አስቻለው ፈጠነ ክራር እየተጫወተ

20 ጥር 2024

ክራርን ይቃኛል። አባቱ፣ ወንድሞቹ እና አጎቱም ክራር ተጫዋች ናቸው።

እሱም ቢሆን የእጅ ጣቶቹን ከክራሩ ላይ ማንሳት አይፈልግም።

አስቻለው የክራር አድናቂ ነው ብቻ ሳይሆን ብዙ ክራሮችም አሉት። እርሱም “ክራሮቼን በጣም እወዳቸዋለሁ” ይላል።

ሳባ፣ ጃኖ፣ ኡምባላ፣ አራዳ እያለም ስም አውጥቶላቸዋል።

ውልደቱ እና እድገቱ ቻግኒ ነው።

‘እናትዋ ጎንደር’ እና ‘ካሲናው ጎጃም’ በሚሉ ዜማዎቹ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ችሏል።

ራሱን “ከያኒው” ሲል ይገልጻል።

ከሰሞኑን 14 ሙዚቃዎችን የያዘ “አስቻለ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ ጆሮ አብቅቷል።

ግጥሞቹ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ይዘት አላቸው።

የተለያዩ ድምጾችን ቀላቅሎ አዲስ ድምጽ እንካችሁ ብሏል።

በሙዚቃዎቹ ውስጥ መንዙማ ይሰማል። አረብኛው እና ግዕዙ ይደመጣል። ባስኬቶው ይንቆረቆራል።

ፈረሶችም በአድዋ ሙዚቃው ውስጥ አብረውት ያዜማሉ።

ከአባይ ቁጭት እስከ ወሎ ፍቅር እና ታሪክ፤ ከሸዋ እስከ በላይ. . .ሰልካካዋ ልጅ እና ሌሎችም በሥራዎቹ ውስጥ ተነስተዋል።

የቀድሞው የግብርና ባለሞያ “በአጋጣሚ” ወደ ሙዚቃ እንደገባ ይናገራል።

እነ ባሕሩ ቃኜ ልቡን ሰርቀውታል። ግን በቁጥጥር ስር አላዋሉትም።

የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃም ወዳጅ ነው።

በአልበሙ የተለያዩ አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያዎች ከዘመናዊ መሳሪያዎች ጋር ተጣምረዋል።

አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ጉምዝኛ፣ አረብኛ እና ሌሎችም ቋንቋዎች ተሰባጥረውበታል።

ሙዚቃ “በብዙ ሕግ እንዲታጠር አልፈልግም” በማለት፤ አዲስ ድምጽ ለመፍጠር ስለመሞከሩ ይናገራል።

ከያኒው አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህሎች አዋህዶ “አዲስ አገር ለመፍጠር እየዳዳሁ ነኝ” ይላል።

ለኮራ አዋርድም ታጭቷል።

ቻግኒ መወለድ እና በአምስት ቋንቋዎች ማዜም

አስቻለው ፈጠነ፣ በቅጽል ስሙ አርዲ ቻግኒ መድኃኒያለም ሰፈር ነው የተወለደው።

አስቻለው ሙዚቃ ከልጅነቱ ጀምሮ አብራው አለች።

“አባቴ፣ አጎቴ፣ ወንድሞቼ ሁሉ ክራር ይሞካክሩ ነበር” ይላል።

የሰፈሩን ሰዎች ከማዝናናት ውጪ ወደ ሙዚቃ ሙያ እገባለሁ የሚል ግምት ግን አልነበረውም።

ግን ሙዚቃ እህል ውሃው ሳትሆን አትቀርም።

“አጋጣሚዎች የሚፈጥሩት ነገር አለ አይደል? በ2002 ዓ.ም. ቻግኒ ውስጥ የፖለቲካ ነገር ተከሰተና ትንሽ ደበቅ ብዬ ወልዲያ ቆየሁ። ከወልዲያ ተነስቼ አዲስ አበባ ቲያትር ቤት [ማዘጋጃ] ስሞክር አለፍኩ። ቲያትር ቤት አሠለጠኑኝ፤ ብዙ እውቀቶችን ሰጡኝ። ነገሮች ተመቻቹልኝ፤ አንዳንድ ስል እዚህ ደረስኩ” በማለት የሙዚቃ ጉዞውን ጅማሮ ያወሳል።

