ጋዛ

20 ጥር 2024, 08:51 EAT

እስራኤል በኻህን ዩኑስ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራለች።

በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን በፍርሃት ተውጠዋል።

ከሰሞኑ ጥቃት የተባባሰው በደቡባዊ አካባቢ ነው።

ናስር ሆስፒታል አካባቢ ተጠልለው የነበሩ ተፈናቃዮች በድጋሚ ለመፈናቀል ተገደዋል።

ይህ ሆስፒታል በአካባቢው አገልግሎት እየሰጠ ያለ ትልቁ ሆስፒታል ነው።

እስካሁን በእስራኤል ጥቃት 24,000 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 2.3 ሚሊዮን ተፈናቅለዋል። ምግብና ውሃ እንዲሁም መድኃኒትም ለማግኘት በየቀኑ ይንገላታሉ።

ሞሐመድ አል-ካልዲ የሁለት ልጆች አባት ነው። ከጋዛ ቤቱ ተፈናቅሏል።

“ቤቴን አጣሁ። ሱቄንና ገቢዬን አጣሁ። ልጆቼ የሚፈልጉትን ማሟላት ተሳነኝ” ይላል።

“ለዚህ ትልቅ ቀውስ ተጠያቂ የማደርገው እስራኤልን ነው። ሐማስ በተፈጠረው እጁ የለም ግን አልልም” ሲልም ያክላል።

በየሁለት ወይም ሦስት ዓመቱ ወደጦርነት መመለስ አስከፊ እንደሆነ ሞሐመድ ይናገራል።

“ሁኔታው ከጦርነቱ በፊትም የከፋ ነበር። አሁን ተባብሷል” ሲል ይገልጻል።

መሠረታዊ ቁሳቁሶች ዋጋቸው እንደናረ ይናገራል። እነዚህን ማግኘትም አይቻልም።

“ልጆቼን ሳያቸውና ምግብ ልሰጣቸው እንደማልችል ሳስብ በየቀኑ ሺህ ጊዜ መሞትን እመርጣለሁ” ይላል ሞሐመድ።

በካሃን ዩኑስ ያሉ ነዋሪዎች የእስራኤል ጥቃት ወደማዕከላዊው አካባቢ እየተስፋፋ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከጋዛ ቤቱ የተፈናቀለው ናጂ ማሕሙድ እንደሚለው እስራኤል ጥቃት እየፈጸመች ያለው ከመሬት ውስጥ ለውስጥ ስለሆነ “መሬቱ እየከዳቸው እንደሆነ” ይሰማቸዋል።

ከደቡባዊ ጋዛ ወደ ካሃን ዩኑስ የተጓዘው አንድ ሳምንት በቆየው ተኩስ አቁም ነው።

“የመሬት መንቀጥቀት ነው የሚመስለው። በየምሽቱ ነው ጥቃቱ የሚፈጸመው። ቦምብ መተላለፊያ ዋሻዎችን ዒላማ አድርጎ ይጣላል” ይላል።

ጋዛ ሳሉ አብዛኛውን ጊዜ የአየር ጥቃት ይፈጸም እንደነበር ይናገራል።

በጋዛ ዝርፊያ እየተከበራከተ መምጣቱንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

አንድ ቢቢሲ ያነጋገረው ጋዜጠኛ እንዳለው በራፋ ከሥራ ሲመለስ ጭምብል ያደረጉ ሰዎች ስለትና ሽጉጥ ይዘው አስቁመውት ሊዘርፉ ሞክረዋል።

“መኪና ውስጥ ጠቃሚ ነገር ካለ ፈተሹ። አንደኛው ጋዜጠኛ እንደሆንኩኝ አስተዋለና እንድሄድ ፈቀዱልኝ” ብሏል።

በራፋ ጎዳና ያሉ ፖሊሶች የቁሳቁስ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን በአግባቡ እየተቆጣጠሩ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ያማርራሉ።

መሐመድ ሼክ ካሊል የተባለነው ነዋሪ “ስንዴ በ100 ዶላር ገዛሁ። ይሄም ከዋጋው አስር እጥፍ ነው” ብሏል።

“በጦርነቱ የሚነግዱትን ለምን ፖሊሶች አያስሯቸውም? ከተባበሩት መንግሥታት የተሰጠ ስንዴ ነው ሰርቀው የሚሸጡት” ሲልም አክሏል።

“ለልጄ ወተት ማግኘት አልቻልኩም። ልጄ ኦቲዝም አለበት። ለወራት ሕክምና አላገኘም። ላረጋጋው አልቻልኩም። ከጦርነቱ በኋላ የጤናው ነገር ተባብሷል” ሲል ለቢቢሲ ያለበትን ሁኔታ ገልጿል።

ሐማስ ከዚህ ቀደም በአስቸኳይ የአደጋ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሠራነት መንገድ ቢኖርም አሁን ይህን ማድረግ አልተቻለም።

የእስራኤል ጥቃት የመንግሥት መዋቅርን አፍርሷል። ፖሊሶችና የፀጥታ ባልደረቦች በከፍተኛ ቁጥርም ተገድለዋል። ፖሊስ ጣቢያዎችም ወድመዋል።

ኔቫን ኢማደዲን እናት ናት። ጋዛ ካለ ቤቷ ተፈናቅላለች። አሁን በራፋ ነው የምትኖረው።

“ጦርነቱ እንዲቆም እንፈልጋለን። ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል። አገራችን ሰላምም ጦርነትም ወደሌለበት ሁኔታ ቢመለስ እንመርጣለን” ትላለች።

“እስኪ የደረሰብንን ተመልከቱ። ሌቦች ከቤቴ ሁሉንም ነገር ዘረፉ። ልብስ፣ የቤት እቃም ሳይቀር” ስትል ኔቫን ትናገራለች።

አሁን ተፈናቅለው ራፋ ይኖራሉ። ከዚያ በፊት ካሃን ዩኑስ ነበሩ።

“ገንዘብ የለንም። ቤት የለንም። ማቆሚያ ያጣው የሐማስና እስራኤል ጦርነት ሕይወታችንን አመሳቀለው” ትላለች።

መሐመድ የተባለ ነጋዴ “ከ16 ዓመታት በላይ ፍትሕ አጥተን ኖረናል። ሐማስ ከፍተኛ ቀረጥ ነው የሚጥልብን። አሁን ደግሞ ጦርነት ውስጥ ገባን። ንብረታችንን፣ ቤታችንን፣ ገንዘባችንን አጣን” ሲል ያሉበትን ገልጿል።

“ጥሩ ቤት ነበረኝ። እነግድ ነበር። አሁን ምን ቀረኝ? ሁሉም ነገር ተዘጋግቷል” ይላል መሐመድ።