
20 ጥር 2024
የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ሴኔጋል ትናንት ምሽት በነበረ ጨዋታ ካሜሮንን አሸንፋ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፏን አረጋገጠች።
በመክፈቻ ጨዋታዋ አቻ፤ ትናንት ደግሞ በሴኔጋል የተሸነፈችው ካሜሮን የጥሎ ማለፍ የማለፏ ዕድል በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ የሚመሰረት ይሆናል።
ትናንት በነበረው ጨዋታ የሴኔጋሉ እስማኤል ሳር የመክፈቻ ጎሉን ሲያስቆጥር፤ ሃቢብ ዲአሎ ደግሞ ሁለተኛዋን ግብ ለሴኔጋል አስመዝግቦ ነበር።
ይሁን እንጂ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ጄን-ቻርልስ ካስቴሌቶ ግሩም ግብ በጭንቅላቱ ለካሜሮን ሲያስቆጥር የማይበገሩት አንበሶች ከጨዋታው ነጥብ የሚያገኙ መስሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ሳዲዮ ማኔ የሴኔጋልን ድል አድራጊነት ያረጋገጠች ጎል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አስቆጥሮ ጨዋታው 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በዚህ መሠረት ሴኔጋል 6 ነጥብ ይዛ አንድ ጨዋታ እየቀራት ከምድብ ሲ ማለፏን ያረጋገጠች ቡድን ሆናለች።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ጊኒ እና ዘ ጋምቢያ ባደረጉት ጨዋታ ጊኒ 1 ለ 0 ማሸነፍ ችላለች። በመክፈቻ ጨዋታ ከካሜሮን ጋር 1 አቻ ተለያይታ የነበረችው ጊኒ የትናንት ምሽቱ ሦስት ነጥብ ተደምሮላት በ4 ነጥብ ከሴኔጋል ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ጊኒ በቀጣይ ከሴኔጋል የምትገናኝ ከሆነ ጨዋታውን በአቻ ውጤት መጨረስ ማለፏን ያረጋግጣል።
- የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ከ12ተኛ ክፍል ፈተናዎች መካከል እንዲወጣ ተደረገ20 ጥር 2024
- “ዓላማዬ የኢትዮጵያ የሀገረ-ሰብ ሙዚቃ መሳሪያዎችን ማጉላት ነው”- አስቻለው ፈጠነ20 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ የተነሱ ውዝግቦች20 ጥር 2024
አምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሱት ካሜሮን ደግሞ ከሁለት ጨዋታ 1 ነጥብ ብቻ መያዛቸው ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ የሌሎች ጨዋታዎች ውጤትን መጠበቅ አልያም ምርጥ ሦስተኛ ሆኖ የማለፍ አማራጭ ነው ያላቸው።
በቀጣይ ጨዋታ ካሜሮን ከምድቡ ለማለፍ ያላት አንድ አማራጭ ዘ ጋምቢያን አሸንፋ፤ ጊኒ ደግሞ በሴኔጋል ተሸንፋ እንዲሁም ካሜሮን በግብ ክፍያ ወይም ባስቆጠረችው የጎል ብዛት ከጊኒ ተሽላ መገኘት አለባት።
በዚህ ሁኔታ ካሜሮን ከጊኒ በልጣ የማትገኝ ከሆነ ምርጥ ሦስተኛ ተብለው ከሚመረጡት አራት ቡድኖች አንደኛዋ መሆን ይጠበቅባታል።
ውድድሩ ቀጥሎ ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። አልጄሪያ ከ ቡርኪና ፋሶ ተጠባቂው ጨዋታ ሲሆን 11 ሰዓት ሲል ይጀምራል።
ሞሪታኒያ ከ አንጎላ እንዲሁም ቱኒዚያ ከ ማሊ ዛሬ ምሽት 2 እና 5 ሰዓት የሚደጉ ጨዋታዎች ናቸው።