አስቻለው ልዩ ተጽዕኖ ፈጠረብኝ የሚለው ባለሙያ ባይኖርም የሚሰማቸው ሙዚቃዎች ግን ዕይታውንም ጆሮውንም የቃኙ ስለመሆናቸው ያነሳል።

እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) “የሠፈራችን ልጅ ናት” የሚለው አስቻለው፤ የድምጻዊቷ እውቅና እና የሙዚቃ ሥራዎቿ ወደ ሙዚቃ የመጀመሪያው በር ከፋች ነው።

“ተወልጄ ባደግሁበት አካባቢ የአያ ሽባባው ልጅ ዘፋኝ ናት ሲባል፣ የራሱ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሁለተኛ የእሷም የሙዚቃ አሠራር ሌላ ነው” ይላል።

በጂጂ ሳያበቃ ክራር ገራፊዎቹ ባሕሩ ቃኜ፣ ሜሪ አርምዴ እና ካሳ ተሰማ በልቡ አደሩ። የባሕሩ ቃኜ ግን ይለያል።

“ጋሽ ባሕሩ ቃኜ አያቴ ነው የሚመስሉኝ። እሳቸውን በጣም እሰማለሁ፤ ደስ ይሉኛል በቃ” ሲል ቃል ያጥረዋል።

ከአገር ተሻግሮ፤ ባሕር አቋርጦ የምዕራብ አፍሪካ ሙዚቃም አድናቂ ነው። በተለይ ግን የማሊን ሙዚቃ ይወዳል።

ለዚህም ነው ራሱን “በዚህ መሀል ነኝ” ሲል የሙዚቃ ተጽዕኖ ሰፋ ያለ እንደሆነ የሚናገረው።

ቻግኒ መወለዱ ደግሞ ትልቅ ዕድልም ሆኖለታል።

አስቻለ ሲል ስያሜ የሰጠው የመጀመሪያ አልበሙ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ግጥሞችን ከመሰነዱ በተጨማሪ ከሰባት በላይ ቋንቋዎች ይዜሙበታል።

አስቻለው የቻግኒ ብዝኃነት ያለው ማኅበረሰብ ባህል እና ቋንቋ ጆሮውን እንዲከፍት እንዳደረገው ይናገራል።

“ቻግኒ ላይ ተወልዶ ሲታደግ፤ አማርኛ፣ አገውኛ፣ ጉምዝኛ፣ ሽናሻኛ፣ ኦሮምኛ፣ ከምባትኛ፣ ሃድይኛ አለ። በተለይ አማርኛ፣ አገውኛ፣ ጉምዝኛ እና ሽናሽኛ ስብጥሩ አለ። ሙዚቃዎቹን ታቦታት ሲወጡ በስፋት ይሰማሉ” ይላል።

የአስቻለው አዲስ የሙዚቃ ሰንዱቅ ማስተዋወቅያ ምስል

ችላ የተባሉትን የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ማንሳት

አስቻለው እና የአልበሙ ተሳታፊ ባለሙያዎች “የኢትዮጵያ የባህል የሙዚቃ መሳሪያዎች” በሚለው መግለጫ አይስማሙም።

ለዚህም ምክንያታቸው ‘አገር በቀል መሳሪያዎችን ወደ ጎን አሽቀንጥረን ዘመናዊ በሚል የተቀበልናቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች የኛ አይደሉም’ የሚል ነው።

የአስቻለ አልበም ሂደትም እነዚህ አገርኛ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ሂደቱ ከሰሜን፣ ከምዕራብ እና ከደቡብ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በማሰባሰብ ሀ ብሎ ስለመጀመሩ ድምጻዊው ያነሳል።

