የከተራ ሥነ ሥርዓት

19 ጥር 2024, 15:39 EAT

ከጥምቀት በዓል ቀደም ብሎ የሚካሄደው የከተራ ሥነ ሥርዓት በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ተከናወነ።

በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ የከተራ በዓል ከወትሮው ቀዝቀዝ ቢልም ታቦታት በቀሳውስት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባሕር አምርተዋል።

የከተራ እና የጥምቀት በዓል በተለየ ሁኔታ በድምቀት የሚከበርባት የጎንደር ከተማ በክልሉ ውስጥ ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ የዘንድሮው የከተራ በዓል አከባበር ከዚህ ቀደሞቹ ቀዝቀዝ ያለ እንደሆነ ነዋሪዎች በሥፍራው ለሚገኝ የቢቢሲ ዘጋቢ ተናግረዋል።

የከተማዋ አስተዳደር በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ሲገልፅ የፀጥታ አባላት በከተማዋ ሲዘዋወሩ ታይተዋል።

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር ነው።

የጥምቀት በዓልን ለመታደም ቱሪስቶችኝ ጨምሮ በርካቶች ወደ ጎንደር ይጓዛሉ።

በጥምቀት ቀን ምዕመናን በታሪካዊው ፋሲለ-ደስ ግቢ በሚገኘው ገንዳ ተሰባስበው ይጠመቃሉ።

ጎንደር

የጎንደር ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አበበ ላቀው “ዝግጅታችንን ጨርሰናል። እስካሁን ሁሉም በሥርዓት እየሄደ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት እንደወትሮው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች እያዜሙ ታቦታትን አጅበው ሲሄዱ አልታዩም።

የጥምቀት በዓል ከአገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ ጎብኚዎችን የሚስብ ሥነ ሥርዓት ቢሆንም፣ የዘንድሮው የቱሪስቶች ቁጥር ከዚህ ቀደሙ አነስ ያነ እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ጎንደር
የምስሉ መግለጫ,የከተራ እና የጥቅምቀት በዓል ሥነ ሥርዓት የሚከናወንበት የፋሲል ደስ ቤተ-መንግሥት

ጎንደር በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተገነቡ ቤተ-መንግሥት መናገሻ ናት። ቤተ-መንግሥቱ እና የጥምቀት በዓል አከባበር የዓለም የማይደስሱ ባሕላዊ ቅርሶች ተብለው በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግበዋል።

የጥምቀት በዓል በጎንደር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሥፍራዎች በወርሃ ጥር በተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ሃይማኖታዊ በዓል ነው።

ታቦታትን በማጀብ ወደ ማደሪያቸው የሚሸኙ ቀሳውስት በጎንደር
የምስሉ መግለጫ,ታቦታትን በማጀብ ወደ ማደሪያቸው የሚሸኙ ቀሳውስት በጎንደር

የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 10 ተጀምሮ ጥር 11 የሚከበር ሲሆን ጥር 12 ደግሞ የቃና ዘገሊላ በዓል በድምቀት ይከበራል።

ጥምቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ እና ጎንደር ይገኙበታል።

በከተራ በዓል ሥነ ሥርዓት የጎንደር ነዋሪዎች
የምስሉ መግለጫ,በከተራ በዓል ሥነ ሥርዓት የጎንደር ነዋሪዎች
የጥምቀት በዓል ከአገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ ጎብኚዎችን የሚስብ ሥነ ሥርዓት
የምስሉ መግለጫ,የጥምቀት በዓል ከአገር ውስጥ እና ከውጪ በርካታ ጎብኚዎችን የሚስብ ሥነ ሥርዓት