
ከ 6 ሰአት በፊት
በዓለማችን መረጋጋታቸው በቀላሉ ሊናጋባቸው ከሚችሉ ቀጠናዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ ቀንድ መሆኑን ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው ተቋም ይገልጻል።
እንደ ተቋሙ ከሆነ መረጋጋት ከራቃቸው የዓለማችን ቀዳሚ አገራት መካከል አንዷ መገኛዋ የአፍሪካ ቀንድ የሆነችው ሶማሊያ ነች።
የአፍሪካ ቀንድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያልቁባቸውን ጦርነቶች የሚያስተናግድ ቀጠና ነው።
በዜጎች መብት ጥሰት ስማቸው በክፉ የሚነሱ አገራት መሪዎች መገኛ ከሆኑ አካባቢዎች መካከልም አንዱ የአፍሪካ ቀንድ ነው።
ይህ ቀጠና ውጥረት የማያጣው በአገራት ውስጣዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአገራቱ መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት መሻከር የሚፈጠርም ናቸው።
ኢትዮጵያ
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ከከጠፈው እና በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ካወደመው የእርስ በእርስ ጦርነት ያላገገመችው ኢትዮጵያ በቀጠናዊ ጉዳዮች ሌላ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።
የአዲስ አበባ የባሕር በር ፍላጎት ከሞቃዲሾ ጋር አጋጭቷታል። በሕዳሴ ግድብ ምክንያት የተቆጣችው ካይሮም ጠልቃ ለመግባት ዳር ዳር እያለች ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ አገር ነኝ ብላ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የመግባቢያ ሠነድ መፈራረሟ ይታወሳል።
አዲስ አበባ ለምታገኘው የባሕር ጠረፍ በምላሹ ለሐርጌሳ የአገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ተገልጧል።
ታዲያ ይህ ሶማሊያን አስቆጥቷል። የአገሪቱ መሪዎች ሉዓላዊነታችን ተጥሷል በማለት ዜጎችን ለጦርነት ተዘጋጁ እስከማለት ደርሰዋል።
ለበርካታ ዓመታት በእርስ በእስር ጦርነት ውስጥ የቆየችው እና በጽንፈኛ ቡድኖች ስትታመስ የኖረችው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ተጋርጦብኛል ላለችው “ወረራ” ድጋፍ ለማግነት ፊቷን በቀጠናው ወደሚገኙ አገራ አዙራለች።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰኝ ሼክ ሞሐሙድ ወደ አሥመራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር መክረዋል። ከዚያም በፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ ግብዣ ወደ ካይሮ ካቀኑ በኋላ ከግብፅ የጥበቃ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።
አል ሲሲ “ግብፅ የትኛውም አገር ሶማሊያንም ሆነ ደኅንነቷን ስጋት ውስጥ እንዲጥል አትፈቅድም” ካሉ በኋላ ሶማሊያ የግብፅን ድጋፍ ከጠየቀች ከጎኗ ለመቆም ዝግጁ ነች ሲሉ አል-ሲሲ ተደምጠዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በዐይነ ቁራኛ በሚተያዩት አገራት መካከልም ሌላ ፍጥጫን የሚፈጥር ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እና ግብፅ በተጨማሪ ከኤርትራ ጋርም በቅርብ ዓመታት አድሳው የነበረው ግንኙነቷ መሻከሩ ይነገራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ከመሻሻሉም በላይ አዲስ አበባ እና አሥመራ “የጋራ ጠላት” ያሉትን ህወሓትን ለመውጋት ብረት አንስተው እስከመዝመት ደርሰው ነበር።
ነገር ግን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ያበቃው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መካከል ያለው ወዳጅነት እንደቀደመው አይመስልም።
ምንም እንኳ የሁለቱን አገራት አሁናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚገልጽ ይፋዊ መግለጫዎች ባይኖሩም፤ በአሁኑ ወቅት ሁለቱም አገራት አዲስ አበባ እና አሥመራ ላይ አምባሳደሮች የሏቸውም።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ለመጨረሻ ጊዜ ለይፋዊ ጉብኝት ኢትዮጵያ የተገኙት የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመጀመሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ነው።
- ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ የተነሱ ውዝግቦች20 ጥር 2024
- ግብፅ ሶማሊያን እደግፋለሁ ማለቷን ተከትሎ ሶማሊላንድ ‘የውጭ ጣልቃ ገብነት’ እንደምትቃወም ገለጸች23 ጥር 2024
- የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ወታደራዊ አቅም ሲነጻጸር23 ጥር 2024