“የኢትዮጵያን የባህል መሳሪያን እና የባህል ሙዚቃዎችን በሚገባ መጠን ሰርተን፤ የሆነ ቦታ ለማድረስ ነበር የጀመርነው” ይላል።

“በመጀመሪያ እቃዎችን ሰበሰብን። ለምሳሌ ትልልቅ ከበሮዎችን እኔ ከተወለድኩበት አካባቢ የጉሙዝ ማኅበረሰብ ‘እንዲህና’ የሚባል ከበሮ አለ። ወደ 50፤ 60 ኪሎ ከሚመዝን ከአንድ ትልቅ ዛፍ የሚፈለፈል ነው። ትንሽዬዋ ደግሞ ለተዝካር መጥሪያ የሚጠቀሙባት ‘ፊሪማ’ የምትባል ከበሮ አለች። እኔ ክራሮችን በትልቅ ቅሎች ነው የማሠራው፤ እነሱ እነሱን እየሰራን ነው ሪከርድ ማድረግ ጀመርነው።

“እምቢልታን ትግራይ አካባቢ ነው በብዛት የሚጠቀሙበት። ዙምባራ ደግሞ ቤንሻንጉል፤ ቶሜ ደግሞ የጋምቤላ፤ ከደቡብም የተለያዩ መሳሪያዎችን መሰብሰበ ጀመርን።”

ከዚህ በኋላ ቡርቧክስ የተሰኘ ባንድ ድረስ መሥርተው የአስቻለን ሥራዎች መቅረጽ እስኪጀምሩ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል።

ልፋታቸው መና አለመቅረቱንም ሲያስረዳ “ግን ንጹህ የሆነ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወጥቶ፣ ሰውም ከሚገባው በላይ ደስታ ሰጥቶናል” በማለት ነው።

የአገሪቱ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች እና ቴአትር ቤቶች የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሳሪያዎች ችላ ብለዋል ሲል የሚወቅሰው አስቻለው፤ ሁኔታውንም “አሳዛኝ” ሲል ይገልጸዋል።

“እንደ እኔ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ የሚገባውን ቦታ አግኝቷል ብዬ አላምንም። ለምሳሌ ድርድር ክራር ጠፍቷል ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ናት ጠብቃ፤ በመዝሙሮች ላይ ይሰማል።

“ወደ ሙዚቃው ሲመጣ ግን ድርድሩን ጋሽ ካሳ ተሰማ፣ እነ ሜሪ አርምዴ፣ እነ አስናቀች ወርቁ እና የተወሰኑ ሰዎች፤ እኔ እንኳ ምንም አላውቅም። ያለቀ፤ ጭላጭ ነገር ነው የደረሰን” ይላል።

አስቻለው “የኛ ዓለማ የኢትዮጵያ የሙዚቃ መሳሪያ ትልቅ ቦታ መድረስ እንዲችል ነው” ይላል።

“ግጥሞቹ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ይሄ ተጨማሪ ነው። ግን ዋናው መነሻ የኢትዮጵያን የሙዚቃ መሳሪያዎች ካሉበት አምጥተን አጣምረን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።”

ታሪክ ወዳዱ አስቻለው

አስቻለው – በእመት ሸዋ ሙዚቃው ከእንጦጦ ተነስቶ በእምዬ ተመርቶ፤

ሸዋ አገር አቀና ድንበር ካርታ ሰርቶ፤

ሲል በእንገር ወሎ ደግሞ፡

አገር ክተት ብለው አዋጅ ሲማማሉ፤

ከቶ ከቶ አደረ ጃማ ወረኢሉ፤

የራስ አሊ ሀገር የሴሩ ጓንጉል፤

ይሾማል ይቀባል አቡን ይመስል፤ እያለ ያዜማል።

ከአስቻለው ሙዚቃዎች ውስጥ ይነቀስ ቢባል ታሪክ አንዱ ነው። ለዚህ ደግሞ “ጎበዝ የታሪክ ተማሪ መሆኑ” ትልቅ ስፍራ አለው።

“የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። [ተማሪዎች] በሌላው [ትምህርት ዓይነት] ሊበልጡኝ ይችላሉ። በታሪክ ግን በጣም ጎበዝ ነበርኩ። አገር አቀፍ የመልቀቂያ ፈተናን 3.8 ነው ያመጣሁት። ታሪክ በጣም ነው የምወደው። ይሄ [ለሙዚቃዬ] ጠቅሞኛል” ሲል ስለ ግጥሞችን ታሪካዊ ይዘት ያነሳል።

