ቪክተር ኦሲምሄን

28 ጥር 2024, 09:18 EAT

በአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ በአዴሞላ ሉክማን ሁለት ጎሎች ካሜሩንን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜው ተሸጋገረች።

ደካማ የሚባል አቋም ያሳየችው ካሜሩን ሻንጣዋን ልትሸክፍ ግድ ሆኗል።

የጣሊያኑ አታላንታ አጥቂ ለአጋማሽ ዘጠኝ ደቂቃዎች ሲቀሩት ባስቆጠራት ጎል ሀገሩን ቀዳሚ አድርጓል።

ሉክማን ከናፖሊው አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን ያገኘውን ኳስ ኦናናን ተክቶ የተሰለፈው ግብ ጠባቂው ፋብሪስ ኦንደዋን ተሻግሮ አስቆጥሯል።

የቀድሞው ከ21 ዓመት በታች የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የነበረው ሉክማን ሁለተኛዋን ጎሎ በ90ኛው ደቂቃ በማስቆጠር የካሜሩንን ልብ ሰብሯል።

ምንም እንኳ በጉዳት ምክንያት ሳይሰለፍ የቆየው የካሜሩኑ አጥቂ ቪንሴንት አቡበከር ዘግይቶ ወደ ሜዳ ቢገባም ሀገሩ አንድ ዒላማውን የጠበቀ ኳስ ሳታስመዘግብ ወጥታለች።

አቡበከር ባለፈው ካሜሩን ባዘጋጀችው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበር።

በዓለም ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ ያልቻለው የካሜሩኑ አሠልጣኝ ሪጎቤርት ሶንግ ጫናው እየበረታ መጥቷል።

የካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሳሙዔል ኤቶ ጨዋታውን በሥፍራው ተገኝቶ የተከታተለ ሲሆን የቀድሞ የቡድን አጋሩን ሥራ የመታደግ አሊያም የማባረር ኃላፊነት አለበት።

በዘንድሮው ውድድር እምብዛም አስደናቂ ብቃት ያላሳዩት የማይበገሩት አናብስት ከናይጄሪያ በነበራቸውም ጨዋታው ከቅርፅ ውጭ ሆነው ተስተውለዋል።

በተቃራኒው ናይጄሪያ ያገኘችው ውጤት የሚገባት የሚያስብል ሲሆን ተጋጣሚዋን በልጣ ታይታለች።

በዘጠነኛው ደቂቃ የናይጄሪያው ተከላካይ ሴሚ አጃይ ያስቆጠራት ጎል በቪኤአር ታይታ ውድቅ ሆናበታለች።

የካሜሩንን የመጀመሪያ ጨዋታ ለማንቸስተር ዩናይትድ ለመጫወት ሲል የቀጣው ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና ለቀሪዎቹ ጨዋታዎች በግል አውሮፕላን ወደ አይቮሪ ኮስት ቢበርም መሰለፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው።

እሱን ተክቶ የተሰለፈው ኦንዶዋ ስኅተት በፈፀመ ቁጥር ካሜራው ኦናናን ሲያስመልክት ተስተውሏል።

በሌላ ጨዋታ አንጎላ ሁለት ተጫዋች በቀይ ያጣችውን ናሚቢያን 3 ለምንም በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅላለች።

የናሚቢያው ግብ ጠባቂ ኔብሉ በ17ኛው ደቂቃ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ጌልሰን ዳላ ከ9 ደቂቃ በኋላ ለአንጎላ ጎል ካስቆጠረ በኋላ የናሚቢያው ተከላካይ ሉቤኒ ሃውኮንጎ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተባሯል።

ዳላ ለራሱ እና ለሀገሩ ሁለተኛዋን ጎል ሲያስቆጥር ማቡሉሉ ደግሞ በአስደናቂ ሁኔታ ሶስተኛዋን በማከል አንጎላ ሩብ ፍፃሜውን እንድትቀላቀል አስችለዋል።

አንጎላ በመጪው አርብ በሩብ ፍፃሜው ናይጄሪያን ትገጥማለች።