
ከ 6 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት በዓለማችን የሚከሰቱ ግጭቶች ማስቆም አልቻለም የሚለው ወቀሳ አዲስ አይደለም።
ነገር ግን መጀመሪያ የዩክሬን ቀጥሎ ደግሞ የጋዛ ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ድርጅቱ ከባድ ትችት እንዲያስተናግድ መስኮት ከፍተዋል።
በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት አለመኖሩ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ አባብሶታል።
የተባበሩት መንግሥታት ጣልቃ እንዲገባ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብም ድርጅቱ ምንም ማድረግ አለመቻሉ፣ ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚሉ ጥያቄዎች እንዲቀርቡበት አድርጓል።
የተባበሩት መንግሥታት ትችት እና ወቀሳ እየዘነበበት ያለው ለምንድን ነው? ምንስ ማድርግ ይችላል?
**
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የተባበሩት መንግሥታት ዋን ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በተደጋጋሚ ሲማፀኑ ተሰምተዋል።
ባለፈው ሳምንትም እንዲሁ ዋና ፀሐፊው በጋዛ በሚካሄደው ጦርነት ዓለም አቀፍ ሕግ እየተከበረ አይደለም ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።
ጉቴሬዝ “ለእስራኤላውያን እና ለፍልስጤማውያን ሰላም የሚያመጣ የሁለት አገር መፍትሔ እንዲመጣ እሻለሁ” ብለዋል።
- የተባበሩት መንግሥታት ሄሊኮፕተር እና ተሳፋሪዎች በአል ሸባብ ቁጥጥር ሥር ዋሉ11 ጥር 2024
- ቀይ ባሕርን ያወከውን የሁቲዎች ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ይሳካ ይሆን?23 ጥር 2024
- የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና አልሻባብ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑ ተዘገበ24 ጥር 2024
ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀፅ 99 ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅመዋል።
ይህ አንቀፅ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ፀጥታ ስጋት ነው ያሉትንን ጉዳይ ለፀጥታው ምክር ቤት የሚያቀርቡበት ነው።
እስራኤል በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደረግ የሚለውን ሐሳብ እስካሁን እየተቃወመች ሲሆን፣ ዘመቻዋን ሐማስ እስኪደመሰስ ድረስ እቀጥልበታለሁ ትላለች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ፍልስጤም አገር መሆን አለባት የሚለውን ሐሳብ ፈጽሞ እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እስራኤል በወሰደቻቸው እምርጃዎች ቢያንስ 25 ሺህ ሰዎች ጋዛ ውስጥ ተገድለዋል።
የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ማድረግ አልቻለም።
ባለፈው ታኅሣሥ ምክር ቤቱ ወደ ጋዛ እርዳታ እንዲገባ ምክረ-ሐሳብ ቢያቀርብም የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚያስችል አስገዳጅ ውሳኔ ለማሳለፍ ሳይቻል ቀርቷል።
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበችው የእስራኤል ቀኝ እጅ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ ናት።
ምንም እንኳ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሁለት ጊዜ በአብላጫ ድምፅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ቢወስንም ይህን ተግባራዊ ማድረግ ተስኖታል።
ለመጨረሻ ጊዜ ድምፅ በተሰጠበት ወቅት ከ193 የድርጅቱ አባላት መካከል 153 አገራት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ አስገዳጅ አይደለም።

“የተባበሩት መንግሥታት ኮማ ውስጥ ነው”
የለንደን ኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካል ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር የሆኑት ፋዋዝ ጌርጌዝ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር፤ አሁን ደግሞ የጋዛው ጦርነት የፀጥታው ምክር ቤት “የማይሠራ እና ከጥቅም ውጪ” መሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ።