ግን ከዚህም ያልፋል። የግብርና ባለሞያ ሆኖ ሲሰራ ታሪክ ብቻም ሳይሆን ባህልን ለመኖር፤ ለመውደድ ቻለ። ከአገው እና ከጉሙዝ ባህሎች ባለፈ በወሎ ባህል ስለመመሰጡ ይናገራል።

“ወሎዬ እስክመስል ድረስ” አወኩት ሲልም በወልዲያ ቆይታው ወቅት ባህሉን ማወቁን ጠቅሶ፤ ሸዋ ስለመዝለቁም ይናገራል።

“ቅድሚያ ማወቅ” ሲልም ያላየውን፣ ያላጠናውን፣ ያላወቀውን፣ ያልተረዳውን እንደማይጽፍ ይናገራል።

“ወሎ ስሠራ ወልዲያ፣ አዳጎ፣ ፒያሳ፣ መቻሬ ሜዳ፣ ጎንደር በር በጣም ትዝ ይሉኛል፤ ደሴ ስመጣ አይጠየፍ አዳራሽ ዲሙ ነው ድባቡ። ጥምቀት ያከበርነው ቆቦ፤ ገምሻራዎች የሚገማሸሩበት እና ሌሎችም ይታሰባሉ። ታሪክ ተማሪ ነኝ ደግሞ፤ እነ ልጅ የእያሱ፣ የእነ ራስ አሊ፣ የጁ . . . በጣም ይመጣብኛል። እና በፊት እና በኋላ አጠናና፤ ቦታዎቹንም ድጋሚ አገላብጥና ስሠራው በጣም ጥሩ ይሆናል ማለት ነው” በማለት የግጥም አጻጻፍ ሂደቱን እና ታሪካዊነቱን ይገልጻል።

ከአባ ሃጂ የመንዙማ ተጽዕኖ ጀምሮ

“ከመቃብር በላይ ስም ይቀራል ብሎ

ፍቅር እና ጀግንነት ያውቅበታል ወሎ

ወሎ ልበ ሰፊ መተኛ ደንኳን

አበጋር ይፈራል እንኳን አምላኩን” ሲል በመንዙማ ሙዚቃውን ጀምሮ ይቃኛል።

መንዙማን ምንአልባትም ከሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ውጪ ዓለማዊ ሙዚቃዎች መስማት እንግዳ ነው።

አስቻለው ለመንዙማ ልቡን የከፈተው ቻግኒ የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ከአባ ሃጂ ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ በወሎ ቆይታው ዳግም መንዙማን አገኘ።

“መንዙማ በጣም እወዳለሁ። መንዙማ ብዙም ዘፈኖች ላይ አይነሳምና በዚህ ተጽዕኖ ይመስለኛል መንዙማን ያስገባሁት።”

አስቻለው ከዚህ በተጨማሪ ቋንቋዎችን ብቻም ሳይሆን ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ከተለያዩ አካባቢዎች የአዘፋፈን ዘዴ እና ቅላጼ ጋር አዋህዷል። እንደ አካባቢው ዘየ የአስቻለው የድምጽ ሬንጅ ከፍ እና ዝቅ ይላል።

“በጣም ትንሽዬ ክራር አለኝ፤ በገና የሚያካክል ክራርም አለኝ። በትንሹ ሬንጅ ስጫወት፣ በመሀለኛው ስጫወት፣ በትልቁ ደግሞ ስጫወት ድምጼ በዚህ ሂደት ውስጥ ይቀያየራል” ይላል።

