EthiopianReporter.com 

ማኅበራዊ ‹‹በሁሉም መለኪያ ቢታይ የውድድር ገበያውን እየመራን ነው›› ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮ…

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: January 24, 2024

በፋይናንስና በተለያዩ አቅሞች ተደራጅቶ ከመጣ የውጭ ኩባንያ ጋር የውድድር ገበያን ለማሸነፍ በርካታ ችግሮች ቢገጥሙም፣ አሁንም በሁሉም መለኪያ ቢታይ፣ ‹‹ኢትዮ ቴሌኮም የውድድር ገበያውን እየመራ ነው›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አስታወቁ፡፡

የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ማክሰኞ ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም ያቀረቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣  ተፎካካሪ ከሆነው ኩባንያ ጋር የነበረው ከባድ የዋጋ ውድድር ፈታኝ ነበር ብለዋል፡፡

‹‹በሁሉም መለኪያ ቢታይ የውድድር ገበያውን እየመራን ነው›› ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮ
ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ይሁን እንጂ ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ በተደረገ ግምገማ ተፎካካሪ ከሆነው ኩባንያ ጋር የነበረው ውድድር በእጅጉ ቀንሶ መታየቱንና የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል፡

በአሁኑ ወቅት በጤናማ አሠራር በተፎካካሪ ኩባንያ መሠረተ ልማት በሊዝ መስጠትና የራስን አቅም በማሳደግ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ተጨማሪ ደንበኞች ለማፍራት ጥረት እያደረገ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በውስጥ የፋይናንስ ሪፖርት አሠራር መሠረት (በውጭ ኦዲት ያልተመረመረ ሒሳብ ሪፖርት) የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የፋይናንስ አፈጻጸም ገቢን በማሳደግና ወጪ ቆጣቢ አሠራር ባህልን በማሳደግ ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት፣ ያልተጣራ ትርፍ 19.77 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 137 በመቶ ማሳካት መቻሉ በሪፖርቱ ተመዝግቧል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 11 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ 18.5 ቢሊዮን ብር ታክስ፣ 2.46 ቢሊዮን ብር (43.4 ሚሊዮን ዶላር) ብድር፣ እንዲሁም የመንግሥት የትርፍ ድርሻ ክፍያ (ዲቪደንድ) አራት ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የፋይናንስ ግልጽነትን ለማስፈንና በተቆጣጣሪ አካላት የወጡትን ደንብና መመርያን ለመተግበር የፋይናንስ ኦዲት በወቅቱ እያስደረገ መሆኑን፣ የፋይናንስ ሪፖርቱን በዓለም አቀፍ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት (IFRS) እያወጣ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በኔትወርክ ሀብት ላይ አደጋዎች እንደሚደርሱ፣ የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና የመሳሰሉ ችግሮች ማጋጠማቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በዚህ ምክንያት የደረሰው ኪሳራ ምን ያህል ነው የሚለው በዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደሚገለጽ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በትግራይ ክልል በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በበርካታ የመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፣ መሠረተ ልማቶቹን ለመጠገን ኩባንያው ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች የ4ጂ አገልግሎት በመጀመሩ ምክንያት፣ በርካታ ደንበኞች አገልግሎቱን እየተጠቀሙ እንደሆነ ወ/ሪት ፍሬሕይወት አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በግማሽ ዓመቱ በተደረገ የኔትዎርክ ማስፋፊያ በ3ጂ 678.200፣ በ4ጂ 1.1 ሚሊዮን፣ በ5ጂ 148,200 ሺሕ በአጠቃላይ 1.9 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞች የማስተናገድ አቅም የተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም 81 ሚሊዮን ማድረስ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

የገጠር ቀበሌዎችን የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በመንፈቅ ዓመቱ ከተከናወኑ የሞባይል ማስፋፊያዎች መካከል ለገጠር ቀበሌዎች የሚውል በ10 ክልሎች በ41 ወረዳዎች 229 ሺሕ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችሉ፣ 41 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተተክለው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በገጠር አካባቢ በ92 ነባር ጣቢያዎች የ3ጂ ማስፋፊያ ሥራዎች ተከናውነው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸው በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