
ከ 5 ሰአት በፊት
በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ የመጨረሻው ምሽት አራት ጨዋታዎች ተደርገው አንድ ጎል ብቻ ነው የተስናገደው።
ጠንካራ አቋም ላይ የምትገኘው ሞሮኮ ዛምቢያን 1 ለምንም በመርታት ለአዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ውለታ ውላለች።
ዛምቢያ ምርጥ ሶስተኛ ሆኖ ዙር 16ን ለመቀላቀል አንድ ነጥብ ብቻ ነበር የሚያስፈልጋት።
ነገር ግን ሐኪም ዚዬች አክርሮ ወደ መረቡ የለጋት ኳስ የዛምቢያን ተስፋ ያጨለመች፤ የአይቮሪ ኮስትን ደግሞ ያለመለመች ሆናለች።
አራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ጋና እና የ2019 የዋንጫው ባለቤት አልጄሪያ በአስደንጋጭ ሁኔታ ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
ያልተጠበቁት ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ኬፕ ቨርድ ደግሞ ምድባቸውን በመምራት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።
የዙር 16 ጨዋታዎች መጪው ቅዳሜ ይጀምራሉ።
ናይጄሪያ ከካሜሩን እና አዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ከሴኔጋል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ከሚባሉ ጨዋታዎች መካከል ናቸው።
- የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ የጨዋታ ፕሮግራም እና ውጤቶች15 ጥር 2024
- የስፖርት እና የታሪክ ማጣቀሻው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ23 ጥር 2024
- ከወጪ ጋር በተያያዘ ፕሪሚየር ሊጉ ለምን ክለቦችን ይቀጣል?19 ጥር 2024
የትኞቹ ቡድኖች አለፉ?
ከምድብ ሀ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ናይጄሪያ ቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ናቸው። ጊኒ ቢሳው ስትሰናበት አስተናጋጇ አይቮሪ ኮስት ምርጥ ሶስተኛ ሆና ተሸጋግራለች።
ኬፕ ቨርድ የምድብ ለ ቁንጮ ሆና ወደ ቀጣዩ ዙር ስትሸጋገር ግብፅ ሁለተኛ ሆና አልፋለች። ጋና እና ሞዛምቢክ ተሰናብተዋል።
ሴኔጋል እና ካሜሩን ከምድብ ሐ ወደ ቀጣዩ ዙር ቀጥታ ያለፉ ሀገራት ናቸው። ጊኒ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ዕድል ሲቀናት ጋምቢያ ልትሰናበት ግድ ሆኗል።
አንጎላ የምድብ መ አናት ላይ ተቀምጣ ነው የጨረሰችው። ቡርኪና ፋሶ ደግሞ ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሞሪታኒያ ምርጥ ሶስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ አልጄሪያ በጊዜ ሻንጣዋን ሸክፋለች።
ቱኒዚያም እንዲሁ ከምድብ ሰ በጊዜ የተሰናበተች ሀገር ስትሆን ማሊ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ ወደ ጥሎ ማለፉ ተሸጋግረዋል።
በመጨረሻው ምድብ ሞሮኮ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ ዲአር ኮንጎ ሁለተኛ ሆና አልፋለች። ዛምቢያ እና ታንዛኒያ ወደ ቤታቸው መሄድ ግድ ሆኖባቸዋል።
የመጨረሻዎቹ 16
ቅዳሜ አንጎላ ከናሚቢያ የሚያደርጉት ፍልሚያ የመጀመሪያው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ነው። ከዚያ ቀጥሎ ንስሮቹ ናይጄሪያዎች ከአይበገሬ አናብስቱ ካሜሩን ይጋጠማሉ።
እሑድ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከጊኒ ይጫወታሉ። የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤቷ ግብፅ ደግሞ ከዲአር ኮንጎ ትፋለማለች።
ሰኞ ሞሪታኒያ ከኬፕ ቨርድ ገጥማ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍፃሜ ለመድረስ ትፋለማለች። ከዚያ ቀጥሎ ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ሴኔጋል ከአዘጋጇ አይቮሪ ኮስት ትገናኛለች።
የዙር 16 የመጨረሻ ጨዋታዎች ማክሰኞ የሚከናወኑ ሲሆን ማሊ ከቡርኪና ፋሶ፤ እንዲሁም በፊፋ ደረጃ ምደባ የአፍሪካ ቁንጮ የተባለችው ሞሮኮ ከደቡብ አፍሪካ ትገናኛለች።
አስደናቂ ብቃት ያሳዩን
ብዙዎች ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ሴኔጋል የዘንድሮውንም ዋንጫ ልታነሳ ትችላለች የሚል ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው።
ሴኔጋል ሁሉንም የምድቡን ጨዋታዎች በማሸነፍ በዘጠኝ ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፉ ተሸጋግራለች።
ወደ ሳዑዲ ያቀኑት ሳዲዮ ማኔ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ እና ኤድዋርድ ሜንዲ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ቶተንሃሙ ፓፔ ማታር ሳር እና ላሚን ካማራ ያሉ ወጣቶችም የሴኔጋል ጥንካሬ መለኪያ ናቸው።
ብዙዎች እዚህ ይደርሳሉ ብለው ያልጠበቋቸው ኬፕ ቨርድ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ምድባቸውን በመምራት ወደ ጥሎ ማለፉ ተሸጋግረዋል።
በተለይ ኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጇ አይቮሪ ኮስትን በገዛ ሜዳዋ 4-0 ረትታለች።
የኢኳቶሪያል ጊኒው የ34 ዓመት አጥቂ አሚሊዮ ንሱዌ በአምስት ጎሎች የውድድር ኮከብ ጎል አግቢ ሰንጠረዥን ይመራል።
ናይጄሪያ ደግሞ አንድ ጎል ብቻ በማስተናገድ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈች ሲሆን የውድድር ምርጥ ተከላካይ ያላት ሀገር ተብላለች።
በካታር የዓለም ዋንጫ ብዙዎችን ያስደመመችው ሞሮኮ አንድ ጨዋታ እየቀራት ወደ ጥሎ ማለፉን ያረጋገጠች ሲሆን ለዋንጫው ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ናት።