የምጽአት ቀን ሰዓት

28 ጥር 2024, 08:07 EAT

ስለ ምጽአት ቀን ሰዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በ1990ዎቹ አጋማሽ ነው። አስተማሪዬ ናት ስለ ምጽአት ቀን ሰዓት የነገረችኝ።

አስተማሪያችን ክፍሉን ለሞላነው ተማሪዎች ጉዳዩን ስታስረዳ ፊቷ ላይ በሚነበብ መመሰጥ ነበር።

ከዚህ ቀደም የሆኑ ነገሮች ሁሉ በአንድ ዓመት ይታጨቃሉ አለችን። ግራ መጋባት ፊታችንን ላይ ጎልቶ ቢታይ የሚገርም አይሆንም።

ሕይወት የጀመረችው መጋቢት አካባቢ ነው፤ ዳይኖሰሮች ደግሞ በታኅሣሥ መጨረሻ ተቀላቀሉ፤ በስተመጨረሻ የሰው ልጅ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ምሽት 5፡30 መጣ።

አስተማሪያችን ቀጠለች። ጥልቅ ከሆነው የሰው ልጅ ታሪክ እየጨለፈች ምን ያህል እዚህች ምድር ላይ የምንቆይበት ጊዜ አጭር እንደሆነ ልታስረዳን ሞከረች።

ቀጥላ የተወሰኑ አሜሪካውያን ሳይንቲስቶች እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ያለን ጊዜ እጅግ አጭር ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረዳችን።

አንድ ቀን ይህንን ጉዳይ እንደ ሥራ ይዤ ደፋ ቀና እላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም።

እነሆ ዛሬ በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ኦፍ ኤክዚዝቴንሻል ሪስክ ማዕከል አጥኚ ሆኜ እየሠራሁ ነው።

ለዘመናት አስብ የነበረው የምጽአት ቀን ይህችን ዓለም እስክንሰናበት ያለውን ጊዜ መቁጠሪያ እንደሆነ ነበር። ግን እውነታው ወዲህ ነው።

ለዕኩለ ሌሊት 90 ሰከንዶች ሲቀሩ

የምጽአት ቀን ሰዓትን የሚቆጥሩ ሳይንቲስቶች በየዓመቱ ምን ያህል ወደ መዳረሻችን እየቀረብን እንደሆነ የሚያሳይ ምስል ያወጣሉ።

እንሆ በ2024 ለ76ኛ ጊዜ ይህን አድርገዋል። ደግሞም በየዓመቱ ወደ ዓለም ፍጻሜ የሚያቀርበንን ምክንያት ይመርቁበታል።

ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች በሉት፣ በተፈጥሮ አካባቢያችን ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ አሊያም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ብቻ የተለያዩ ምክንያቶችን ይደረድራሉ።

የአቶሚክ ሳይንቲስቶች ቡሌቲን የተሰኘው መፅሔት ፕሬዝዳንት የነበሩት ሪቻርድ ብሮንሰን ዕኩለ ሌሊት ልንደርስ 100 ሰከንድ ነው የቀረን ሲሉ አውጀው ነበር።

ሰዓቱ በአውሮፓውያኑ 2021 እና 2022 እዚያ ከቆየ በኋላ በ2023 ደግሞ በአስር ሰከንድ ቀንሷል። በያዝነው የአውሮፓውያኑ 2024 እዚያው ቁጭ እንዳለ ነው።

ይህ ምን ማለት ነው? ይህን ለመረዳት መጀመሪያ ሰዓቱ ከየት እንደመጣ፣ ታሪኩ ምን እንደሆነ፣ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ አለብዎ።

የምጽአት ቀን ሰዓት በተለያዩ ዘመናት

ኑክሌር ቦምብ

የኑክሌር ጦር መሣሪያ ተሠርቶ የተጠናቀቀበት ፍጥነት አይደለም ለተመልካች ለፈጣሪዎቹም እጅግ አስገራሚ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1939 አልበርት አይንስታይን እና ሊዮ ስዚላርድ አንድ ደብዳቤ ለወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ፃፉ።

በደብዳቤያቸው እጅግ ኃይለኛ ስለሆነው የኑክሌር ጦር መሣሪያ አብራሩ።

ይህ መሣሪያ እጅግ ኃይለኛ መሆኑን ለመግለጽ “አንድ የባሕር ዳርቻ ላይ ብናፈነዳው መላውን ጠረፍ ከመጠራረግ አይመለስም” ሲሉ ፕሬዝዳንቱን ተማፀኑ።

ይህ ደብዳቤ ነው ሳይንሳዊ፣ ወታደራዊ እና ኢንዱስትሪ መር መላዎች ተጣምረው የማንሀተን ፕሮጀክት እንዲወለድ ምክንያት የሆነው።

ይህ ፕሮጀክት በስድስት ዓመቱ አይንስታይን እና ሊዮ ከገመቱት በላይ አጅግ አደገኛ የሆነውን ቦምብ ፈጠረ።

ይህ ቦምብ እነ አይንስታይን እንዳሉት አንድ የባሕር ዳርቻን የሚደምስስ ሳይሆን፣ አንድ ከተማ እና ሕዝቧን ከምደረ-ገጽ የሚያጠፋ ሆኖ ተገኘ።

