ሟች ከወላጅ እናቱ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሟች ከወላጅ እናቱ ጋር

21 ጥር 2024, 11:40 EAT

ቱ ዤር ሺንግ አሜሪካዊ ነው። እንደ ኮሎምቢያ የሚወደው አገር የለም።

በተለይ ሜዴይን (Medellin) ከተማ በፍቅሯ ጥላዋለች። አውርቶ አይጠግብም።

“ሕይወት በዚያ ሙሉ ናት፤ ንቅት ያለች ከተማ ናት፤ መኖርን የምታስመኝ” ይላል።

ይህንን ነው ሁልጊዜ በተመለሰ ቁጥር ለወንድሙ ኤህ ሺንግ የሚነግረው።

የ50 ዓመቱ ጎልማሳ ቶ ጄር በሥራው ኮሜዲያን ነው። ሚኒሶታ ነበር የሚኖረው።

የሥራ እረፍት ነበረው። እንደተለመደው ዛሬ ነገ ሳይል ወደ ኮሎምቢያ አቀና። ሁልጊዜም የሚሄደው ወደ ሜዴይን ከተማ ነው።

ለሁለት ወር እረፍት ነበር የሄደው።

የሆነ ቀን ለወንድሙ ደውሎ 2ሺህ ዶላር ላክለኝ አለው። ብሩን ለዚህ ፈልጌው ነው አላለውም። በቃ አስቸኳይ ነው ዝም ብለህ ላክ አለው። ላከለት።

ከዚያች ቅጽበት ወዲያ ወንድሙ ደብዛው ጠፋ። በስንተኛው ቀን የወንድሙ ሬሳ በአንድ ጎጥ ተጥሎ ተገኘ።

“ወንድሜ እንዲያ በሚወዳት ከተማ በፍጹም ይህ ይደርስብኛል ብሎ አላሰበም” ይላል አሜሪካዊው ኤህ ሺንግ።

ሜዴይን ከተማ የሄደው እንዴት ነበር?

ወንድሙ እንደሚለው መጀመርያ አንዲትን ሴት በፍቅር ግንኙነት ማሰናኛ (Dating App) ሲያወራት ነበር።

ፖሊስ እንደሚገምተው ከሆነ አሜሪካዊው የሚኒሶታ ነዋሪ ታግቶ ነው የተገደለው። ከተገደለ በኋላ ከከተማዋ ራቅ ብሎ በሚገኝ አንድ ቆሻሻ መጣያ አስክሬኑ ተጥሎ ተገኘ።

“ልቤ ተሰበረ’’ ይላል ወንድሙ።

የኮሎምቢያ ፖሊስ ከግድያው ጋር ግንኙነት አላት የተባለች አንዲት ሴት እና ሁለት ወንዶችን በቁጥጥር ሥር አድርጓል።

ተመሳሳይ ግድያዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የአሜሪካ ኤምባሲ ለዜጎቹ ማሳሰቢያ መስጠት ጀምሯል።

የፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎችን ተጠቅማችሁ ወደ ኮሎምቢያ ስትሄዱ ቢያንስ ለቤተሰብ አሳውቁ – ሥርቻ ለሥርቻ አትሂዱ ብሏል ኤምባሲው።

ባለፈው ኅዳር እና ታኅሣሥ ወር ብቻ ስምንት አሜሪካዊያን ቱሪስቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድለዋል።

ኤምባሲው እንደሚለው አሜሪካዊያንን በፍቅር አሰናኝ መተግበሪያዎች እያማለሉ የሚዘርፉና የሚገድሉ አደገኛ ቦዘኔዎች በኮሎምቢያ ሜዴይን ከተማ ተበራክተዋል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ10 ወራት ብቻ 32 ቱሪስቶች በዉቧ ሜዴይን ከተማ ተገድለዋል። 12ቱ አሜሪካዊያንና እንግሊዛዊያን ናቸው።

ጄፍ ሔወት ከሟቾቹ አንዱ ነው። ጓደኞቹ ተጫዋች፣ ተግባቢና ከሰዎች ጋር ማውራት የሚወድ ነበር ይላሉ። አስክሬኑ በአንድ የከተማዋ ሆቴል መዋኛ ተንሳፎ ተገኘ።

ጄፍ የተገደለው በዝርፊያ መሀል በተፈጠረ ግብግብ ነበር።

ጆኒ ጀሮሜ ደግሞ 45ኛ ዓመት ልደቱን ሊያከብር ወደዚች ከተማ ሄደ። 46ኛ ዓመቱን ለማክበር አልታደለም። በዚያው ተገደለ።

ፊሊፕ ሉሪንስ ሌላው ሰለባ ነው። አደገኛ እጽ እንዲወስድ ተደርጎ ተገደለ።

እነዚህን ግድያዎች በሙሉ አንድ የሚያደርጋቸው ታዲያ ሁሉም ሟቾች በፍቅር አሰናኝ መተግበሪያ ትውውቅ ወደዚች የኮሎምቢያ ከተማ የሄዱ መሆናቸው ነው።

