
ልናገር ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ራሱን በመፈተሽ አገርን ይታደግ
ቀን: January 24, 2024
በያሲን ባህሩ
አንድ የአበው አባባል አለ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል›› የሚል። ይህንን አባባል ወደ ፖለቲካው አምጥተን ስናየው ለብዙ ነገሮች ልክ ሆኖ እናገኘዋለን። ፖለቲከኞች ለሕዝብ ጥቅም ብለው፣ በሕዝብ ስም ተደራጅተው፣ የሕዝብ በሆነ ነገር ሁሉ እየተጠቀሙ ሕዝብን ቢረሱ መልሶ ሕዝቡ ያስወግዳቸዋልና አባባሉ ልክ ስለመሆኑ ምንም ክርክር አያስነሳም፣ ጥርጥርም የለውም።
ከዚህ አንፃር ብልፅግናን እንደ ድርጅት መንግሥትንም እንደ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ያላቸውን መሰጠት ስንፈትሽ፣ በተፈጥሯቸው ወይም ከአጭር ታሪካቸው አኳያ መብጠልጠል አይገባቸውም ቢባል እንኳን ከችግር ፈጥነው አለመውጣታቸውና ነገሮች ሲባባሱ መታየታቸው ከመወቀስ እንዳይድኑ አድርገዋቸዋል። ከሁሉ በላይ አገራዊ የሰላምና የደኅንነት ዕጦት እስከ መቼ ፖለቲከኛውን እንቅልፍ እንዲወስደው ያደርጋሉ? የኢሕአዴግ ወራሹ ብልፅግና የቀደመውን ሥርዓት የለወጠበትን ጠባብ ብሔርተኝነት፣ ሙስና፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ኢፍትሐዊነትና የሕዝብ አገልጋይነት መጥፋትና የመሳሰሉ ችግሮችን ላለመድገም መትጋት ነበረበት፡፡ በአመለካከት የቅደም ተከተል ጉዳይ አንዱ ከሌላው ቢያለያይምና መንግሥት በልማት ረገድ የጀመራቸው ሥራዎች አሁንም ተስፋ ሰጪ ናቸው ቢባልም፣ የኑሮ ውድነትና ድህነት ግን እየተቀረፉ አይደለም፡፡ የሰላም መደፍረሱም በየቦታው የችግረኛውን ቁጥር እያበራከተው ነው፡፡
መላው ሕዝብ በዕርቀ ሰላም መንፈስ ተደማምጦና ተከባብሮ፣ በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና በአንድነት እንዲኖር አለማድረግ፣ ነገሩን ሁሉ በቡሃ ላይ ቆረቆር እያደረገው ነው፡፡ በእርግጥም አሁን እየታየ ያለውን በየክልሉ የተስፋፋ ግጭት፣ አለመግባባትና የደኅንነት ሥጋት ለመቅረፍ አለመነሳት ከውድቀት የሚያድን አይሆንም፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ፖለቲከኞች፣ ራሱ ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡
በተለይ አገርን ከዕልቂት አደጋ መጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ዜጎች የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ላይ አጥብቆ ማሰላሰል ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች የአገራቸው ጉዳይ ያገባቸዋል፡፡ በገዛ አገራቸው የሚፈጠሩ ጉዳዮችን ችላ ማለትም ሆነ የተፈጠረውን እንዳልተፈጠረ መተው፣ እንዲሁም የተፈጠረውን ችግር በማቀጣጠል ማራገብ አይገባቸውም፡፡
ሁሉም በአገሩ ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት ሊኖረው ይገባል ሲባልም፣ የተናጠልና የወል እሴቶችን ጠብቆ በአገረ መንግሥቱ ሥር ተግባብቶ እንዲኖር ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ከጊዜያዊና ዘላቂ የጥቅም ግጭቶች እየወጣ ዕድል ፈንታውን በጋራ ወደ የሚወስንበት አቅጣጫ ሲተም ነው፡፡ ከጦርነትና ከዕልቂት ማንም አያተርፍምና መነጋገርና መቀራረብን የፖለቲካው መልህቅ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ተዋናይ ብልፅግናና መንግሥት ናቸውና ትኩረታችንን በእዚህ አካላት ላይ በማድረግ እንቆይ፡፡
በታሪክ አጋጣሚ የአገሪቱ ከሰማይ በታች ያሉ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶችና ሕዝቦች ብሎም የውስጥና የውጭ ግንኙነቶች፣ ከእነ ሉዓላዊ ግዛትና ድንበራችን ሁሉ ለመንግሥት ይተዳደሩ ዘንድ ግድ ሆኗልና መሪው ፓርቲ የውስጥ ችግሮቹን በመቅረፍ፣ የአገሪቱን ችግሮችም ያስወግድ ዘንድ ይጠበቃል፡፡ የእነ እገሌ መንግሥት ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች መንግሥት በቃልም በተግባርም መሆን ግድም ይላል፡፡