በተጨማሪም አንጎራጓሪውም ተቀባዩም አስቻለው ነው። የአልበሙ አዘጋጆች ‘የሴት ድምጽ ስትሰሙ እንዳትደነግጡ’ ሲሉም ሁሉም ድምጾች (ከአንድ ሴት በስተቀር) የአስቻለው ናቸው ብለዋል።

“ከጎጃም እና ከሸዋው ውጪ ያሉ ኳየረችን [ተቀባይ] እኔ ነኝ የሠራሁት። በቀጭን ድምጽ፣ በመካከለኛ፣ በሴት ዓይነት ድምጽ በሌላ ድምጽ አድርጌ ኳየሩን ስሠራው በጣም አሪፍ ይሆናል። ይሄ በተለያየ የሙዚቃ መሳሪያዎች መጫወት፤ የሌሎች አገራትን ልምድ ማየት ይመስለኛል” ሲልም ተጽዕኖውን ያነሳል።

በሙዚቃዎቹ ላይ የሚጠሩ እንደ ወ/ሮ ተሰሩ፣ ደገኛው ጀንበር . . . ያሉ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች ምናባዊ ወይስ እውነተኛ ሰዎች ናቸው?

ይህን አስቻለው ለአድማጩ የቤት ሥራ ትቷል።

“በክራሩ ላይ እንደምመራመረው ግጥሙም ዜማውም ላይ መመራመር አለብኝ ብዬ አምናለሁ። ሰው በየራሱ ይተርጉመው። ሙዚቃን እንዲህ ነው ብል የአድማጭን አስተያየት፤ ምልከታ መገደብ ነው ብዬ አምናለሁ” ይላል።

አስቻለው ፈጠነ

ከያኒው አስቻለው

እራሱን “ከያኒው” ብሎ የሚጠራው አስቻለው “ጥሩ ሥራዎችን ሠርቶ ወደ ሕዝቡ ለመውጣት ተፍ ተፍ የሚል ጀማሪ አርቲስት፤ ከያኒ ነው” ሲል ራሱን ይገልጻል።

ከአራት አምስት ዓመታት በፊት በጉምዝኛ እና በአገውኛ ሙዚቃዎችን ሠርቷል። ግን እምብዛም እውቅና አላገኘም። ለዚህም አስቻለው ጊዜ እና ሂደትን እንደምክንያት ያነሳል። አንድ ሳይባል 20፤ 30 አይባልም ሲል ጉዞው ለትጋት መንገድ እንደጠረገለት ይናገራል።

“ሁሉም ነገር ሂደት ነው። ከቻግኒ ከሰፈሬ ተነሳሁ፤ የሰፈሬን ሰዎች በሙዚቃ በክራር አዝናናሁ፤ ትችላለህ ተባልኩ። ከዚያ ባሕር ዳር አካባቢ ቀለበቴ የሚል ዘፈን ዘፈንኩ፤ እዚያም ትችላለህ ተባልኩ። በላይ ዘለቀን ዘፈንኩ፣ በአገውኛ እርግብ ዳባ፣ እቀፍ አድርጊኝ የሚሉትን ዘፈንኩ። እየሰፋ እየሰፋ ነው የመጣው።

“ከዚያ አዲስ አበባ መጥቼ እናትዋ ጎንደርን ቡርቧክስ ሪከርድስ ሰፋ አድርጎ ሠራው። በጣም ትችላለህ አሉኝ። ከዚያ ካሲናውን. . .እያለ እየሰፋ መጣ። አሁን ደግሞ ይሄ አልበም ሲለቀቅ ተቀባይነቱ በቀናት ውስጥ ትልቅ ነው፤ በጣም ደስ ይላል።”

የከያኔው “አስቻለ” አልበም 14 ዘፈኖችን ይዟል። ቋንቋ፣ ዜማ፣ የሙዚቃ መሳሪያ፣ ድምጽ፣ ባህል፣ ታሪክ. . . ወዘተ። በአጭሩ የማይሰማ ድምጽ የለም።

