየማን ችሎት እያየሁ ሄድኩ” ይላል።

ኢዩኤል ለመጀመሪያ ጊዜ የማ ሙዚቃ ስትጫወት ከቀዳት በኋላ የነበረውን ሁኔታ አይረሳውም። የማ ማይክ ፊት ቁማ የጋሽ ግርማ በየነን “ወይዘሪት ኢትዮጵያ” ትዘፍናለች፤ ኢዩኤል ሌላ ክፍል ሆኖ ድምጿን ይቀዳል። ኢዩኤል “ድምጿን ቀድቼ ስሰማው በጣም ነው የደነገጥኩት የተለየ ስሜት ነው የተሰማኝ” ሲል ያስታውሳል።

ከስድስት ዓመት በፊት በአንዲት ቅዳሜ አመሻሽ፣ በአዲስ አበባው ራማዳ ሆቴል የተጀመረው ትውውቅ፣ በሁለት ነጠላ ሙዚቃዎች በኩል አልፎ፤ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የተቀረጸውን የደጋ ሰውን እውን አድርጓል።

ድምጻዊት የማ (የማርያም ቸርነት)

የማ፣ “ዳግማዊት ጂጂ”?

የደጋ ሰው አልበም ለአድማጮች ከመድረሱ በፊት ጀምሮ “እጅጋየሁ ሽባባውን (ጂጂ) የምትመስል ሙዚቀኛ መጣች?” የሚሉ አስተያየቶች ሲሰሙ ነበር።

የማ የራሷን የሙዚቃ ስራዎች ከማውጣቷ በፊት የጂጂን ስራዎች ዳግም አንጎራጉራቸዋለች።

አልበሙን ፕሮዲዩስ ያደረገው ኢዩኤል፣ የደጋ ሰው አልበም ሀገረ ሰባዊ ይዘት “ከጂጂ ጋር በጣም ያመሳስለዋል ግን አንድ ዓይነት አይደለም” ይላል።

የሙዚቃ አድማጮች የደጋ ሰው አልበምን ከጂጂ ስራዎች ጋር እንዲያመሳስሉት ያደረጋቸው፤ ጂጂ የምትጠቀማቸው የሀገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች በዚህኛው አልበም ላይ በስፋት መግባታቸው መሆኑን ይገልጻል።

ኢዩኤል አክሎም “እሷ [ጂጂ] ውስጥ ያለ የሙዚቃ መሳሪያ እኛ ውስጥ የሌለ አለ። እኛ ውስጥ ያለ እሷ ውስጥ የሌለ አለ” ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ የጂጂ ስራዎች እና የደጋ ሰው በአንድ አይነት ዘውግ መሰራታቸውም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ያነሳል።

“የማን፣ እንደ የማ እንድትታወቅ እፈልጋለሁ፤ እንደ ፕሮዲዩሰር እንደ ሙዚቀኛ ሰው እንዲያውቃት የምፈልገው እንደዛ ነው” የሚለው ኢዩኤል፤ “ግን ደግሞ ከጂጂ ጋር መነጻጸር በጣም ያኮራኛል። ደስ ይለኛል። ከሷ ጋር መነጻጸር ስለሚያስፈራኝ ነው እንጂ ደስ ይለኛል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።