
ከ 2 ሰአት በፊት
“ጃፓናዊት እንደሆንኩ ለመቀበል ብዙዎች ይቸግራቸው ነበር።”
ይህ ካሮሊና ሺኖ ‘ሚስ ጃፓን’ ተብላ ዘውድ ስትደፋ እንባ እየተናነቃት የተናገረችው ነው።
የ26 ዓመቷ ሞዴል ዩክሬን ተወለደች፤ ከዚያም በአምስት ዓመቷ ወደ ጃፓን አቅንታ ናጎያ ከተማ አደገች።
ጃፓን ብዙ ዓመታት በመኖሯ ዜግነት ያገኘችው ካሮሊና ጃፓናዊ ደም የሌላት የመጀመሪያዋ የውድድሩ አሸናፊ ሆናለች።
ነገር ግን የእሷን ማሸነፍ ተከትሎ ጃፓናዊ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው ጥያቄ እንደ አዲስ ተቀስቅሷል።
አንዳንዶቹ የእሷ ማሸነፍ “የደረስንበትን ዘመን” ያሳያሉ የሚሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ‘ሚስ ጃፓን’ የሚያስብል ነገር የላትም የሚል ሐሳባቸውን እየሰጡ ነው።
አሪያና ሚያሞቶ ከ10 ዓመታት በፊት የአሸናፊነት ዘውዱን ስትደፋ የመጀመሪያዋ ግማሽ ጃፓናዊት ነበረች።
በአውሮፓውያኑ 2015 ‘ሚስ ጃፓን’ ተብላ የተመረጠችው ከጃፓናዊት እናት እና ከጥቁር አሜሪካዊ አባት የተወለደችው አሪያና፤ በወቅቱ ውድድሩን ስታሸንፍ ግማሽ ጃፓናውያን መወዳደር አለባቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
- አሜሪካዊው ወንጀለኛ በናይትሮጅን የሞት ቅጣት የሚቀጣ የመጀመሪያው ሰው ሊሆን ነውከ 4 ሰአት በፊት
- ዩናይትድ ኪንግደም የተዘረፉትን የጋና ‘የአክሊል ጌጣጌጦች’ በብድር ልትመልስ ነውከ 5 ሰአት በፊት
- ዶናልድ ትራምፕ በኒው ሐምፕሻየር ግዛት ድል ቀናቸው24 ጥር 2024
ዘንድሮ ጃፓናዊ ካልሆኑ ወላጆች የተወለደችው ካሮሊና ዘውዱን መድፋቷ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችን አስቆጥቷል።
“ሚስ ጃፓን ተብላ የተመረጠችው ግለሰብ ከጃፓናዊ ጋር እንኳ አልተደባለቀችም። መቶ በመቶ ዩክሬናዊት ናት። ቆንጆ መሆኗን አልክድም፤ ግን ይህ ‘ሚስ ጃፓን’ ነው። ጃፓናዊነቷ የታለ?” የሚል ጥያቄ ኤክስ ላይ ተለጥፏል።
“ግማሽ [ጃፓናዊት] ብትሆን ችግር አልነበረውም። ነገር ግን ምንም የጃፓን ዘር የለባትም። የተወለደችውም ጃፓን ውስጥ አይደለም ” የሚል ሌላ መልዕክትም በቀድሞው ትዊተር ላይ ተለጥፎ ታይቷል።
ሌሎች ደግሞ ካሮሊና አሸናፊ ተብላ መመረጧ “የተሳሳተ መልዕክት” ነው የሚያስተላልፈው የሚል ስጋት አላቸው።
“እኔ እንደሚመስለኝ አውሮፓዊ የምትመስል ሴት በጃፓን እጅግ ቆንጆዋ ተብላ መመረጧ ለጃፓን ሕዝብ የተሳሳተ መልዕክት ማስተላላፍ ነው።”
ሌሎች ደግሞ ዩክሬናዊቷ አሸናፊ ሆና የተመረጠችው በፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ይሆን ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።
“ሩሲያዊት ብትሆን ኖሮ አታሸንፍም ነበር። በተዓምር። እንደምናየው ዘንድሮ መስፈርቱ ፖለቲካዊ ነው። ይህ ለጃፓን አሳዛኝ ክስተት ነው” ብሏል ሌላ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ።
አይ ዋዳ ከሚስ ጃፓን አዘጋጆች መካከል አንዷ ናት፤ የውድድሩ ዳኞች ካሮሊናን አሸናፊ አድርገው የመረጡት “በልበ-ሙሉነት ነው” ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
“ጃፓንኛ ትናገራለች። ትጽፋለች። ትሁት ናት። ከእኛ በላይ ጃፓናዊት ናት” ትላለች ዋዳ።
ካሮሊና ባፈለው ዓመት የጃፓን ዜግነት ካገኘች በኋላ በኢንስታግራም ገጿ ባስተላለፈችው መልዕክት “ጃፓናዊ ባልመስልም እዚህ በማደጌ አስተሳሰቤ ጃፓናዊ ነው” ስትል መልዕክት አስፍራ ነበር።