ሕዝብን ከሕዝብ አስማምቶና በፍትሐዊነት አስተዳድሮ፣ የሕግ የበላይነትን አንብሮ መገኘትም ይጠበቅበታል፡፡ እናም በታማኝነትና በቅንነት ብቻ ሳይሆን በመዋቅር ደረጃ አፍ ከልብ ሆኖ በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች አገርን ወደፊት ለማራመድ መትጋት ቀዳሚ ድርሻው ሊሆን ይገባል፡፡ ታሪካዊ አደራም ወድቆበታል፡፡
እውነት ለመናገር ብልፅግና በታሪክ አጋጣሚ አገራችንን እየመራ ስላለ፣ ከችግሩ እንዲወጣና አካሄዱን እንዲያርም ከመጎትጎት አልቦዝንም፡፡ ነገር ግን ብልፅግና የተስፋ ዳቦ እየሆነ ነው ያስቸገረው፡፡ ሲጀምር በአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር፣ በሕዝቦች ብዝኃነትና ጠንካራ መስተጋብር መፍጠር ላይ የማያወላዳ ብሎም ለልማትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይተኛ እንደሆነ ቢታመንም፣ እንደ ቃሉ ሆኖ እየተገኘ አይመስልም፡፡ ከቀውስ ውስጥ ወጥቶ ራሱንም አገርንም ዕፎይታ እንዳልሰጠም እየታየ ነው (በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየሆነ ያለውን ልብ ይሏል)፡፡
የብልፅግና ትልቁ ፈተና ደግሞ በውስጡ ካለው አድርባይነትና አፈንጋጭነት የሚመነጭ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች በሹክሹክታ እየተናገሩ ነው፡፡ በመሠረቱ ምንጊዜም ለውጥ ሲመጣ ዋነኞቹ እንቅፋት የሚደቅኑት ከውጭው ሁኔታ ይልቅ፣ በውስጥ ጥንካሬ ማጣት ላይ የሚጠነሰሱት ችግሮች ናቸው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ እናም መንግሥትም ይባል ፓርቲው በረጋ መንፈስና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ውስጡን ይፈትሽ ዘንድ እንደ ዜጋ የመሰለኝን ከመጠቆም አልቦዝንም፡፡
ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው በሚገባ እየተናበቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠበቅ ያለ ሲሆን ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውና በሁሉም አካባቢዎች ደኅንነታቸው በተግባር ሲረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ ይህን ቁልፍ ተግባር አጠናክሮ መተግበር ደግሞ የመንግሥት አልፋና ኦሜጋ መሆን አለበት፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው አንዳንዱ የመንግሥት አካል በዕብሪት ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ፣ ለሴራ ፖለቲካ ራሱንና መንግሥትን እያጋለጠ፣ በታሪክ የተዛባ ትርክት ሲሳከር ይከርማል፡፡ ተው ባይም ያለ አይመስልም፡፡
የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች፣ ክልሎች እርስ በራሳቸው የማይተማመኑ፣ ቃላቸው የሚጣረስ፣ የመንግሥት አካሄድም የማይታወቅና ግልጽነት የሌለው እየሆነ ያለውም በዋናነት በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ችግር በሚፈጥሩ አካላት ነው፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ትልልቅ ሰዎች ሳይቀሩ አፍ ከልብ ሆነውና ተደማምጠው ከመሥራት ይልቅ፣ አስመሳይነትና አፈንጋጭነትን መገለጫቸው ማድረጋቸው የአገር ችግር ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አላባራ ላለው የግጭት አዙሪት መነሻውም ይኼው አለመደማመጥ ነው፡፡
