ሰሜን ኮሪያ

ከ 5 ሰአት በፊት

አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን በጋራ ላካሄዱት ወታደራዊ ልምምዶች ምላሽ ለመስጠት በሚል ሰሜን ኮሪያ “የውሃ ውስጥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ” መሞከሯን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ሰሜን ኮሪያ ‘ሃኤል-5-23’ ስትል የሰየመችው ኒውክሌር መሸከም የሚችሉ የውሃ ውስጥ ድሮኖችን ሙከራ በምስራቃዊ የባሕር ዳርቻዋ አካሂዳለች።

ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሙከራዎችን አድርጋለች።

ሰሜን ኮሪያ በአካባቢው ላይ “በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ” ለሚችል ጦርነት ለመዘጋጀት ወታደራዊ አቅሟን እያጠናከረች መሆኑን ደጋግማ አስታውቃለች።

መሪዋ ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ሳምንት ከደቡብ ኮሪያ ጋር ዳግም የመዋሃድ ህልም ማብቃቱን ገልጸው ደቡብ ኮሪያንን “ቀንደኛዋ ጠላት” በማለት ፈርጀዋት ነበር።

የውሃ ውስጥን ጨምሮ የአገራቸው ወታደራዊ እና የኒውክሌር አቅሞች በርካታ እድገቶችን ማስመዝገባቸውንም ጠቁመዋል።

ፒዮንግያንግ ባለፈው መስከረም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማስወንጨፍ የሚችል የመጀመሪያው ሰርጓጅ መርከብ ነው ያለችውን መሣሪያ ይፋ አድርጋ ነበር።

ከ2023 ጀምሮም ሃኤል የሚል መጠሪያ የተሰጣቸውን እና ኒውክሌር የታጠቁት የውሃ ውስጥ የሰው አልባ ድሮኖችን መሞከሯን ተናግራለች።

ስለእነዚህ መሳሪያዎች ወይም ውጤታማነታቸው ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ከሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ባሊስቲክ ሚሳኤሎች አንጻር ሚናቸው አነስተኛ መሆኑን ተንታኞች ይገልጻሉ።

ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ወራት በርካታ የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን ሞክራለች።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የስለላ ሳተላይት ወደ ህዋ ላይ እንዳመጠቀች እና በዚህ ዓመትም ተጨማሪ እንደምታመጥቅ ይፋ አድርጋለች።

የመከላከያ ሚኒስቴሩ የውሃ ውስጥ ድሮን መሞከሯን ገልጾ የሙከራው ዓላማ “የአሜሪካ እና አጋሮቿን የባሕር ኃይሎች ጠብ የሚያጭር ወታደራዊ ልምምድን ለመከላከል ያለመ” ስለማለቱ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

ዋሽንግተን፣ ሴኡል እና ቶኪዮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችን ጨምር በማሰለፍ በኮሪያ ባሕር ገብ አካባቢ የሦስት ቀናት የጋራ ልምምድ አድርገው ነበር።