
21 ጥር 2024, 12:22 EAT
ኢቫን ቶኒ በቁማር ምክንያት ከተከናነበው የስምንት ወር ቅጣት ተመልሷል።
የእግር ኳስ ሜዳ እንደናፈቀው የሚያስታውቅበት ቶኒ መመለስ ብቻ ሳይሆን ጎል በማስቆጠር ደጋፊዎቹን አስፈንድቋል።
የብሬንትፈርዱ አጥቂ ቦግ ባሉ መብራቶች ወደደመቀው ሜዳ ሲገባ ደጋፊዎቹ በእልልታና ሆታ ተቀብለውታል።
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ብሬንትፈርድ ከኖቲንግሀም ፎሬስት ያደረጉት ፍልሚያ በንቦቹ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
እልህ አስጨራሽ በነበረው ፍልሚያ ፎሬስት በዳኒሎ ጎል ቅድሚያውን ቢወስድም ኢቫን ቶኒ ቅጣት ምት አስቅጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።
ቤን ሚ ሁለተኛውን አክሎ ብሬንትፈርድ ቅድሚያ ቢወስድም ፎረስት ድጋሚ በክሪስ ውድ ጎል አቻ መሆን ችሎ ነበር። ነገር ግን ኒል ሞፔይ ለብሬንትፈርድ ሶስተኛ ጎል እና ሶስት ነጥብ አስገኝቷል።
ነገር ግን ቶኒ ያስቆጠራት ጎል ‘አከራካሪ’ ሆናለች።
የ27 ዓመቱ እንግሊዛዊ የብሬንትፈርድ አጥቂ ቅጣት ምቱን ከመምታቱ በፊት የፎሬስት ተጫዋቾች አጥራቸውን እያስተካከሉ ሳለ ኳሷን ከተፈቀደለት ቦታ ሁለት ጊዜ አርቋታል።
ቶኒ ኳሷን በግብ ጠባቂው ግራ ጠርዝ በኩል ባለው ሥፍራው መሬት መሬት በመስደድ ነው ያስቆጠራት።
- የኤሲ ሚላኑ ግብ ጠባቂ በደረሰበት የዘረኝነት ጥቃት ሜዳ ጥሎ ወጣ21 ጥር 2024
- ካሪም ቤንዜማ የፈረንሳይ አገር ውስጥ ሚኒስትርን በስም ማጥፋት ከሰሰ17 ጥር 2024
- ከወጪ ጋር በተያያዘ ፕሪሚየር ሊጉ ለምን ክለቦችን ይቀጣል?19 ጥር 2024
አጥቂው ኳሷን ብቻ ሳይሆን ዳኛው ኳሷን እንዳያንቀሳቅስ ያሰመሩትን ነጭ አረፋ በእጁ ፍቆ ሲያስተካክል ይታያል።
ቢሆንም ቶኒ በቁማር ምክንያት ለስምንት ወር ከሜዳ ርቆ መመለሱ እንጂ ጎሏ እንዴት ተቆጠረች የሚለው አላሳሰበውም።
“ከረዥም ጊዜ በኋላ ተመልሻለሁ” ሲል ለስካይ ስፖርትስ ተናግሯል።
“ቤት ቁጭ ብዬ ስመለስ ቡድኔ ያሸንፋል እያልኩ ሳስብ ነበር። አሁን ይኸው እዚህ ነኝ። በመመለሴ ደስተኛ ነኝ፤ ቡድኔ በማሸነፉም እንዲሁ” ብሏል።
“ገና ከቤት ሳልወጣ ዛሬ እናሸንፋለን፤ እኔም አስቆጥራለሁ እያልኩ ሳስብ ነበር።”
ጨዋታውን በድል የተወጣው ብሬንትፈርድ ወደ 14ኛ ደረጃ ከፍ ብሎ በሁለት ነጥቦች ከፎሬስት ርቆ ተቀምጧል።
ቶኒ ጎሏን ለማስቆጠር ያደረገው ነገር አንዳንዶች ብስጭታቸውን ሲገልጡ ሌሎች ደግሞ በእግር ኳስ ያጋጥማል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የኖቲንግሀም ፎሬስት አሠልጣኝ ኑኖ ኤስፔሬቶ ሳንቶስ ደስተኛ እንዳልሆኑ ከጨዋታው በኋላ ገልጠዋል።
ብሬንትፈርድ ካለፈው የአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ በኋላ በሁሉም ውድድሮች ድል ሲነሱ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
እንግሊዛዊው አጥቂ ባፈለው የውድድር ዘመን 22 ጎሎች ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ነገር ግን አሁን የብሬንትፈርድ ራስ ምታት የሚሆነው በርካታ ክለቦች ዓይናቸውን ቶኒ ላይ መጣላቸው ነው።
ቶኒ “ለትልቅ ክለብ” መጫወት እንደሚፈልግ አይደብቅም። አርሰናል እና ቼልሲ ተጫዋቹን ለማስፈረም ከሚሹ ክለቦች መካከል ናቸው።