ሶማሊያ
በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ለሦስት አስርት ዓመታት የቆየችው፣ እስላማዊው ቡድን ጋር እየተዋጋች ያለችው እና ሰብዓዊ ቀውስ የማይለያት ሶማሊያ፤ ሰሞነኛው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት ሌላ ራስ ምታት ሆኖባታል።
የአል-ሸባብ እንቅስቃሴን በራሷ አቅም መግታት ተስኗት የጎረቤት አገራት ወታደሮችን ወደ ደንበሯ አዝልቃ ለማስገባት የተገደደች አገር መሪዎች፤ ስምምነቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት በኃይል ለመፍታት የጦርነት ቅስቀሳ ሲያደርጉ እየተሰሙ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ18.7 ሚሊዮን አጠቃላይ የሶማሊያ ሕዝብ 8.3 ሚሊዮን የሚሆኑት እርዳታ ጠባቂዎች ናቸው ይላል። ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 1.5 ሚሊዮን የሶማሊያ ታዳጊዎች ደግሞ የምግብ እጥረት ያለባቸው ናቸው።
ከሰብዓዊ ቀውስ እና የፀጥታ ችግር በተጨማሪ በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ቀዳሚ የሆነው የሶማሊላንድ ጉዳይ የአገሪቱን አንድነት የሚፈታተን ተደርጎ ይወሰዳል።
ታዲያ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችው ስምምነት እንደ አገር ከአዲስ አበባ እውቅና እንደሚያስገኝለት መገለጹ በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ሌላ ትኩሳት ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪ ሶማሊያ በደቡብ ምዕራብ በኩል ከምታዋስናት ኬንያ ጋር የሚያወዛግባት የባሕር አካል ይገባኛል ጉዳይ አልተቋጨም።
በተፈጥሮ ጋዝ እና ነዳጅ የበለጸገ ነው ተብሎ በሚታሰበው እና 100 ሺህ ሲኩዌር ኪሎ ሜትር በሚሰፋው የሕንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘው የውሃ አካል የይገባኛል ጭቅጭቅ የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አሻክሮ ቆይቷል።
ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት በአብዛኛው ለሶማሊያ ያደላ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ ኬንያ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጋ የሁለቱ አገራት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው።

ሱዳን
በአንድ ወቅት በኦማር አል በሽር ጠንከራ ክንድ ስር የነበረችው ሱዳን፤ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በነበረው የዳርፉር ጦርነት ስሟ በመጥፎ ቢነሳም አንጻራዊ መረጋጋት የነበራት አገር ነበረች።
አል-በሽር በሕዝባዊ አብዮት ከመንበራቸው ከወረዱ በኋላ አገሪቱ በሥልጣን ሹክቻ ተወጥራ ተይዛ ቆየች። ከዚያም የካርቱም እና ኦማድሩማን ጎዳናዎች የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት በሚጠይቁ ዜጎች ይጥለቀላቁ ጀመር።
ከአል-በሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ባሉት ዓመታት አለመረጋጋት፣ ፖለቲካዊ ውጥረት እና የኑሮ ውድነት ሕዝቡን ከማማራሩ ባሻገር ሚያዚያ 2016 ዓ.ም. አገሪቱ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገባች።
የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አበደል ፋታህ አል ቡሩሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) አገሪቱ እንዴት ትመራ በሚለው ላይ መግባባት ሳይችሉ ቀርተው ነው በሥልጣን ሽሚያ ወደለየለት ጦርነት የገቡት።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት አሃዝ ከሆነ ቀጥሎ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል። ከ13ሺህ የማያንሱ ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ተቀጥፏል።
ጄኔራል አል ቡርሃን እና ጄኔራል ሔሜቲ በቀጠናው ያሉ አገራት እና ድርጅቶች በጦርነቱ እጃቸውን እያስገቡ ነው ሲሉ ክስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የጄኔራል አል ቡርሃን ምክትል የሆኑት ጄኔራል ያሲር አል-አታ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ወታደራዊ ድጋፎችን በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በኡጋንዳ እና በቻድ በኩል አድርጋ ለሐምዳን ዳጋሎ ጦር እያደረሰች ነው ሲሉ ከሰው ነበር።
አረብ ኤሜሬቶች እና ኡጋንዳ ይህን ክስ አስተባብለው ነበር።
በቅርቡ ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ሁለቱ የጦር መሪዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡ አል-ቡርሃንን አስቆጥቷል።
አል-ቡርሃን በመሪዎች ስብሰባ ላይ ሔሜቲ ለምን ይጋበዛል በሚል ሱዳን እራሷን ከኢጋድ አባልነት አግልላለች።

