
ከ 1 ሰአት በፊት
የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌናሌና ቤርቦክ ወደ ጂቡቲ ለሚያደርጉት ጉብኝት በኤርትራ የአየር ክልል በኩል ለማለፍ የሚያስችል ፈቃድ ባለማግኘታቸው ወደ ሳዑዲ ለማቅናት መገደዳቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የጀርመኑ ዲደብሊው እንደዘገበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከዕቅዳቸው ውጪ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማቅናት የተገደዱት ወደ ጂቡቲ በሚያደርጉት ጉዞ በኤርትራ በኩል ለማለፍ አውሮፕላናቸው የሚያስፈልገው ፈቃድ በመከልከሉ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ለሦስት ቀናት በሦስት የአፍሪካ አገራት ጉብኝት ለማድረግ በመነሳት በቀዳሚነት ወደ ጂቡቲ አቅንተው በሱዳን ውስጥ ስላለው ጦርነት እና በቀይ ባሕር ላይ ስላጋጠመው የደኅንነት ችግር ለመወያየት አቅደው ነበር።
ሚኒስትሯ ጉዟቸው ከተስተጓጎለ በኋላ ባወጡት መግለጫ የጉዞ አቅጣጫቸው መቀየሩ በአጠቃላይ በቀጠናው ላይ ያለው አለመረጋጋት ነጸብራቅ መሆኑን በማመልከት፣ ሱዳን እና የመን ውስጥ ያለው ግጭት የአየር ክልላቸውን ለመጠቀም አለማስቻሉን ገልጸዋል።
ቤርቦክ ወደ ጂቡቲ በሚያደርጉት ጉብኝት ጀርመን እና የአውሮፓ ኅብረት በቀይ ባሕር ላይ ያለውን የመርከቦች ጉዞ መስመር በየመን ካሉት ሁቲ ታጣቂዎች ለመጠበቅ እየሠሩ መሆናቸውን መልዕክት ለማስተላለፍ አቅደዋል።
- የአፍሪካ ቀንድ ትኩሳት፡ ቀውስ በማያጣው ቀጠና ያሉ አገራት ግንኙነትከ 6 ሰአት በፊት
- ቀይ ባሕርን ያወከውን የሁቲዎች ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ይሳካ ይሆን?23 ጥር 2024
- አሜሪካ እና ዩኬ በሁቲዎች ላይ አዲስ ጥቃት ከፈቱ23 ጥር 2024
እስራኤል በጋዛ ላይ ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደች መሆኑን ተከትሎ በኢራን የሚደገፉት ሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚቀዝፉ የምዕራባውያን ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
ሁቲዎች እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ ትፈጽመዋለች ያሉትን በደል በመቃወም በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ የጭነት መርከቦች ላይ በድሮን እና በሚሳኤሎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ጉዳት አድርሰዋል።
በደኅንነት ስጋት ሳቢያ የዓለማችን ግዙፍ የጭነት መርከብ ኩባንያዎች መርከቦቻቸው በቀይ ባሕር በኩል እንዳያልፉ አግደዋል።
ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የፈጠሩት የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ እንቅፋት ለመግታት በሚል አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ባለፉት ቀናት የመን የባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኙ የታጣቂ ቡድኑ ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባን ፈጽመዋል።
ቤርቦክ በምሥራቅ አፍሪካ በሚያደርጉት ጉብኝት አንድ ዓመት ሊሞላው ስለተቃረበው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከአካባቢው አገራት ባለሥልጣናት ጋር ይመክራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከጂቡቲ በተጨማሪ ወደ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን የመጓዝ ዕቅድ አላቸው።
ትናንት ረቡዕ ወደ ጂቡቲ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ በኤርትራ የአየር ክልል ለማቋረጥ ፈቃድ ባለማግኘታቸው አቅጣጫ እንዲቀይሩ የተደረጉት ሚኒስትሯ፣ ዛሬ ሐሙስ ወደ ጂቡቲ ያቀናሉ ተብሏል።
የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንን አሳፍሮ ሲጓዝ ለነበረው አውሮፕላን በአየር ክልሏ ውስጥ ለማቋረጥ ፈቃድ መከልከሉን በተመለከተ በኤርትራ በኩል የተባለ ነገር የለም።
የአውሮፕላኑ አብራሪ እንዳለው “በኤርትራ የአየር ክልል በኩል ለማለፍ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ብናደርግም ሰቃይፈቀድልን ቀርቷል” በማለት ተናግሯል።
አውሮፕላኖች በጉዞ ላይ እያሉ በአገራት የአየር ክልል ውስጥ ለማቋረጥ የሚያስችላቸውን ፈቃድ ማግኘት የተለመደ መሆኑን የጠቀሰው ዲደብሊው፣ ለሚኒስትሯ አውሮፕላን ፈቃድ አለመሰጠቱን እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሊረዳቸው እንዳልቻለ ተገልጿል።