
ከ 6 ሰአት በፊት
ኪም ጁ ኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ የታየችው በአውሮፓውያኑ 2022 ነበር።
ኪም ጁ ኤ አባቷን ለመተካት ትልቅ ተስፋ የተጣለባት እንደሆነች የደቡብ ኮሪያ የስለላ ኤጀንሲ ያምናል።
ለመሆኑ ስለዚህች ሴት ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
ኪም ስለቤተሰባቸው ጉዳይ ምሥጢረኛ ናቸው። ለዚህ ነው ስለልጃቸው ብዙም የማይታወቀው። ኪም ሌላውን የቤተሰቡን አባላት ይቅርና የገዛ ባለቤታቸውን ሪ ሶል ጁንን ደብቀው ነው የኖሩት። ከሠርግ በኋላ ለረዥም ዓመታት በአደባባይ ታይተው አያውቁም ነበር።
የደቡብ ኮሪያ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት የተጋቡት እንደ አውሮፓውያኑ 2009 ነበር፤ በ2010 ደግሞ ልጅ መውለዳቸው ተዘግቧል።
ምናልባት ሪ ሶል ጁን የዚህች ብዙ እየተባለላት ያለችው የኪም ሴት ልጅ እናት ሳትሆን አትቀርም። በትክክል ይቺ ልጅ የተወለደችበት ዘመን አይታወቅም።
የኪም ሴት ልጅ ጁ ኤ መፈጠሯ ራሱ የታወቀው በ2013 (እአአ) ነበር። አጋጣሚው ደግሞ የቀድሞው ዝነኛ የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ወደ ሰሜን ኮሪያ መሄዱን ተከትሎ ነው።
የቅርጫት ኳስ ኮከቡ ዴኒስ ሮድማን አነጋጋሪ የሆነ ጉዞ ወደ ሰሜን ኮሪያ አድርጎ ከተመለሰ በኋላ ስለቆይታው ሲናገር “ከኪም ቤተሰብ ጋር ቆንጆ ጊዜ አሳለፍኩ፤ በባሕሩ ዳርቻ ተዝናናን። ልጃቸውን ጁ ኤን አቀፍኳት” ማለቱን ተከትሎ ነው ኪም ሴት ልጅ እንዳላቸው መታወቅ የጀመረው።
የሰሜን ኮሪያ ሚዲያ ራሱ ‘የኪም ልጅ’ እያለ ነው የሚጠራት። ሙሉ ስሟን ጠርቶት አያውቅም። ዕድሜዋን አይጠቅስም።
- ኪም ጆንግ ኡንን የምትተካቸው ሴት ልጃቸው ልትሆን እንደምትችል ተጠቆመ5 ጥር 2024
- የሰሜን ኮሪያው ኪም ሴት ልጅ ለ5ኛ ጊዜ በአደባባይ መታየቷ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?12 የካቲት 2023
- ስሟን በሚዲያ ለመጥራት የምትፈራው የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ26 ጥር 2023

ፊዮዶር በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ላይ አጥኚ ሲሆን፣ በሴዑል ኩክሚን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው።
ስለ ኪም ጆን ሴት ልጅ ዕድሜ የሚያውቅ ባይኖርም አሁን 10 ዓመት እንደሞላት ይገመታል ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ የስለላ መሥሪያ ቤት እንደሚለው ይቺ ልጅ በየትኛውም ትምህርት ቤት አልተመዘገበችም።
ምናልባት በፒዮንግያንግ የግል መምህር ተመድቦላት ይሆናል ሲል ይገምታል።
የስለላ መሥሪያ ቤቱ እንደሚለው ልጂቱ ፈረስ መጋለብ፣ መዋኘት እና የበረዶ ሸርተቴ ትወዳለች። አባቷ ኪም በእርሷ የፈረስ መጋለብ ችሎት ደስተኛ እንደሆኑም የስለላ መሥሪያ ቤቱ ይናገራል።
ይህ የደቡብ ኮሪያ የስለላ መሥሪያ ቤት ይፋ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ ጄ ኤ ታላቅ ወንድም እንዳላት ነው። ሌላ አንድ እህት ወይም ወንድም ሳይኖራት እንደማይቀርም ፍንጭ ሰጥቷል።
አንዳቸውም ወንድም/እህቶቿ ለሕዝብ ታይተው ግን አያውቁም።
ጁ ኤ ለመጀመርያ ጊዜ ለሕዝብ የታየችው በ2022 (እአአ) አባቷ የሚሳኤል ሙከራ ለማየት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ነበር።
ከዚያ ወዲያ ግን በተደጋጋሚ ከአባቷ ጉያ ሥር ሸጎጥ ብላ ታይታለች።
በቅርቡ በዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ግንቦት-1 ስታዲየም በአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ላይ አባቷን ጉንጭ ስትስም በቴሌቪዥን የታየ ሲሆን፣ ትልቅ መነጋገሪያም ሆኗል።
ባለፈው ታኅሣሥ ደግሞ ተምዘግዛጊ አገር አቋራጭ ሚሳኤል ሲሞከር አብረው ነበሩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ማሊጊዮንግ-1 የተባለችው ሳተላይት ስትመጥቅ አብረው ሸኝተዋታል። ፒዮንግያንግ እንደምትለው ይህ ሳተላይት ለኪም ዋይት ሐውስን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳያቸው ይሆናል።