ጠቅላላ ጉባዔው “ከሥራ አስፈፃሚ ድርጅትነት ይልቅ የይስሙላ ተቋም ነው” ሲሉም ይተቻሉ።
ምሑሩ እንደሚሉት የፀጥታው ምክር ቤት ቻይና እና ሩሲያ በአንድ በኩል፤ አሜሪካ እና አውሮፓ በሌላ በኩል ሆነው ጉልበታቸውን የሚለካኩበት መሣሪያ ነው።
“የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በውስጡ ያሉ ድርጅቶች ‘ኮማ’ ውስጥ ናቸው” የሚሉት ፕሮፌሰሩ “ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የከፋው ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት 15 አባላት ያሉት ሲሆን፣ አስሩ ተለዋዋጭ አምስቱ ደግሞ ቋሚ ናቸው።
አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ እና ቻይና የምክር ቤቱ ቋሚ አባል አገራት ናቸው።
እኒህ አገራት በተለምዶ ፒ5 ተብለው ይጠራሉ።
አገራቱ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት ከመሆናቸው በተጨማሪ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አላቸው። ይህ ማለት ሌሎች ቢስማሙ እንኳ አንድ አገር ውሳኔን ውድቅ የማድረግ ኃይል አለው ማለት ነው።
አሜሪካ ሁለት ጊዜ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የቀረበውን ጥያቄ ድምጿን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋለች፤ ሩሲያ ደግሞ በዩክሬን ጉዳይ እንዲሁ ኃይሏን ተጠቅማ ውድቅ አድርጋለች።
“የተባበሩት መንግሥታት ችግር ሁለት ዓይነት መስፈርት መከተሉ ነው” ይላሉ የሂውማን ራይትስ ዋች አባሉ ሉዊ ቻርቦኖ።
“በሩሲያ ጉዳይ ሲሆን አሜሪካ የምታቀርባቸው ነገሮች ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተሉ ይሆናሉ፤ ነገር ግን እነዚህ ለእስራኤል አይሠሩም” ይላሉ።
“አሜሪካ ብቻ አይደለችም ሁለት ዓይነት መስፈርት የምትከተለው። ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ እያደረሰች ያለውን እያዩ ስለጋዛ ስታወራ መስማት በጣም ከባድ ነው።”

“ያረጀ እና ያፈጀ”
የካርኒጌ ዩሮፕ ቲንክ ታንክ ነባር ባልደረባ የሆኑት ሲናን ኡልጌን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አመሠራረት “ያረጀ እና ያፈጀ” ነፀብራቅ ነው።
“[በሁለተኛው የዓለም ጦርነት] ከ80 ዓታት በፊት በአሸናፊው ወገን የነበሩ አምስት አገራት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አላቸው። ከእነሱ ውጪ ማንኛውም አገር ይህ መብት የለውም።”
“ለምሳሌ አፍሪካ ከአምስቱ አገራት መካከል አንድም ተወካይ የላትም። በዓለማችን ብዙ ሕዝብ ካላቸው አገራት መካከል የሆነችው ሕንድ ቦታ የላትም። ላቲን አሜሪካ ተወካይ የላትም። አልፎም በአብዛኛው ሙስሊም ማኅበረሰብ ያለበት አንድም አገር የለም” ሲሉ ያክላሉ።
“ይህ አሁን ላለንበት ዓለም ጥያቄ በፍፁም መልስ ሊሆን አይችልም።”
ምሑሩ፤ የአውሮፓ ሕብረት አንድ ድምፅ ብቻ እንዲኖረው ማድረግ፤ የአምስቱን አገራት መብት መቃኘት፤ የአንድ አገር ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የሚገዳደር መንገድ ማቋቋም የሚሉ ሐሳቦች እንደ መፍትሔ ያቀርባሉ።
ነገር ግን የፀጥታው ምክር ቤት የበለጠ አካታች እና ተወካዮች የበዙበት ቢሆን እንኳ በአንዳንድ አገራት ጫና ሥር ከመውደቅ አያድነውም የሚል ሐሳብ አላቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አወቃቀርን ለማስተካከል የሚደረግ ማንኛውም ሐሳብ ከተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት በሁለት ሦስተኛው እና በሁሉም የፒ5 አገራት መፅደቅ አለበት።

እርዳታ አቅራቢ
ከጋዛ ጦርነት አስቀድሞም ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት የራሱ ችግሮች ነበረቡት የሚሉት ደግሞ የኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ በልደረባው ሪቻርድ ጎዋን ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት ባለፈው ዓመት ብቻ የፀጥታው ምከር ቤት በሱዳን ለተፈጠረ ጦርነት፣ ለኒጀር መፈንቅለ-መንግሥት ምላሽ መስጠት ተስኖታል፤ ሩሲያ እና ምዕራባውያን በዩክሬን ያሻቸውን ሲያደርጉም ምንም አላለም።
