
January 24, 2024

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑቴ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሳፋሪኮም የበይነ መረብ የክፍያ ሥርዓት የሆነውን ኤምፔሳን እንደ አንድ የክፍያ አማራጭ አድርጎ መረጠ፡፡
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ዊም ቫንሄለፑቴ፣ እንዲሁም የኤምፔሳ ሥራ ኃላፊዎች በዚህ ሳምንት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህም አየር መንገዱ ለሚያደርጋቸው ሽያጮች፣ የአየር መንገዱ ደንበኞችና ተጓዦች ትኬት ለመግዛትና ሌሎች ሽያጮችን ለማካሄድ አዲሱን የኤምፔሳ የበይነ መረብ የክፍያ ሥርዓት እንዲጠቀሙ ያስችላል፡፡
‹‹ከቴሌ ብር ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት አለን፡፡ በቴሌብር ሽያጮች እየተካሄዱ ነው፡፡ ሳፋሪኮም ደግሞ አዲሱ የቴሌኮም ድርጅት በመሆኑ ከሳፋሪኮም ኤምፔሳ ጋር ሌላ ውል እንገባለን፡፡ ይኼ ማለት ቴሌ ብርን የሚጠቀም ደንበኛ ከአየር መንገዱ ጋር ትኬት ሲገዛ ወይም ሌላ ሽያጭ ሲያካሂድ ቴሌብርን መጠቀም ይችላል፡፡ ኤምፔሳን የሚጠቀም ደንበኛ ደግሞ አየር መንገዱ ትኬት ለመግዛት ወይም ሌሎች ሽያጮችን ለማካሄድ ኤምፔሳን መጠቀም ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኤምፔሳ አዲስ አማራጭ የክፍያ ሥርዓት ሆኖ ለአየር መንገዱ ያገለግላል፡፡ ወደፊትም አዳዲስ የክፍያ ሥርዓት አማራጮች አስፈላጊ ሲሆኑ ተመሳሳይ ውል እንገባለን›› ሲሉ የአየር መንገዱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኬንያው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩን ተከትሎ በ150 ሚሊዮን ዶላር ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት፣ ኤምፔሳም ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት በሆነው የኢትዮ ቴሌኮሙ ቴሌብርና የሳፋሪኮሙ ኤምፔሳ መካከል የሚደረገው የንግድ ውድድር ከአሁኑ ትኩረት እየሳበ ይገኛል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ከተቋቋመው ቴሌብር ጋር እስካሁን 602 የመንግሥት ተቋማት ስምምነት በመፈጸም የክፍያ ሥርዓታቸውን ያስፋፉ ሲሆን፣ ኤምፔሳም በጅምር ላይ ይገኛል፡፡
ቴሌብር እስካሁን 41 ሚሊዮን ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን በባለፉት ስድስት ወራት 911 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ሽያጮች በቴሌ ብር የክፍያ ሥርዓት በኩል መካሄዳቸውን ትናንት ማክሰኞ ይፋ የተደረገው የኢትዮ ቴሌኮም የመጀመርያው መንፈቅ ዓመት ሪፖርት ያሳያል፡፡
በኬንያ ውስጥ ዋነኛው የበይነ መረብ የመገበያያ ሥርዓት የሆነው ኤምፔሳም በፍጥነት ደንበኞችን እያፈራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሥራ በጀመረ የመጀመርያ ሦስት ወራት ውስጥ 16 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ኤምፔሳ ከሁለት ወር በፊት ገልጾ ነበር፡፡
በተነፃፃሪነት ቴሌብር ከሁለት ዓመታት በፊት ሥራ ሲጀምር በመጀመርያው አምስት ወራት ሊያከናውን የቻለው ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የነዳጅ ሽያጭን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የክፍያ ሥርዓታቸውን በቴሌብር እንዲያከናውኑ መደረጋቸው ቴሌብር በፍጥነት እንዲያድግ አድርጎታል፡፡