አስቻለው በሥራው እንደ ቋንቋዎቹ ቅላጼ የአካባቢዎቹን ለዛ ለመላበሱ “ሙዚቃ ሲሰራ ዋናው ነገር ጉሮሮ ላይ ያለው የአነጋገር ዘይቤ ነው፤ ባህሉን መማግ ነው” ይላል።

“ሙዚቃ ሲሰራ ነፍስያን በደንብ ማዳመጥ ያስፈልጋል፤ ምንም ነገር መስማት አያስፈልግም። ዜማ ስሠራ ራሴን እና ራሴን ነው የማዳምጠው። እና የሆነ ነገር መጥቶ አስገባኝ ይለኛል። ቅኝቶችን እንደ ዥረት ስደረድራቸው የሆነ ነገርም ይመጣልኛል። ያን ነገር ደግሞ በአግባቡ ሸመን አድርጎ መጠቀም ነው።

“የጥበብ ማስፈጸሚያ ነኝ ብሎ ነው ማሰብ የሚያስፍልገው። ከጥበብ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መስርቶ፤ የሚገባውን ነገር አድርጎ፤ የሚገባውን ድካም ደክሞ መሥራት ነው። እና ቅስቀሳው ራሱ ሙዚቃው አንድ ሲባል ሁለት፣ ሦስት፣ አራት፣ አምስት አድርገኝ ይላል። ዥረቱን መከተል ነው” ይላል ስለሥራው ሲያስረዳ።

አስቻለ አልበም የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ዜማዎች እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ቅይጥ ነው።

አልበሙ ምን ዓይነት አልበም ነው? ዘውጉ ምንድን ነው? ለሚለው የቢቢሲ ጥያቄ አስቻለው ፈጠነ፤ መልሱ “እኔ አላውቀውም” ነው።

አክሎም “አስቻለ የሚለው ዘፈን ባስኬቶዋ ትጀምራለች፤ እኔ በአማርኛ እቀጥላለሁ፤ በአገውኛ እቀጥላለሁ፤ አማርኛ አገውኛ እየተደረገ፤ በመጨረሻ በግዕዝ [ያበቃል]። የቋንቋም ፊውዥን (ውህደት) አለው።

“ፐርከሽን የደቡብ አለ፤ የእኔ ክራር አለ፤ አታሞ አለ፤ የጉሙዝ ከበሮ አለ። ይሄ ፊውዥን ነው። ስም እስክንሰጠው ድረስ የተለያየ የባህል እና የዘመናዊ መሳሪያዎች ስለሆነ ፊውዥን ብንለው ይሻላል” ይላል።

የራሱን የሙዚቃ ፍልስፍና ነው እየተከተለ እንደሆነ የሚጠቅሰው አስቻለው፤ የተለመደውን የሙዚቃ ሕግ መስበር ይፈልጋል።

“የሆነ ነገር ላይ ለመድረስ ጀምረናል። ከነበረው የሙዚቃ አሰራር ኢንትሮ፣ ብሪጅ ምናምን የሚባለው፤ ሦስት ሦስት. . . ከእሱ ወጥተናል። የሆነ ነገር ለማሰማት ዥረት ጀምረናል” በማለት ሥራዎቹ ላይ ስለሚሰሙ የተለያዩ ድምጾች እና የሙዚቃ መሳሪያዎች ያነሳል።

አስቻለው እና ባልደረቦቹ አዲስ ድምጽ ለመፍጠር ጉዞ ጀምረናል ይላሉ።

እርሱም “ሙዚቃ ፍልስፍና ነው ብዬ አምናለሁ። ግን ደግሞ በብዙ ሕግ እንዲታጠር አልፈልግም። ቀመር ቢኖረንም በቀመር የምንሠራውን በሕግ ለማጠር አንፈልግም። አንድ ሲደመር ሁለት እኩል ይሆናል ሦስት፤ ይሄ ቀመር ነው አይደል? ማሴንቆ ሲደመር ክራር ሲደመር ከበሮ ሲደመር ዋሽንት ምናምን፤ ይሄ ቀመር እንዲሆን አንፈልግም” ይላል።