ጂቡቲ
በአፍሪካ ቀንድ ትንሹ የቆዳ ስፋት ያላት አገር ጂቡቲ በስተሰሜን ከምታዋሰናት ኤርትራ ጋር በግዛት ይገባኛል ትወዛገባለች።
ቀይ ባሕር ላይ በሚገኙት ራስ ዱሜራ ተብሎ በሚጠራው ተራራ እና ዱሜራ በተባለ ደሴት ሁለቱ አገራት ሲካሰሱ ቆይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ እና ኤርትራ በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ በሚገኘው ሙሳ አሊ የተባለው ተራራማ ቦታ ሌላኛው የኤርትራ እና የጂቡቲ የውዝግብ ምንጭ ነው።
ሁለቱ አገራት የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት ዱሜራ የኳታር ጦር ሰፍሮ ነበር። ይሁን እንጂ ከሰባት ዓመታት ገደማ በፊት ዶሃ ከሳዑዲ መራሹ ኃይል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ጦሯን ከስፍራው ስታነሳ፣ በጂቡቲ እና በኤርትራ መካከል ውጥረት ነግሶ ነበር።
በወቅቱ ጂቡቲ የኳታር ጦር ቦታውን መልቀቁን ተከትሎ ኤርትራ ወታደሮቿን ቦታው ላይ አስፍራለች በሚል ክስ አቅርባ ነበር።
በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ጦር ቦታው ላይ የሚገኝ ሲሆን ሁለቱ አገራት እአአ 2018 ላይ የሻከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ቢስማሙም በግዛት ይገባኛል ጉዳያቸው እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።

ደቡብ ሱዳን
ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር ከመሆኗ በፊት በአብዛኛው አረብ-ሙስሊም በሆኑት ሰሜን ሱዳናዎች እና አብዛኞቹ ክርስቲያን በሆኑት ደቡቦች መካከል ለረዥም ዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል።
እአአ 2005 ላይ ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ብታገኝም በካርቱም እና ጁባ መካከል ያለው ግንኙነት ሁሌም የሰመረ አልነበረም።
በሁለቱ አገራት መካከል የውዝግብ ምንጭ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል የግዛት ይገባኛል ጥያቄ እና የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ኪራይ እና ክፍያ ተጠቃሽ ናቸው።
ወደብ አልባዋ ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የነዳጅ ሃብት አላት። ታዲያ ነዳጇን ለገበያ የምታቀርበው በሱዳን በኩል ወደ ቀይ ባሕር በተዘረጋው የነዳጅ ቱቦ አማካይነት ነው።
ሱዳን በግዛቷ በቱቦ ለሚያልፈው ነዳጅ ደቡብ ሱዳን ከምታገኛው ትልቁን ድርሻ መጠየቋ ጁባን የሚጎረብጥ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
አሁን ላይ ደግሞ በሱዳን ያለውን ጦርነት ተከትሎ ከአገሪቱ ጦር ጋር እየተዋጋ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተቆጣጥሮ በያዛቸው አካባቢዎች ለተዘረጋው ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የትራንዚት ክፍያ የደቡብ ሱደን መንግሥት የማይፈጽምለት ከሆነ የነዳጅ ፍሰቱን እንደሚያቋርጥ ዝቷል።
በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገችው የአቢዬ ግዛት ሌላኛዋ የሁለቱ አገራት የውዝግብ ምንጭ ሆና ቀጥላለች።
ደም አፋሳሽ የሆነ የግጭት ታሪክ ያላቸው ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር ከአንድ ዓመት ባነስ ጊዜ ውስጥ ለማድረግ በታቀደው ምርጫ ምክንያት በክፉ ዐይን መተያየት ጀምረዋል።
ፕሬዝዳንት ኪር በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው እንደሚወዳደሩ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ምክትላቸው ሪክ ማቻር ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ምርጫ እንዲያስፈጽሙ የሾሟቸው የምርጫ ኮሚሽን አባላት የፕሬዝዳንቱ ወዳጆች ናቸው ይላሉ።
ከፖለቲካዊ ውጥረት በተጨማሪ በሱዳን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ አለ። 11 ሚሊዮን ከሚገመተው አጠቃላይ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ 9.5 ሚሊዮን የሚሆነው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሃዝ ያሳያል።

ኤርትራ
ኤርትራ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ከኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ጋር አዎንታዊ የሚባል ግንኙነት የላትም።
ከዚህ በተጨማሪም ከ25 ዓመታት ገደማ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ላስገባት የድንበር ግጭት የተደረሰው የልጀርስ ስምምነተ እስካሁን ተፈጻሚ አልሆነም።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጠንካራ ክንድ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሲመሯት በቆዩት ኤርትራ ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ለውጥ ተመዝግቦ አያውቅም።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት በሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ዜጎችን ጨቁኖ በመያዝ ክስ ይቀርብበታል።
ኤርትራ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ወጣቶቿ ማብቂያ የሌለውን አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎትን በመሸሽ እና የተሻለ ሕይወትን ፈለጋ ጥለዋት የሚሰደዱባት አገር ሆናለች።
በተጨማሪም በአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እና ተቋማት ላይ በአሜሪካ መንግሥት ማዕቀብ ተጥሎባት የምትገኝ አገር ነች።