ከለውጥ ወዲህ ተፎካካሪው ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ራሱ የብልፅግና ኃይል በሚያራምደው የተምታታና ግብታዊ ውሳኔና አለመግባባት (ውሳኔዎችን በጋራ ጨብጦ ወደ ተግባር ባለመግባት) የፀጥታ መዋቅሩና መከላከያው ላይ ታች ሲል የሚኖረውስ እስከ መቼ ነው ብሎ መጠየቅ ግድ የሚልበት ወቅት መጥቷል፡፡ በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ እንኳን የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ፣ መላው ይመለከተናል የሚሉ ኃይሎች ሁሉ ሊመክሩባቸው የሚገቡ አገራዊ አጀንዳዎችስ ወዴት ቸል ሊባሉ ይችላሉ ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡
በመሠረቱ በየትኛውም መለኪያ የመጨረሻው የሥልጣን ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ በመሆኑም በሕዝቡ ይሁንታ የፀደቁትን ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና በጥቅሉ የሕግ የበላይነት የነገሠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከሕዝብና ከወኪሎቹ ጋር እየመከሩና እየተደማመጡ ከመሥራት ውጪ ሌላ መንገድ የለም፣ ሊኖርም አይገባም፡፡ እዚህ ላይ በኃይል መብታቸውን ለማስከበርም ሆነ አስተሳሰባቸውን ለመጫን የሚሹ ኃይሎች ቆም ብለው ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ወደ ሰላም አማራጭም መምጣት አለባቸው፡፡
አሁን በሚታየው ሁኔታ በብልፅግና ቤት ሕዝበኝነት፣ ብሔርተኝነትና መርህ አልባነት ክንፍ አውጥተው መብረር ይዘዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን እንደ መርህ አለመቁጠርና በየራስ ፈረስ መጋለቡም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮችን በኃይል ብቻ ልፍታ ብሎ ማሰብ የሚበጅ አልሆነም፡፡ እነዚህ ፈተናዎች ደግሞ አገርን ወደ ቀውስ ይወስዱ እንደሁ እንጂ ለማንም አይጠቅሙም፡፡ እናም ለቀውስ ሁሉ መፍቻ መንገዱ ከራሱ ከገዥው ፓርቲ የውስጠ ዴሞክራሲ ትግል ሊጀምር ይገባል ብቻ ሳይሆን፣ ከድርድርና ሰጥቶ መቀበል ዕሳቤ መመንጨትም አለበት እላለሁ፡፡
መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በብዙ ፈተና ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት እንኳን፣ ከራሳቸውና ከቢጤዎቻቸው ጥቅም በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የማይሰጣቸው ደካሞች በየመዋቅሩ ውስጥ እየታዩ ነው፡፡ ያላመኑበትን ለማስፈጸም ተማምለው የሚንሸራተቱ ድንክዬዎችም በዝተዋል፡፡ ከጎን ያለው የዩቲዩብ አጫፋሪና ሕዝብ ጥቅም ደንታ የሌለው ቱልቱላ እየበዛ የሄደውም በዚህ ክፍተት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ መንግሥት በ‹‹ቼክና በባላንስ›› ሥርዓቱ እንዲመራ እየተደረገ አለመሆኑ፣ ግለሰባዊ አምባገነንነትና ኦሊጋሪክን መታገል አለመቻሉ ነው የሚሉም በርካታ ናቸው፡፡
ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ምቾት ብቻ ስለሚያስቀድሙ፣ ለእነሱ ሕዝብ ማለት ምንም አይደለም፡፡ ሕዝብን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በዳበረ ዕውቀትና ክህሎት ለማገልገል አሁንም ብቃቱ ያላቸው በርካታ ዜጎች እያሉ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ የኦሊጋርኪዎች ስብስብ መንግሥትን መፈናፈኛ እያሳጡት መሆኑን ማወቅና ማስተካከል ይጠበቅበታል (በሠለጠነ ዘመን እንደ ጥንቱ በመሳብ ስለተራና አድሏዊነት መጨነቁ የሚመጣውም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማንነት ካለመረዳት ነው)፡፡
እንዲህ ያሉ ፖለቲከኞች ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ሆነ ለአገር አንድነት ደንታ የላቸውም፡፡ ብቻ በብሔር እየማሉና እየተገዘቱ ጥቅማቸውን ማሳደድ፣ ካልበላሁት ጭሬ ልድፋው ማለት ነው የሚቀናቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ኃላፊነታቸው የሆኑ ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ተሰግስገው እየመዘመዙን መሆኑንም እያየን ነው። ይህን ክፉ መንገድ አለመታገል ካለ ጥርጥር አገርን ወደ ቀውስ መግፋቱ አይቀሬ ነው፡፡
