EthiopianReporter.com 

ዜና የሲቪክ ማኅበራት ከመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ እንዲሠሩ ተጠየቀ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: January 24, 2024

በኢትዮጵያ በሰላም ጉዳይ ምክክር የሚያደርጉ የሲቪክ ማኅበራት፣ ከመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ እንዲሠሩ ጥያቄ ቀረበ፡፡

‹‹ሥርየት ለሁሉም›› የተሰኘ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላም፣ መተባበር፣ መግባባትና ትብብርን ለመፍጠርና ለመሥራት፣ በዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን የመሠረቱት አገር በቀል ድርጅት ትናንት ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሰላም ግንባታ የሚሠራውን ፕሮግራም ይፋ ሲያደርግ ነው ጥያቄው የቀረበው፡፡

በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ 5,000 ያህል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶ መካከል፣ በቁጥር ውስን የሚባሉት ብቻ በሰላምና ሰላማዊ ምክክር ዙሪያ ለመሥራት መመዝገባቸውን፣ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የተበታተኑና ራሳቸውን ያልቻሉ መሆናቸው ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በሰላማዊ ውይይት ችግር እንዲፈታ ጥረት የሚያደርጉ ‹‹ቅን ልብ ያላቸው›› ሰዎችና የመሠረቷቸው ተቋማት፣ በሕግ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር በጋራ የማትጋት ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ፣ በሰላም ሚኒስቴር የማኅበራዊ ሀብት ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ኃይለ መስቀል ፀጋዬ አሳስበዋል።

ሰላም ለማስፈን የተቋቋሙ ተቋማት ትርጉም ያለው ሚና ሊጫወቱ ይገባል ያሉት አቶ ኃይለ መስቀል፣ ‹‹ልጃገረዷ የወጠነችው ሰፌት ተጠናቆ አገልገሎት ካልሰጠ በተቀመጠበት እንደሚበሰብስ ሁሉ፣ ድርጅቶችም ዓላማ ይዘው ሲመሠረቱ  የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት በትጋትና በዕቅድ ካልሠሩ መቋቋማቸው ፈይዳ ቢስ ነው፤›› ብለዋል::

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ክንዳለም ዳምጤ (ዶ/ር) አገር አቀፍ የጤና ወረርሽኝ በተነሳበት ወቅት በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የሕክምና ባለሙያ ቁጭ ማለት እንደማይችለው ሁሉ፣ አገር በሰላም ዕጦት ወረርሽኝ እየታመሰች ባለችበት ወቅት ቁጭ ብሎ መመልከት ጤነኛ አያስብልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ለሰላም የሚችለውን ጠብ ያድርግ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ጤነኛ ለሆነ ሰው፣ በለው በለው ከማለት ገለልተኛ ሆኖ አንድ የተሻለ ነገር ጠብ ማድረግ ይሻላል ብለን እናምናለን፡፡ አላስፈላጊ የሃይማኖት፣ የባህል ወይም የቋንቋ ድንበሮችን በማስወገድ ለሰውነት እንሥራ፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ድርጅቱ ወደፊት ከሚዲያ ተቋማት፣ በታችኛው መዋቅር ላይ ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቆዩ አገራዊ እሴቶች፣ ሰላማዊ የችግር መፍቻ መንገዶችና እርሾዎችን አጉልቶ ለማውጣት ያተኮሩ ጉዳዮች ላይ ለመሥራት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የተገኙ አንድ ተሳታፊ፣ ‹‹ያልተበላሸ ነገር የለም፣ እሴቶቻችን ተበላሽተዋል ተበውዘዋል፣ በተወሰነ ደረጃ ሁላችንም ተሳስተነናል፣ ያለንበትን እንደገና ቆመን ማየት አለብን፤›› ብለዋል።

‹‹ጥሩ ዘር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ›› የሚል ድርጅትን ከቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር መመሥረታቸውን የተናገሩት አቶ ዮናስ ማሞ በበኩላቸው፣ ‹‹የአገሪቱ ችግሮች እንደ ፊልም በተለያየ ክፍል ተከፋፍለው እየመጡ ነው፡፡ ሩቅ የመሰሉ ነገሮች እየቀረቡ በራችንን እያንኳኩ ነው፡፡ አንዱ ሲያለቅስ አንዱ እየጨፈረ በተራ ማልቀሳችን አይቀርም፣ በጋራ እየሠራን የጋራ ሀብታችንና እሴታችን የሆነውን ሰላም በጋራ እንጠብቅ፤›› ብለዋል።