EthiopianReporter.com


ማኅበራዊ
ከሱዳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እየገቡ ላሉ ስደተኞች ተጨማሪ ጣቢያ ሊቋቋም ነው

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: January 24, 2024

በየማነ ብርሃኑ

በሱዳን እስካሁን በቀጠለው ጦርነት ተፈናቅለው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀቡ፣ ተጨማሪ የስደተኛ መጠለያ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የአሶሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያሲን አሸናፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሱዳን ውስጥ ያለውን ጦርነት ሸሽተው ድንበር በማቋረጥ ወደ ክልሉ የሚመጡ የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ፣ ጽሕፈት ቤታቸው ተጨማሪ የስደተኛ ጣቢያ ለማቋቋም ከክልሉ መንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡

በክልሉ የሚገኙ ነባር የስደተኛ ጣቢያዎች በበርካታ ስደተኞች በመጨናነቃቸውና ከአቅማቸውም በላይ በመሆኑ፣ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የሚመጡ ስደተኞችን በጊዜያዊነት በክልሉ ኩርሙክ ወረዳ ለማስጠለል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ መሠረት ስደተኞች ከድንበር 50 ኪሎ ሜትር መራቅ ስላለባቸው፣ በጊዜያዊነት ስደተኞችን ያስጠለልንበት ሳድራ ድንበር አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ፣ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ተጨማሪ አራተኛ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ለማቋቋም የቦታ ልየታ ሥራ በማከናወን ላይ ነን፤›› ሲሉ አቶ ያሲን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ሸርቆሌ፣ ፃሬና ባምባሲ በተባሉ አካባቢዎች በሚገኙ ሦስት የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ95,000 በላይ ጦርነቱን ሸሽተው የመጡ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ስደተኞች እንደሚገኙ፣ ጣቢያዎቹ ከሚችሉት በላይ ስደተኞችን እያስተናገዱ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ አምስት የስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ የቶንጎና የጉሬ ጣቢያዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በመቃጠላቸውና በመዘረፋቸው ምክንያት ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ በጣቢያዎቹ የሚገኙ 22,000 ያህል ስደተኞችም ወደ ሌሎች የመጠለያ ጣቢያዎች የተዛወሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