በየአካባቢው የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና ያልተሠራውን ሁሉ በወሬ በመሙላት መንግሥት በሕዝብ ዘንድ እንዳይታመን ከማድረግም አይቦዝኑም፡፡ እናም እንደ መንግሥትም (በሦስቱም መንግሥታዊ ክንፎችና በየደረጃው) ሆነ ብልፅግና እነዚህን አካላት ሳያስተካክሉና ሳያጠሩ ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደ ምን ይቻላል? ሕዝብ ሳይፈቅድና ቅሬታ ሲያቀርብ በኃይል ልጨፍልቀው ብለው የሚያስቡም ተሳስተው የሚያሳስቱ ከንቱዎች ናቸውና ይነቃባቸው፣ አገር አትጎዳ፡፡
በተለይ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በክልልም ሆነ በቦታ የተቀመጡበት ሥፍራ ይለያይ እንጂ ዓላማቸው ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት እንደሚያሳየው ግን በተለያየ አገር እንደሚሠሩ ሁሉ ውህደትና መናበብ የጎደለው አፈጻጸም ነው ያለው፡፡ በአንዳንዱ አካባቢ በግል ጥቅምና ሌብነት ላይ ሲርመጠመጥ የሚውለውም ትንሽ አይደለም፡፡ አንዱ ተግቶ ሲሠራ፣ ሌላው ከሽፍታና ከወንበዴ ጋር እየተሞዳሞደ በንፁኃን ደም የሚቀልደውም ቢሆን እዚሁ ዓይናችን ሥር ነው፡፡
በመላ አገሪቱ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ በትራንስፖርት፣ በግዥና ጨረታ፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በፍትሕ አካላት፣ ወዘተ ውስጥ አሁንም ቀላል የማይባል የመልካም አስተዳደር ጉድለትና ሙስና ይስተዋላል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ በመዋቅሩ ውስጥ ባሉ ጥቅመኞች መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ሕዝብንም እያማረረና እያቆሰለ ነው፡፡
ለሙስና መስፋፋት አሉታዊ ሚና የሚጫወቱትን ነጣቂዎች ከተነጠቀውና እየተነጠቀ ከሚገኘው ሕዝብ በላይ ማንም የሚያውቃቸው የለም፡፡ ሥርዓቱ ደግሞ ሕዝቡን እያዳመጠ ውግንናውን ለብዙኃኑ ማረጋገጥ ካልቻለ ሥርዓታዊ ሙስና ወደ መምሰል ነው የሚሄደው፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ተግባርም ሆነ አፈጻጸም ላይ ሕዝብን እያሳተፉ ከመታገል ውጪ አማራጭ የለም። ለሥልጣን መሟሟቱ የሚመነጨውም ከአቋራጭ ብልፅግና ዕሳቤ መሆኑን ተረድቶ መታገል ግድ ይላል፡፡
አሁንም የሥርዓቱ አደናቃፊዎች ለውጡም ሆነ መጭው ጊዜ ከቀውስ እንዲወጣና አገር እንድትረጋጋ አይፈልጉም፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግም አይፈልጉም፡፡ በአንድ በኩል ሌብነቱና የሴራ ፖለቲካው እንዳይጋለጥባቸው፣ በሌላ በኩል ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነትን እንዳይላበስ ይኳትናሉ፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ተዓማኒነት የሌላቸውና ልፍስፍስ እንዲሆኑ የሚሠሩ ኦሊጋርኪዎችም አይጠፉም፡፡ ይኼን መቀየር ካልተቻለ አገር መምራት ከንቱ ምኞት ነው፡፡
በየአካባቢው ሕዝቡ በተደማመረ ምሬት መንግሥትን እንዲያጨናንቅ የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና ያልተሠራውን ተሠራ በማለት ሲያውኩም ይታያሉ፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንዲኮሰምንና ጠባብነትና መንደርተኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ሕዝብ በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ምሬት እየተፈጠረበት አገሩን እንዲጠላ ሲደረግ መታገል ካልተቻለ አደጋ ላይ ነን (በእውነቱ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ባይጠቁና ባይገደሉ አሁን ይኼ ሁሉ አፈንጋጭነት ይፈጠር ነበር)፡፡