ባለፈው የካቲት 2023 ራዲዮ ፍሪ ኢዢያ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ስሙ ወይም ስሟ ጁን ኤ የሚባል ልጅ ካለ በአስቸኳይ ስማቸውን እንደያስቀይሩ የሚል መመሪያ መተላለፉን ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያን በቅርብ የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ ስምን የማስቀየሩ ተግባር አዲስ ነገር አይደለም።
የኪም ቤተሰብን ስም መያዝ በአገሪቱ ክልክል ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኪም ሴት ልጅ “እጅግ የተከበረችው” የሚል ተቀጽላ በስሟ ላይ እንዲጨመርላት ሆኗል። ከዚህ ቀደም ትጠራ የነበረው “ተወዳጇ የመሪያችን ልጅ’’ በሚል ነበር።
ይህ “እጅግ የተከበረችው” የሚለው ገለጻ በሰሜን ኮሪያ የመጨረሻው የክብር መገለጫ ነው።
አባቷ ኪምም ሲጠራ “እጅግ የተከበሩት ጓድ” በሚል ነው።
የፕሬዝዳንቱ ሴት ልጁ “እጅግ የተከበረች” በሚል እንድትጠራ መደረጉ ምናልባት ለትልቅ ሥልጣን ከወዲሁ እየተዘጋጀች ይሆናል የሚል ጥርጣሬን አጭሯል።
ሰሜን ኮሪያውያን መሪዎቻቸው ከተቀደሰ ደም (ዘር) የሚመዘዙ እንደሚሆኑ ይነገራቸዋል። ይህም ማለት አገሪቱን መምራት የሚችሉት እነርሱ ብቻ ናቸው።
ተንታኞች እንደሚሉት ኪም ሴት ልጃቸውን በዚህ ለጋ ዕድሜዋ ወደ አደባባይ ይዘዋት የሚወጡት በአጋጣሚ አይደለም።
ለሥልጣን እያለማመዷት ነው ብለው ያምናሉ።

በእርግጥ ይህ የመተካካቱ ጉዳይ በቅርብ ዓመታት የሚሆን ነገር ላይሆን ይችላል። ከዚህ ቀደም ኪም ከውፍረት ጋር በተያያዘ ጤናቸው አደጋ ላይ ወድቋል የሚለው ሐተታ ውድቅ ሆኗል።
ሌሎች ተንታኞች ደግሞ ሌላ ይላሉ። ኪም ከሴት ልጃቸው ጋር እየታዩ ያሉት አፍቃሪ እና ቤተሰባቸውን ወዳጅ መሪ ሆነው ለመታየት፤ ለሕዝቡም ምሳሌ ለመሆን ነው ይላሉ።
ቀደም ያሉት የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ማለትም ኪም ጆንግ ኢል እና ኪም ኢል ሱንግ አባታዊ ሥርዓትን አጥብቀው የሚከተሉ ነበሩ።
ምናልባት ከዚህ ባለፈ ኪም ይህን ጠጣር አባታዊ ባሕል ለመስበር እየሞከረ ይሆን? ብለው የሚጠረጥሩም አሉ።
ሰሜን ኮሪያ አገር ከሆነችበት ከአውሮፓውያኑ 1948 ጀምሮ በወንዶች ነው የተመራችው። ምናልባት ሴት ልጁ ከዚህ በኋላ አባቷን ብትተካ የመጀመሪያዋ የአገሪቱ ሴት መሪ ትሆናለች።
የኪም ሴት ልጅ መሪ ባትሆን ሌላ ለመሪነት የምትታጨውም ሴት ናት።
እሷም የኪም እህት የሆነችው እና ኃያልነቷ የሚነገርላት ኪም ዮ ጆንግ ናት።
ዮ ጆንግ አሁንም ቢሆን ቀላል ሥልጣን አይደለም ያላት። የአገሪቱ ገዢ የሠራተኞች ፓርቲ አባል ናት። ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ስሟ የተነሳው በኅዳር 2014 (እአአ) ነበር።
ጆን ኤ ከአክስቷ ዮ ጆንግ በጣም ያነሰ ዕድሜ ላይ ነው የምትገኘው። ዮ ጆንግ ሰፊ የፖለቲካ አመራር ልምድ አላት።
የሰሜን ኮሪያ ጉዳዮች ተንታኝ ፊዮዶር እንደሚሉት በዚህ ወቅት ኪም እያደረጉ ያሉት የሕዝብን ትርታ መለካት ነው።
“ኪም በአባቱ ዕድሜ ይሞታል ብለን ብንገምት ራሱ ያ የሚሆነው በ2054 (እአአ) ነው። ሰሜን ኮሪያ አሁን ባለው አገርነት እስከዚያ ዘመን ይጸናል ብለን ብናስብ እንኳ ማኅበረሰቡ አሁን ያለውን ዓይነት ማኅበረሰብ ይሆናል ተብሎ አይገመትም። በዚያ ላይ የፆታ እኩልነትን መቀበል እና ሴት መሪን መሪ አድርጎ መቀበል ሁለት የተለያዩ ነገሮቸ ናቸው” ይላሉ ተንታኙ ፊዮዶር።
ያም ሆነ ይህ የኪም ሴት ልጅ ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሆና ትቀጥል ይሆን ይሆናል።