ሳዲ

28 ጥር 2024, 08:08 EAT

በመላው ዓለም ታዳጊዎች የውበት መጠበቂያ ምርቶች የመጠቀም ልማድ መስፋፋት ልጆችን ሊድን ለማይችል የቆዳ በሽታ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል የብሪታኒያ የቆዳ ሐኪሞች ማኅበር አስጠነቀቀ።

ታዳጊዎች በቲክቶክ እና ዩቲዩብ ላይ የሚከተሏቸው ተጽእኖ ፈጣሪዎች አልያም ወላጆቻቸው የሚጠቀሟቸውን የቆዳ ማስዋቢያ ምርቶች እንዲገዙላቸው ይጠይቃሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ለአዋቂዎች ተብለው የሚዘጋጁት ምርቶች የሕጻት ቆዳን በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉ እንደ ኤክስፎሊአቲንግ አሲድ በውስጣቸው ይዘዋል።

ይህ አሲድ የአዋቂዎችን ቆዳ ለስላሳ ለማድረግ፣ ቆዳ ላይ ያሉ ምልክቶችን ለማጥፋት እና ቆዳ ፈካ ብሎ እንዲታይ ያደርጋል።

ታዲያ ይህ ዓይነት ንጥረ ነገር ያለው ምርትን ታዳጊዎች ቢጠቀሙት የሰውነት ቆዳ መቆጣትን ወይም ኤክዜማ የተባለ የቆዳ በሽታን ሊያስከትልባቸው ይችላል።

ኤክዜማ በሽታ ቆዳን በጣም በማድረቅ እና በማሳሳት እያሳከከ ሽፍታን እና ቁስልን የሚፈጥር ነው።

የስምንት ዓመቷ ሳዲ ስለ ውበት መጠበቂያ ምርቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተችው ቲክቶክ ላይ ነው። ታዳጊዋ ቲክቶክ ላይ የምትከተላቸው ተጽእኖ ፈጣሪዎች ምርቶቹ “ቆዳን እንዴት ውብ እንደሚያደርጉ ያወራሉ” ትላለች።

ይህች ታዳጊ ባብል የሚባል ኩባንያ የሚያመርተውን የውበት መጠበቂያ ምርትን ለመሞከር በእጅጉ ከመጓጓቷ የተነሳ፣ “ወደታች ስትገፊው የአበባ ቀርጽ ይዞ ይከፈታል” ስትል ምን ያህል እንደማረካት ትናገራለች።

ሳዲ ሌላ የወደደችው ምርት ድራንክ ኤሌፋንት የተባለ ኩባንያ የሚያመርተው የቆዳ ድርቀትን የሚከላከል ቅባትን ነው። ሳዲ ይህን ምርት ለመጠቀም የፈለገችው “አስተሻሸጉ በጣም ስለሚያምር ነው” ትላለች።

በርካታ ወላጆች ቲክቶክ ላይ ባሉ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ምክንያት ልጆቻቸው የውበት መጠበቂያ ምርት እንዲገዛላቸው እንደሚጠይቋቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቲክቶክ ላይ በስፋት ከሚተዋወቁት ምርቶች መካከል የድራንክ ኤሌፋንት ውጤቶች ይገኙበታል። ይህ ኩባንያ በውድ ዋጋ የሚሸጣቸው ምርቶች ኤክፎሊአተር አሲድ ይዘዋል።

የውበት መጠበቂያ ምርቶች ማስታወቂያ ወይም ስለ ምርቶቹ ማውራት በቲክቶክ የተከለከለ አይደለም።

ተጽእኖ ፈጣሪዎች ‘ለዕለት ውሎዬ ስዘጋጅ ተመልከቱኝ’ አልያም ደግሞ ‘የዕለት ውሎ’ የሚል ይዘት ባላቸው ቪዲዮቻቸው ከቤት ከመውጣታቸው በፊት ሲቀባቡ እና ሲዘገጃጁ ይታያሉ።

የድራክ ኤሌፋንት መሥራች የሆነችው ቲፋኒ ማስተርሰን “ልጆች አሲድ የያዙ ምርቶቻችንን አትጠቀሙ። የእናንተ ቆዳ ለዚህ ደረጃ አልደረሰም” በማለት በማኅበራዊ ድረ-ገጿ ላይ ጥሪ እስከማስተላለፍ ደርሳለች።