ሴት ዘራፊዎቹ መጀመርያ ቱሪስቶቹን በአደገኛ እጽ ያደነዝዟቸዋል፤ ከዚያም ይዘርፏቸዋል፤ ከዚያ ይገድሏቸዋል።

ዝነኞቹ የፍቅር አሰናኝ መተግበሪያ የሆኑት ቲንደር እና በምብል በዚህ ረገድ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ካርሎስ ቻሌ የቀድሞው የከተማዋ ቱሪዝም ዳይሬክተር ናቸው።

ሜዴይን በቱሪስቶች የምትወደድ የኮሎምቢያ ከተማ ናት
የምስሉ መግለጫ,ሜዴይን በቱሪስቶች የምትወደድ የኮሎምቢያ ከተማ ናት

ብዙዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ‘ስኮፕላሚን’ የተባለ እጽ እንዲወስዱ ይገደዳሉ። ሽታ የሌለው እጅግ አደገኛ አእጽ ነው። “የሰይጣን እስትንፋስ” በሚል ቅጽል የሚጠራውም ለዚሁ ነው።

አንዴ ከወሰዱት 24 ሰዓት ግለሰቡን ያደነዝዛል።

“ብዙዎቹ ቱሪስቶች ወደዚህ ከተማ የሚሄዱት ለወሲብ ነው፤ አጥቂዎቹም ሴተኛ አዳሪዎች ናቸው” ይላሉ ኬል።

የቱሪዝም ቢሮ ቃል አቀባይ የሆኑት ሰው ደግሞ ከሟቾቹ ብዙዎቹ ወንዶች የሆኑት ለዚህ ነው ይላሉ።

በኮሎምቢያ የወሲብ ንግድ ሕጋዊ ነው። በተለይ ሜዴይን እና ካርታጌና የሚባሉት ከተሞች በዚህ የወሲብ ንግድ ታዋቂ ናቸው።

ነገር ግን ሟቾቹ ሁሉ የወሲብ ንግድ ፍለጋ ሄደው ነው የተገደሉት ማለት አይደለም።

የ36 ዓመቱ አሎክ ሻህ ስኮፖላሚን የሚባለው አደንዛዥ እጽ ምን እንዳደረገው ያስታውሳል።

በ2022 አንዲትን ኮሎምቢያዊት ሴት ወደ ሆቴሉ ይዟት ሄደ። ይህን ‘የሰይጣን እስትንፋስ’ የሚባል እጽ እንዲወስድ አደረገችው። ኋላ ላይ ትዝ እንደሚለው ከእጹ በኋላ የቅርብ ትውስታው ጨርሶውኑ ከአእምሮው ተሰረዘ።

ሁሉም ነገር ሕልም ነበር የሚመስለው።

አሎክ ሻህ የቴክሳስ ነዋሪ አሜሪካዊ ነው። እጹን እንዲወስድ ካደረገችው በ20ዎቹ አጋማሽ ከምትገኝ ኮሎምቢያዊት ጋር የተዋወቀው በቲንደር መተግበሪያ አማካኝነት ነበር።

መጀመርያ ቀን ቡና ጠጡ። በሚቀጥለው ቀን ቢራ ይዘው ወደ ሆቴሉ ይዟት እንዲሄድ አግባባችው።

ምንም አጠራጣሪ ነገር ስላላየ እሺ አላት።

አንገቱ ላይ የሆነ ዱቄት ስትበትንበት ትዝ ይለዋል። 200 ዶላር እና ጃኬቱን ስትወስድ ትዝ ይለዋል። ከዚያ ውጭ ትዝታ የለውም።

አሁን የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ወደ ሆቴላቸው ወይ ገለል ወዳለ አካባቢ በከተማዋ የሚተዋወቋቸውን ሰዎች ይዘው እንዳይሄዱ ማሳሰብ ጀምሯል።

ሌላው ዜጎች በዝርፊያ ጊዜ ፈቃደኛ ሆነው ከመዘረፍ ውጭ ሌቦቹን እንዳይታገሉ አሳስቧል። ምክንያቱም ዝርፊያ ላይ ለመከላከል መሞከር በገዛ ራስ ላይ የሞት ትኬት እንደመቁረጥ ስለሚቆጠር ነው።

ቢቢሲ የከተማዋን ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቀም ከንቲባ ቢሮ አነጋግሩ የሚል መልስ ተሰጥቶታል።

የሜዴይን ከተማ ከንቲባ ፌዴሪኮ ጉቴሬዝ የውጭ ዜጎች በብዛት ወደ ከተማችን እንዲመጡ እንፈልጋለን ካሉ በኋላ ነገር ግን ለወሲብና ለአደገኛ እጽ ሲሉ ብቻ የሚመጡ ቱሪስቶች በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል።

ከንቲባው ጨምረው በተለይ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴቶችን ለወሲብ ንግድ የሚደልሉ ቱሪስቶች ላይ ፖሊስ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

በከተማዋ ወንጀል መበራከቱን ተከትሎ አሁን ፖሊስ በተለይ በምሽት ሕይወት የምትታወቀውን ኤል-ፖፕላዶ ሰፈርን በቅርብ እንዲጠብቅ ተሰማርቷል።

በፈረንጆቹ 2022 ብቻ ይቺን ተወዳጅ ከተማ 1.4 ሚሊዮን ቱሪስቶች ጎብኝተዋታል። ከነዚህ መሀል ሲሶዎቹ አሜሪካዊያን ናቸው።