
ከ 4 ሰአት በፊት
በአላባማ የሞት ፍርድ የተላለፈበት እስረኛ ባለቀ ሰዓት ያስገባው ይግባኝ ተቀባይነት በማጣቱ በናይትሮጅን ጋዝ የሚገደል የመጀመሪያውን አሜሪካዊ ለመሆን ሰዓታት ቀርተውታል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የኬኔት ዩጂን ስሚዝ ጠበቆች ጨካኝ እና ያልተለመደ የሚሉትን የቅጣት መንገድ ለማስቀረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ለ15 ደቂቃ ያህል ናይትሮጅን በጭንብል ወደ ሰውነቱ እንዲገባ በማድረግ ግድያው ይፈጸማል።
የ58 ዓመቱ ስሚዝ እአአ በ1989 የሰባኪ ሚስት የነበረችውን ኤልዛቤት ሴኔትን በመግደል ወንጀል ነበር የተከሰሰው።
የአላባማው የሞት ፍርድ ዛሬ እንዲፈጸም ቀጠሮ ተይዟል።
እንደ ዴዝ ፔናሊቲ ኢንፎርሜሽን ሴንተር ከሆነ ስሚዝ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በዚህ ዘዴ የሚገደል የመጀመሪያው ሰው ይሆናል።
እአአ ከ1996 ጀምሮ በሞት ፍርድ ላይ የሚገኘው እስረኛ ጠበቆች ባለቀ ሰዓት ሌላ ይግባኝ ለአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እያቀረቡ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ስሚዝ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለቢቢሲ በጽሑፍ በሰተው ምላሽ ዕጣ ፈንታውን ለማወቅ መጠበቁ “ስቃይ” ሆኖበታል።
አላባማ ወንጀለኛውን ከሁለት ዓመት በፊት በገዳይ መርፌ ለመግደል ሞክራ ነበር።
- የአፍሪካ ቀንድ ትኩሳት፡ ቀውስ በማያጣው ቀጠና ያሉ አገራት ግንኙነትከ 6 ሰአት በፊት
- ዩናይትድ ኪንግደም የተዘረፉትን የጋና ‘የአክሊል ጌጣጌጦች’ በብድር ልትመልስ ነውከ 5 ሰአት በፊት
- የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ እና ዩክሬን ጉዳይ የሚወቀሰው ለምን ይሆን? ምንስ ማድረግ ይችላል?ከ 6 ሰአት በፊት

ስሚዝ የ45 ዓመቷን ሴኔትን አንድ ሺህ ዶላር ተከፍሏቸው ከገደሏት ሁለት ወንጀል ፈጻሚዎች መካከል አንዱ ነው።
ተደብድባ ደረቷ እና አንገቷ ላይ በጩቤ ተወግታ ህይወቷ አልፏል። ህይወቷ ያለፈው በቤት ዘረፋ ወቅት እንዲመስል ተሞክሮ ነበር።
በዕዳ የተዘፈቀውና ሰባኪ የነበረው ባለቤቷ የኢንሹራንስ ገንዘብ ለማግኘት ግድያውን ማስፈጸሙ ታውቋል። መርማሪዎች ሊደርሱበት መሆኑን ሲያውቅ ራሱን አጥፍቷል።
ከስሚዝ ጋር በተባባሪነት ወንጀሉን የፈጸመው ጆን ፎረስት ፓርከር በ2010 ተገድሏል።

ስሚዝ ተጎጂዋ ስትገደልል መገኘቱን ቢያምንም በጥቃቱ እንዳልተሳተፈ ለፍርድ ቤት ተናግሯል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ስሚዝን በጋዝ መግደል ማሰቃየት ወይም ሌላ ጭካኔ የተሞላበት ኢሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ በዚህ መንገድ የሚደረገው ግድያ እንዲቆም ጠይቋል።
የስሚዝ ጠበቆች በበኩላቸው ወንጀለኞችን በበርካታ የግድያ ዘዴ ለመግደል መሞከር “ከጨካኝ እና ያልተለመደ” ቅጣት የሚጠብቀውን የአሜሪካ ህገ መንግስት እንደሚጥስ በመግለጽ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከራክረዋል።
ረቡዕ ዕለት ዳኞቹ ይግባኙን ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ግድያውን ለማስቆም የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል። ፍርዱን በይፋ የተቃወመ አንድም ዳኛ የለም።
የአላባማ ናይትሮጅን ጋዝ ህጋዊነት በመቃወም ስሚዝም የራሱን ይግባን ለታችኛው ፍርድ ቤት አቅርቧል።
ፍርድ ቤት ረቡዕ አመሻሽ ላይ በሰጠው ብይን የእስረኛውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።
የስሚዝ ጠበቆች በድጋሚ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለይግባኝ እንደሚመለሱ ተናግረዋል።
የናይትሮጅን ጋዝ “በቅርቡ የተጀመረ እና ሙከራ ያልተደረገበት ነው” በማለት ከመከራከር ባለፈ ይህም በራሱ ትውከት የመታፈን አደጋ ያስከትልበታል ብለዋል።
የአላባማ ግዛት ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደገለጸው ከሆነ ስሚዝ ንቃተ ህሊናውን በሰከንዶች ውስጥ ስቶ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ድግሞ ይሞታል ብሎ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።
የግዛቱ አቃቤ ህግ ስቲቭ ማርሻል ከዚህ ቀደም “ምናልባትም እስካሁን ከተወሰዱት እጅግ ሰብዓዊነት የተሞላበት አፈጻፈም ነው” ብለውታል።
ለገዳይ መርፌዎች ጥቅም ላይ የሚውሉትን መድኃኒቶችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ አላባማ እና ሌሎች ሁለት የአሜሪካ ግዛቶች ናይትሮጅን ሃይፖክሲያን እንደ አማራጭ የግድያ ማስፈጸሚያ ዘዴ እንዲውል ፈቅደዋል።