EthiopianReporter.com 

ሲሳይ ሳህሉ

January 24, 2024

በሕዝብ ተወካዮች ምክር የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

በመላ አገሪቱ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ከሚጠይቁ ከ238 የመንገድ ፕሮጀከቶች መካከል፣ በቻይና ኤግዚም ባንክና የዓረብ አገሮች ባንኮች ለሚሸፈኑ ፕሮጀክቶች፣ ገንዘብ ባለመለቀቁና ክፍያዎች በመዘግየታቸው ግንባታቸው እየተስተጓጎለ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቱን ከትናንት በስቲያ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያቀርብ አስታወቀ፡፡

በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክና በጃፓን ብድሮች የሚደገፉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ክፍያቸው በወቅቱ ስለሚፈጸም የግንባታ ሒደታቸው ጥሩ አፈጻጸም እንዳላቸው በመግለጽ፣ ቻይና እንዲሁም ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ አራት የዓረብ አገሮች የባንክ ተቋማት ክፍያውን በወቅቱ ባለመፈጸማቸው ከመንግሥት ካዝና ወጪ ተደርጎ እንዲፈጸም መገደዳቸውን፣ የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር መሐመድ አብዱራህማን (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

መቀመጫውን ሱዳን ያደረገውና የዓረብ ባንክ ለአፍሪካ ዴቨሎፕመንት (Arab Bank for Economic Development in Africa-BADEA)፣ እንዲሁም ባዲያና ኦፊድ የተሰኙ የዓረብ ባንኮችና ሳዑዲ ዓረቢያ ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የሚሆን ክፍያ ከተስማሙ በኋላ ለምን እንደሚያዘገዩ እንደማይገባቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ክፍያ እንዲለቁ ሲጠይቁ መልስ አይሰጡም፣ ክፍያውም ለምን እንደማይለቁ አይናገሩም፣ በርካታ ደብዳቤዎች ተልከው መልስ አይሰጡም፣ በጣም ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ ከባንኮቹ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው ገንዘብ ትንሽ በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቢያጋጥምም መንግሥት እንዲሸፍን ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ2016 በጀት ዓመት ለመንገዶች ግንባታ  በአጠቃላይ 76.57 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደጀኔ ፈቃደ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የመንገዶች የካሳ ክፍያ ከግንባታ ፕሮጀክቶች ዋጋ ጋር እኩል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ከ60 በመቶ በላይ ለመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያቱ የወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ከካሳ ክፍያ ጋር በተገናኘ የገንዘብ መጠናቸው 13.9 ቢሊዮን ብርና ከ60.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ 659 መዝገቦች በመደበኛ ፍርድ ቤቶችና በግልግል ዳኝነት ክርክር እየተካሄደባቸው እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርብ አስታውቋል፡፡

አስተዳደሩ ከካሳ ክፍያ ባሻገር የተጋነነ የካሳ ክፍያ መጠየቅና ሕገወጥነት መኖሩን ጠቅሶ፣ ፍርድ ቤቶች ከተቋሙ አካውንት ገንዘብ እንዲከፈል ስለሚያዙ በርካታ ክፍያዎችን ለመፈጸም መገደዱን ገልጿል፡፡

‹‹ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ እጃችን ላይ አለ፤›› ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተጋነኑ የካሳ ግምቶች፣ በተቋራጮች አቅም ማነስና በተለያዩ ምክንያቶች 52 ፕሮጀክቶች በጊዜያዊነት መቆማቸውን፣ 32 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ውላቸው መቋረጡ፣ 109 ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ ቢሆኑም ለረጅም ጌዜ የተጓተቱ መሆናቸው፣ እንዲሁም ስምንት ፕሮጀክቶች ጭራሽ አለመጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በኮሚቴው የመስክ ምልከታ ወቅት አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለመንገድ ግንባታ ካስረከቡ በኋላ የካሳ ከፍያ አልተሰጠንም በማለት ቅሬታ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ለምክር ቤት ጭምር አቤቱታ በፖስታ እየላኩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አንድ የመንገድ ፕሮጀክት ከመጀመሩ በፊት መጠናቀቅ ያለበት ሥራ ተከናውኖ ወደ ሥራ መገባት አለበት ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ይህን የካሳና የወሰን ማስከበር ማነቆ በተደጋጋሚ በማቅረብ ችግሩን መሻገር የማይቻል በመሆኑ፣ የተለየ ሥልትና ስትራቴጂ በመቀየስ እንዲሠራ፣ የተጋነነው የካሳ ክፍያ ተስተካክሎ መስመር እንዲይዝ፣ ተገቢ ነው ተብሎ የቀረበው ካሳ ደግሞ መከፈል እንዳለበት ተናግረው፣ ይህ ጉዳይ በድጋሚ ክፍተት ነው ተብሎ መቅረብ የለበትም በማለት አሳስበዋል፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ የመንገድ ተቋራጮች ብዛት 72 መሆናቸውንና ከእነሱም ውስጥ 45 የአገር ውስጥና 27 የውጭ ተቋራጮች ናቸው ተብሏል፡፡ አፈጻጸማቸው በአገር ውስጥ ተቋራጮች የተያዙ 25 ፕሮጀክቶችና በውጭ አገር ተቋራጮች 11 ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በታች መሆኑን፣ አስተዳደሩ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