በአየዋ ግዛት በበረዶ የተሸፈነ መኪና
የምስሉ መግለጫ,በአየዋ ግዛት በበረዶ የተሸፈነ መኪና

ከ 3 ሰአት በፊት

በአሜሪካ ባለፉት ሳምንታት ቅዝቃዜው መበርታቱን ተከትሎ 89 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።

እነዚህ ከአየር ሁኔታው ጋር የተያያዙት ሞቶች ከተመዘገቡባቸው ግዛቶች መካከል በቴነሲ 25 ሰዎች፣ በኦረገን ግዛት ደግሞ 16 ሰዎች ይገኙበታል።

ሁለቱ ግዛቶች ኃያል የበረዶ ውሽንፉሩን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ይታወሳል።

በረዷማ የአየር ሁኔታው እስከ ቀጣይ ሳምንት አጋማሽ ድረስ ሊዘልቅ ይችላል የሚል ትንበያ አለ።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሚዲያ የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው በጥቅሉ በመላው አሜሪካ የሞቱት ሰዎቸ ቁጥር አሁን ላይ 89 ደርሷል።

ምንም እንኳ ሞት በብዛት የተመዘገበው በኦረገን እና ቴነሲ ግዛቶች ቢሆንም ሌሎች ጉዳቶች በፔንሴልቬኒያ፣ ኢሊኖይ፣ ሚሲሲፒ፣ ዋሺንግተን፣ ኬንታኪ፣ ዊስኮንሲን፣ ኒው ዮርክ፣ ኒው ጀርዚ እና ሌሎች ግዛቶች ተመዝግቧል።

ባለፈው ረቡዕ በፖርትላንድ ኦረገን በመኪና ሲጓዙ የነበሩ ሦስት ሰዎች በበረዶ አውሎ ንፋስ የኤሌክትሪክ መስመር መኪናቸው ላይ ወድቆ ሞተዋል። በመኪናው ውስጥ የነበረች ሕጻን በሕይወት ተርፋለች።

በኬንታኪ አንድ ግለሰብ በመኪና መንሸራተት ግጭት ተፈጥሮ ሕይወቱን ያጣ ሲሆን በኢሊኖይ ግዛት ደግሞ በተመሳሳይ አደጋ 4 ሰዎቸ ሞተዋል።

በሲያትል ከተማ ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑ አምስት ሰዎች በአራት ቀናት ውስጥ መሞታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በሚሲሲፒ የአየር ሁኔታው እየከፋ በመምጣቱ ነዋሪዎች የግድ ካልሆነ መኪና እንዳያሽከረክሩ ተነግሯቸዋል።

በግዛቱ ኮሌጆች ተማሪዎች ከእረፍት የሚመለሱበትን ጊዜ ገፍተወታል።

በሚሲሲፒ ግዛት የዉሃ እጥረት ይከሰታል በሚል ነዋሪዎች ዉሀ ማጠራቀም በመጀመራቸው የቧንቧ ዉሃ ግፊት መቀነሱ ተነግሯል።

ወትሮም ነዋሪዎች ዉሃ በሚቸገሩባት የግዛቱ ዋና ከተማ ጃክሰን የዉሃ እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ባለሥልጣናት እየመረመሩ ነው።

ይህ በሚሲሲፒ ብቻ ያጋጠመ ጉዳይ አይደለም። በቴነሲ ግዛት መምፊስ አካባቢ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች በቧንቧ መስመር መሰበር የተነሳ ለችግር ተዳርገዋል።

የቧንቧ ዉሃ ለጽዳት ካልሆነ እንዳይጠጡም ተመክረዋል።

አዮዋ

በአየር ሁኔታው አስቸጋሪነት የተነሳ የተሰባበሩ የቧንቧ መስመሮችን መጠገን አስቸጋሪ ሆኗል።

በኒው ዮርክ የበፋሎ ቢልስ የአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን መጫወቻ ሜዳው በበረዶ በመሞላቱ ደጋፊዎቹን ትብብር ለመጠየቅ ተገዷል።

ቡድኑ እሑድ ከካንሳስ ሲቲ ቡድን ጋር ለነበረበት ግጥሚያ ነው ትብብር የጠየቀው። ቢልስ ማፊያ ሚል የሚጠሩት የቡድኑ ደጋፊዎች ለሰዓት በረዶውን በማጸዳት 76 ሴንቲ ሜትር ግግር በረዶ ከስታዲየሙ አስወግደዋል።

በአሜሪካ በርካታ አካባቢዎች አሁን የኤሌክትሪ አቅርቦት የተመለሰ ሲሆን በርካታ ቦታዎች ግን አሁንም ችግር ላይ እንደወደቁ ናቸው። ይህም የሆነው የበረዶ አውሎ ንፋስ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ከጥቅም ውጭ እያደረጋቸው በመሆኑ ነው።