የስምንት ዓመቷ ሳዲ ግን ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ማሳሰቢያዎች ቁብ አትሰጥም። ጓደኞቿ ያሏቸው የውበት መጠበቂያ ምርቶች እንዲገዙላት እናቷን ደጋግማ ትወተውታለች።

ሳዲ እና ሉሲ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሳዲ እና ሉሲ ከቢቢሲ ጋዜጠኛ ጋር

እናቷ ሉሲ አልገዛም በማለቷ ሳዲ ሌሎች የቤተሰብ አባላት የፈለገችውን ቅባት እንዲገዙላት አስደርጋለች።

ሳዲ የተገዛላትን ምርት ከተጠቀመች በኋላ ቆዳዋ ቀይ ሆኗል፤ እንዲሁም አሳክኳታል።

መግዛት ያልቻሉ ታዳጊዎች ደግሞ በኮስሞቲክስ ሱቆች ውስጥ እየገቡ ለመሞከሪያ ተብለው የሚቀመጡ ምርቶችን ከአግባብ ውጪ እንደሚጠቀሙ ሲፎራ የተባለው ኩባንያ ሠራተኞች ለቢቢሲ ይናገራሉ።

“ሳዲ የመዋቢያ ምርቶችን መቀባበት ትወዳለች። ጓደኞቿ እያደረጉት እሷ ከተከለከለች ቅር ይላታል” በማለት ሉሲ ትናገራለች።

ሉሲ እርሷም ብዙ የመዋቢያ ምርቶችን እንደምትጠቀም ብትናገረም ልጇ ሳዲ እንዲገዙላት ከምትጠይቃቸው ምርቶች መካከል ስማቸውን እንኳ ሰምታ የማታውቃቸው አሉ ትላለች።

ሉሲ ልጇ ቲክቶክ እንዳትጠቀም ብታግዳትም፤ ሳዲ የምትከተላቸው ተጽእኖ ፈጣሪዎች ዩቲዩብ ላይ በቀላሉ ይገኛሉ።

“ከማንም በላይ የምታምናቸው ተጽእኖ ፈጣሪዎች እያሉ ስለ የውበት መጠበቂያ ምርቶች የምነግራትን በጭራሽ አትቀበለም።”

አንዳንድ ምርቶች ማሸጊያዎቻቸው ባለቀለም እና ብሩህ በመሆናቸው የልጆችን ቀልብ ይስባሉ።
የምስሉ መግለጫ,አንዳንድ ምርቶች ማሸጊያዎቻቸው ባለቀለም እና ደማቅ በመሆናቸው የልጆችን ቀልብ ይስባሉ

የልጆች የቆዳ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ቴስ ማክፒርሰን ልጆች ስለ የቆዳ ውበት አጠባብቅ “ትክከለኛ መረጃ እንጂ የተሳሳተ መረጃ” ማግኘት የለባቸውም ይላሉ።

ልጆች ሊሞክሯቸው የሚፈልጓቸው ምርቶች አብዛኛዎቹ የተሸበሸበ ቆዳን ወጣት ለማስመሰል ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው ይላሉ ዶ/ር ማክፒርሰን።

ምርቶቹ “በዕድሜ ለገፋ ቆዳ ተስማሚ ሊሆኑ ይችላሉ – ለልጆች ቆዳ ግን ፈጽሞ ተስማሚ አይደሉም። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ባለ ሰው ላይ የቆዳ መቆጣት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በልጆች ላይ ግን ችግሩ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

የቆዳ ሐኪሟ ጨምረው ሲናገሩ፤ “ቀድሞውኑ ኤግዜማ ባለባቸው ወይም በቀላሉ ተጋላጭ የሆነ ቆዳ ባላቸው ልጆች ላይ ከባድ የሆነ ችግር ሊያስከትል ይችላል።”

የብሪቲሽ የቆዳ ሐኪሞች ማኅበር ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ማክፒርሰን፣ ለአዋቂ ተብለው የሚዘጋጁ ምርቶች ማሸጊያዎች ባለ ቀለም እና ብሩህ መሆናቸው የልጆች ትኩረትን እንዲስቡ አድርጓልም ይላሉ።