በየትኛውም አገር ይሁን መንግሥታት እንቅፋቶች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ አገራችንም በተለያዩ ጊዜያት ፈተና ሲገጥማት ነበር፡፡ ይነስም፣ ይብዛም የሚገጥሟት ፈተናዎችና ችግሮችም የሚደርሱትን ጉዳት እያደረሱ ታልፈዋል፡፡ አሁን በፖለቲካ ተቸንካሪዎችና አክራሪ ብሔርተኞች ወዳልተፈለገ ግጭትና ትርምስ ገብታ ዋጋ ስትከፍል ማየት ግን ብልፅግናን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ ይኼን መታገል ያልቻለ አገረ መንግሥት ደግሞ መቀጠል የሚቻለው አይሆንም፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው ከመኖራቸው ባሻገር፣ ወደፊትም ተደጋግፈው ለመኖር በቃል ኪዳን መተሳሰራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ አብሮ ለመኖር የሚያውኩ የሕግም ሆኑ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚቻለው ደግሞ፣ በመነጋገርና በመደማመጥ ብቻ ነው፡፡ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጋራ በሚገነቧት አገር በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተማምነው የጀመሩት ጉዞ የሚፀናው ደግሞ ብልፅግናን የመሰሉ አገር የሚመሩ ኃይሎች ሲጠናከሩ ነው፡፡ መጠናከር ለምን ተሳነን ብሎ መነሳት ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተያያዙትን የብልፅግና መንገድም ሆነ አዲስ ዕይታ ለማጠናከር ተሳትፏቸው መጠናከር አለበት፡፡ ከተዛባ ትርክትና ፍጥጫ ወጥተው ለመጭው ትውልድ የሚተርፍ ጉዞ መጀመርም አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መላው የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃኑ ዴሞክራሲያዊ ባህል ማጎልበት ሰላማዊ ትግልን ማጠናከር ግድ ይላቸዋል፡፡ መንግሥትም ውስጡን ማጥራት ብቻ ሳይሆን አካሄዱን ግልጽ ማድረግና ራዕዩን ለመላው ሕዝብ ማጋራት አለበት፡፡
ብልፅግና የመላው የአገራችን ሕዝቦች ውክልና ያለውና አገር እየመራ ያለ እንደመሆኑ በሆደ ሰፊነትና በኃላፊነት ስሜት አገር መምራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅድሚያ የራሱን አዋኪዎች ማጥራትና ማስወገድ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀድሞ ያጡትን መብትና ጥቅም ራሳቸው በጋራ ባፀደቁት ሕገ መንግሥት አማካይነት ተጎናፅፈውም ሆነ እያሻሻሉ መሄድ የሚችሉት ይህ የፖለቲካ መረጋጋትና ስክነት ሲኖር ነውና። ከአመፃና ከትጥቅ ትግል ይልቅ የዴሞክራሲ ትግል ሲበረታም ነውና፡፡
ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደርም በተጨማሪ፣ በአገራቸው ሀብት እኩል የመጠቀምና በእኩልነት የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው ቅድሚያ ሰላማቸው ሲጠበቅ ነው፡፡ ልማታቸውን በማፋጠንና ዴሞክራሲያቸውን በማጎልበት ጉዟቸውን መቀጠል የሚችሉትም አንዱ ከሌላው ሳይበላለጡና ሳይገፋፉ በሥርዓቱ ላይ እምነታቸውን ሲያጠናክሩ ነው፡፡
አሁን እየታየ ያለው ሽኩቻና መብላላት ቆሞ፣ በሰከነ መንገድ ኢትዮጵያውያን ኅብረታቸውና አንድነታቸው መጠናከር የሚችሉት ግን አርዓያነቱ ከመሪው ፓርቲ ሲጀምር ነው፡፡ የአገራችን ሕዝቦች በእስከ ዛሬው ትግላቸው ወድቀው እየተነሱ፣ ያበበውን የዴሞክራሲያዊ ጅምር ማጠናከር የሚችሉትም በዚሁ መንገድ ነው፡፡ እንደ ዜጋ መንግሥትን አምነውና አደራ ሰጥተውም አገርን መጠበቅና የጋራ ጥቅምን ማስከበር ሲችሉም ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ግን መንግሥትና ተዋንያኑ ወደ ቀልባቸው ይመለሱልን፡፡ አገርን ከውድቀት ለማዳንም ይነሱ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