EthiopianReporter.com 

ሲሳይ ሳህሉ

January 24, 2024

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለ2016 በጀት ዓመት ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከጠየቀው ሲሚንቶ ማግኘት የቻለው 14 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ከተጠየቀው 682,085 ቶን ሲሚንቶ ማግኘት የተቻለው 95,610 ቶን ወይም 14 በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሪፖርት ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ አስተዳደሩ ለግንባታ ግብዓትነት ከጠየቀው 202,315,139 ሊትር ነዳጅ ውስጥ ማግኘት የቻለው 79,446,433 ሊትር ወይም 39 በመቶ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ችግሩ በጣም ያውካል፣ በጣም ከባድ ነው፡፡ መንግሥት ለህዳሴው ግድብ በሚያቀርበው ሁኔታ እንዲያቀርብልን ጠየቅን፣ ያልወጣንበት ያልወረድንበት ሁኔታ የለም፡፡ አሁን ያለን ተስፋና እየጠበቅን ያለነው በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቀው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያስፈልገንን ምርት ለማግኝት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የአስፋልት (ሬንጅ) እጥረት ማጋጠሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ የነበረው አስተዳደሩ፣ ባለፉት ስድስት ወራት 22,000 በርሜል አስፋልት በአገር ውስጥ ግዥ፣ እንዲሁም 70,000 በርሜል ከውጭ አገር ግዥ ለማከናወን በሒደት ላይ መሆኑን የጠቀሱት መሐመድ (ኢንጂነር)፣ ከዚህ ውስጥ 10,000 በርሜል አስፋልት ገብቶ ለዲስትሪክቶች መሠራጨቱን ተናግረዋል፡፡

ከ238 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉኝ ያለው አስተዳደሩ የግንባታ ፕሮጀክቶች የግብዓት እጥረትን በሚመለከት ከሲሚንቶ አምራቾች ማኅበር፣ ከማዕድን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁንም መቀጠሉንና አሳሳቢ መሆኑን በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

አስተዳደሩ ከግብዓት እጥረት በተጨማሪ በመላ አገሪቱ ካሉት 25 የፕሮጀክት ቢሮዎች 48 በመቶ በፀጥታ ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን አለመቻላቸውን፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ደጀኔ ፈቃደ (ኢንጂነር) ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት ከፕሮጀክት አስተዳደር ኃላፊዎች መካከል ታግተው መለቀቃቸውን፣ መንገድ ላይ በሽፍታ መዘረፋቸውን፣ በጉባ ድልድይ አራት መሐንዲስና ዘጠኝ ባለሙያዎች መገደላቸውን አስረድተዋል፡፡

በየጊዜው የሕይወት መስዋዕትነት እየተከፈለ ነው ያሉት ደጀኔ (ኢንጂነር) በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ሠራተኞች በፕሮጀክት ተሽከርካሪ ብቻቸውን መሄድ ባለመቻላቸው፣ ከሕዝብ ጋር በቅጥቅጥ አውቶቡስ ወይም በሚኒባስ በመሄድ ፕሮጀክቶችን እየተከታተሉ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እያስተዳደርን ያለው ፕሮጀክት ሳይሆን ቀውስ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶች ብዛት 52 መሆናቸውንና ከእነዚህ መካከል በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ ቄለምና ሆሮ ጉዱሩ የወለጋ ዞኖች የሚገኙ ፕሮጀክቶች፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ ባቱ፣ አርሲ ነገሌ፣ ቢልባላ፣ ሰቆጣ፣ ክምር ድንጋይ፣ ጉና፣ እስቴ ስማዳ፣ ጊንጪ ሽኩቴ፣ ሻምቡ አጋምሳ፣ ሻምቡ አጋምሳ፣ ደብረ ማርቆስ ሞጣ ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ከተቋረጡ 32 ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ  አዲአርቃይ ጠለምት፣ ጋሸና ቢልባላ፣ ጥቁር ውኃ ሐዋሳ፣ ውቅሮ አፅቢ ኩናባ፣ ኮረም ላሊበላ፣ ዓዲሸሁ ደላ ሳምረ፣ ማይጨው መኾኒ፣ ዓዲሸሁ ደላ ሳምረ፣ ማይጨው መኾኒ፣ ፍየልውኃ ተከዜና ሌሎችም እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

በዋነኛነት በፕሮጀክቶች አካባቢና በፕሮጀክቶች መዳረሻ (Logistic Corridor) የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች በፕሮጀክቶች ቀጥታ አፈጻጸም ላይ፣ እንዲሁም በግብዓት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