ቢሆንም ይላሉ ጎዋን የፀጥታው ምክር ቤት አሁንም ቢሆን እነ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ አንድ ላይ ሆነው ዓለም አቀፍ ውሳኔ የሚሰጡበት ነው።
ይህን የሚሉት የአፍጋኒስታንን ጉዳይ እንደምሳሌ በማንሳት ነው።
“አሜሪካ ከካቡል ስትለቅ፤ ምዕራባውያን ከአፍጋኒስታን ሲወጡ፤ እዚያ የቀሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት ናቸው። ትምህርት ቤቶችን በማስተዳደር እና ለሚሊዮኖች እርዳታ በማቅረብ የበኩላቸው አድርገዋል” ይላሉ።
“የተባበሩት መንግሥታት ከታሊባን ጋር ማውራት ባይችል ኖሮ አገሪቱ በድርቅ ምክንያት የማትወጣው ማጥ ውስጥ ትገባ ነበር” የሚል ሐሳባቸውንም ያቀርባሉ።
“በጋዛ፣ ሶሪያ እና በሌሎችም በርካታ አገራት አሁንም ምግብ እና መድኃኒት እያቀረቡ ያሉት የድርጀቱ ተቋማት ናቸው።”
የተባበሩት መንግሥታት የበርካታ ፈንዶች፣ ፕሮግራሞች እና ወኪሎች ውቅር ነው። ሁሉም ድርጅቶች የራሳቸውን ሥራ ያላቸው ሲሆን፣ የራሳቸው አስተዳደር እና በጀትም አላቸው።
የስደተኞች ጉዳይን የሚከታተለው ዩኤንኤችሲአር፣ የዓለም የምግብ ፕሮራግራም፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዩኤንዲፕ እና የዓለም የጤና ድርጅት ተጠቃሾች ናቸው።
ሁልጊዜ ስለፀጥታው ምክር ቤት ብቻ ነው የምናስበው የሚሉት ሉዊ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ሰውተው ለተባበሩት መንግሥታት እየሠሩ እንዳለ እንዘነጋለን የሚል ትችት አላቸው።
በጋዛ ጦርነት ከ100 በላይ ባልደረቦቹ ተገድለዋል። ይህ ድርጅቱ ከ78 ዓመታት በፊት ከተቋቋመ በኋላ እጅግ ትልቁ ቁጥር ነው።
አክለውም የተባበሩት መንግሥታት ምርመራ የሚያካሂድበት፣ ከባድ ወንጀል የፈጸሙ አገራት የሚቀጡበት፣ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮዎች የሚመሠረቱበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚመዘገቡበት አሠራር አለ ይላሉ።
ነገር ግን የፀጥታው ምክር ቤት ሁኔታዎች እንደከበዱት አይክዱም።
“ወደድንም ጠላንም የተባበሩት መንግሥት የ193 አገራት ውህድ ነው። የመሠረቱት አገራት ናቸው ሁሉንም ሊያስተካክሉ የሚችሉት።”
“ሩሲያ በዩክሬን የፈፀመችውን ወንጀል የምትሸፍንበት አሊያም ሶሪያን የምትከላከልበት፣ አሜሪካ ደግሞ እስራኤልን ከጫና የምትገላግለበት፣ ቻይና በበኩሏ ሰሜን ኮሪያን የምትደግፍበት ወይም በዜጎቿ ላይ የምታደርሰውን በደል የምትሸፋፍንበት ነው. . .
“ፍፁም የሆነ ቻርተር ያለው ፍፁም ድርጅት ማቋቋም ይቻላል። ነገር ግን አገራት ቃላቸውን መጠበቅ ካልቻሉ ምንም ዋጋ የለውም።”

መራር ትግል
በሚቀጥለው መስከረም የተባበሩት መንግሥታት ‘ሰሚት ኦፍ ዘ ፊውቸር’ ብሎ የጠራውን ስብሰባ ያካሂዳል።
ይህ ስብሰባ ለዓለም አቀፍ አስተዳደር አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች የሚቃኙበት እና መተማመን ተመልሶ እንዲሰፍን የሚሞከርበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሪቻርድ ጎዋን እንደሚሉት ይህ ስብበሳ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ መሣሪያ ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ስብሰባው ከአሜሪካ ምርጫ ሁትለ ወራት ቀድሞ እንደሚደረግ የሚጠፋቸው አይደለም።
“በ2025 ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሊወጡ እንደሚችሉ እያሰቡ፤ ዲፕሎማቶችን የተባበሩት መንግሥታት ለውጥ ያስፈልገዋል ብሎ ማሳመን ከባድ ነው” ይላሉ።
ፕሮፌሰር ጌርጌዝ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ጉልበት ሊያዳክም የሚችል ለውጥ እንድትቀበል ማድረግ መቻል የማይታሰብ ነው ባይ ናቸው።
“ይህ መራር ትግል ነው። አስር ዓመት ስለሚፈጅ ጉዳይ አይደለም እያወራን ያለነው። እያወራን ያለነው አስርታትን ስለሚፈጅ ለውጥ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ዓለም አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ያስፈልጋታል ባይ ናቸው።
“[የተባበሩት መንግሥታት ቢከስም] ትርፉ ቀውስ ነው። ወደ ጫካ ሕይወት ነው ተመልሰን የምንገባው” ይላሉ።