
19 ጥር 2024, 16:28 EAT
የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ጥቃትን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ አስወጥቶ የነበረው የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ ሠራተኞቹን ወደ አገሪቱ ሊመልስ መሆኑን አስታወቀ።
አህጉራዊው ባንክ በሠራተኞቹ ላይ የተፈጸመው ድብደባ እና እንግልት “የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት” መሆኑን ገልጾ፤ ታኅሣሥ 10/2016 ዓ.ም. ሠራተኞቹን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
ከዚህ ውሳኔው ከአንድ ወር በኋላ ባንኩ እንዳስታወቀው ውሳኔውን የቀለበሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተ ይቅርታ በመጠየቃቸው መሆኑን አመልክቷል።
አህጉራዊው የገንዘብ ተቋም ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለሱን ያስታወቀው ዛሬ አርብ ጥር 10/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
የአፍሪካ ልማት ባንክን ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን ከአዲስ አበባ የማስወጣት ውሳኔ ላይ ያደረሰው ከሦስት ወራት ገደማ በፊት ሁለት ሠራተኞቹ በኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች “ከሕግ ውጪ ታስረው አካላዊ ጥቃት” በመፈጸሙ ነበር።
ይህንን ጥቃት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ምርመራ አካሂዶ መረጃ እንዲያቀርብለት ጠይቆ የነበረው ባንኩ፤ ምንም አይነት ምላሽ አለማግኘቱን በወቅቱ አስታውቋል።
በዚህም ምክንያት መንግሥት የምርመራ ውጤቱን እና በጥፋተኛ አካላት ላይ የወሰደውን እርምጃ ለሕዝብ ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹ ከኢትዮጵያ ወጥተው በርቀት እንዲሠሩ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በውሳኔው መሠረት ሠራተኞቹ ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን አስታውሷል።
ከዚህ ውሳኔ በኋላ ግን ከታኅሣሥ 19 እስከ 21/2016 ዓ.ም. ባሉት ቀናት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንውሚ አዴሲና ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው እንደነበር በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጉዟቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው እንደነበር አመልክቶ “ስብሰባዎቹ ውጤታማ ነበሩ፤ ለጉዳዩም መፍትሄ አስገኝቷል” ሲል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክቷል።
የባንኩ መግለጫ እንደሚያስረዳው ከዶ/ር አኪንውሚ ጋር የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም በባንኩ ሠራተኞች ላይ ለደረሰው አካላዊ ጥቃት እና የዲፕሎማሲያዊ መብት ጥሰት “መደበኛ ይቅርታ” አቅርበዋል።
- የአፍሪካ ልማት ባንክ ሠራተኞቹ አዲስ አበባ ውስጥ እስር እና ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገለጸ16 ህዳር 2023
- የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት “አሉታዊ ተጽዕኖ” ሊገጥመው እንደሚችል ገለጸ20 ታህሳስ 2023
- ኢትዮጵያ የቦንድ ብድር ወለድ ያልከፈለችው በገንዘብ እጥረት አለመሆኑን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ15 ታህሳስ 2023
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በአስተናጋጇ ኢትዮጵያ ስምምነት መሠረት ባንኩን እና ሠራተኞቹ የሚኖራቸውን “ደኅንነት፣ የሠራተኞች መብት፣ ጥቅም እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ያለመከሰስ መብት” እንደሚከበር “ጠንካራ ማረጋገጫ” እንደሰጡ ባንኩ አስታውቋል።
“በተጨማሪም [የኢትዮጵያ] መንግሥት ባንኩ ላይ ያጋጠመውን ክስተት ለመመርመር እና የምርመራውን መደበኛ ሪፖርት ለባንኩ ለማጋራት እንዲሁም በሁሉም ተሳታፊዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል” ሲል ሁለቱ አካላት የደረሱበትን ስምምነት አስታውቋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ሠራተኞች በፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እንዲደርስባች ምክንያት የሆነው ክስተት ኢትዮጵያ ለባንኩ ከምታደርገው ዓመታዊ መዋጮ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የኬንያው “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። በኢትዮጵያ መንግሥት በባንኩ ስም በደረሰው የተጨበረበረ ኢሜል መሠረት ይህንን ገንዘብ ሜክሲኮ ውስጥ ወደሚገኝ የባንክ አካውንት ማስተላለፉን ዘገባው አመልክቶ ነበር።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ዓመታዊው መዋጮ እንዳልደረሰው ለኢትዮጵያ መንግሥት ካሳወቀ በኋላ የባንኩ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኃላፊ አብዱል ካማራ እና ሌላኛው የባንኩ ኃላፊ ጆን ቦስኮ ቡኬንያ ድብደባ እና እስር እንደደሰረባቸው ዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የጠፋ ገንዘብ ተመለከተም ለመመርመር መስማማቱን አስታውቋል። ባንኩ በመግለጫው “[የኢትዮጵያ] መንግሥት፤ ወደ ባንኩ መተላለፍ ሲኖርበት የጠፋውን ገንዘብ ጉዳይ በተመለከ ለሚደረግ ምርመራ ከባንኩ ጋር ለመተባበር ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል” ብሏል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እና የባንኩን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንውሚን ውይይት “ውጤታማ” ሲል የገለጸው ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል አስታውቋል። ከአገሪቱ ወጥተው የነበሩት የባንኩ ዓለም አቀፍ ሠራተኞችም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያለን አጋርነት ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዐላዊነት ጥረት ወሳኝ ነው” ሲሉ የባንኩ ድጋፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልዕክታቸው ከባንኩ ጋር ተፈጥሮ ስለነበረው ችግርም ሆነ ባንኩ አሁን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን መደበኛ ግንኙነት ለመቀጠል ስለመወሰኑ ያሉት ነገር የለም።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ በትግበራ ላይ ያሉ 22 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ የ1.24 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው ናቸው።
ባንኩ ባለፈው ወር ባወጣው መግለጫ ሠራተኞቹን ለእስር እና ጥቃት የዳረገው ክስተት “ሙሉ በሙሉ” የማይፈታ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ላይ “አሉታዊ” ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።