ይህ ቦምብ ከመፈጠሩ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ዘመናዊውን ዓለም ጠራርገው ሊያጠፉ የሚችሉ ኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ።

የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ለሰው ልጅ ኅልውና አደጋ ናቸው የሚለው ስጋት የመጣው የመጀመሪያውን የኑክሌር ቦምብ ከሠሩ ሳይንቲስቶች አንደበት ነው።

እኒህ ሳይንቲስቶች ቦምቡ የምድራችንን ከባቢ አየር ፈንቅሎ እንዲወጣ በማድረግ ከምድረ-ገጽ ያጠፋናል የሚል ስጋት ነበራቸው።

ይህ ስጋታቸው ሰሚ ጆሮ ባያገኝም እንደመታደል ሆኖ ፅንሰ-ሐሳባቸው ውሃ የሚያነሳ አልነበረም።

ያም ሆነ ይህ በማንሀተን ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉ ምሑራን ስላመረቱት ቦምብ ያላቸው አስተሳሰብ ቀና አልነበረም።

በ1942 በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ይህን ቦምብ መሥራት ይቻል እንደሆነ በላቦራቶሪ ሞክረው የተሳካላቸው ሳይንቲስቶች ሎስ አልሞስ በረሃ መንግሥት ወዳዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲያቀኑ ተደረጉ።

የተወሰኑ ሳይንቲስቶች ወደፊት የኑክሌር ቴክሎጂ ጫፍ ደርሶ ለሰው ልጆች ኅልውና አደጋ እንዳይሆን ለማድረግ ይንቀሳቀሱ ጀመር። ነገር ግን በጊዜው የነበረው መንግሥት ጆሮ ነሳቸው።

እኒህ ሳይንቲስቶች ናቸው የቺካጎ ሳይንቲስቶች ቡሌቲን የተሰኘው መፅሔት የጀመሩት። የመጀመሪያው ዕትም ለንባብ የበቃው ሂሮሽማ እና ናጋሳኪ በአቶሚክ ቦምብ ዶግ አመድ ከሆኑ ከአራት ወራት በኋላ ነው።

የዓለም አቀፍ ሕግ አዋቂዎች፣ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች፣ ሌሎች ባለሙያዎች ተባብረው ዓለም አቀፍ የዜጎች እና ሳይንቲስቶች ንቅናቄ ጀመሩ።

‘ኑክሌር ታቡ’ ወይም ደግሞ የኒውክሌር ጦርነትን ነውረኛ እንዲሆን የማድረግ ጥበብ አንዱ መስክ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ሞራል አልባ የመባል አደጋ” ኑክሌር እንዳንጠቀም አድርጎናል ብለው ሲያማርሩ ተሰምተዋል።

ሕትመቱ መጀመሪያ ሲጀመር እንደ አዋጅ ዓይነት ቅርፅ ነበር። ከአራት ዓመት በኋላ ግን ወደ መፅሔት ቅርፅ ራሱን ቀይሮ ሰፊ ታዳሚ ለመድረስ መትጋት ጀመረ።

ይሄኔ ነው አርቲስቷ ማርቲል ላንግስዶርፍ የምጽአት ቀን ቆጣሪ ሰዓት የተሰኘ ሥራ ለመፅሔቱ ሽፋን ይሆን ዘንድ ሠርታ ያስረከበችው።

ባለቤቷ የማንሀተን ፕሮጀክት አባል ነው። የኑክሌር ጦር መሣሪያ ነገር እጅግ እንቅልፍ እንደሚነሳው ታውቃለች። ለዚህ ነው ትኩረት እንዲስብ አድርጋ የምፅዓት ቀን ሰዓትን የተጠበበችበት።

የሰዓቱ መልዕክት ግልፅ ነው። የሰዓቱ ቆጣሪ ወደፊትም ወደኋላም መሄድ ይችላል ነው መልዕክቱ።

በአውሮፓውያኑ 1949 ሶቪዬት ኅብረት የመጀመሪያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራዋን አደረገች። ይህን ተከትሎ መፅሔቱ ለዕኩለ ሌሊት ሰባት ደቂቃ ይቀረው የነበረውን ሰዓት ወደ ሦስት ደቂቃ አሳጠረው።

በ1953 ዩናይትድ ስቴትስ እና ሶቪዬት ኅብረት ቴርሞኑክሌር መሣሪያዎቻቸውን ሲያፈነዱ ሰዓቱ ለዕኩለ ሌሊት ሁለት ደቂቃ እንዲቀረው ሆነ።

ይህ 20ኛው ክፍለ ዘመን ሰዓቱ ለዕኩለ ሌሊት እጅግ የቀረበበት ወቅት ነበር።

የምፅዓት ቀን ሰዓት

ሰዓቱን ማንበብ

ለመሆኑ የሰዓቱ እንቅስቃሴዎች ትርጉማቸው ምንድነው? እርግጥ ነው አስተማሪያችን እንዳስረዳችን ሰዓቱ የሰው ልጅ ምን ያህል ጊዜ ቀረው የሚለውን ለማየት ይጠቅማል ብሎ ማስረዳት ቀላል ነው።

ነገር ግን ትክክለኛው አነባበብ የሚሆነው ሰዓቱ አሁን የሰው ልጅ ምን ያህል ስጋት ውስጥ እንዳለ ማሳያ ነው የሚለው ነው።

በአውሮፓውያኑ 2003 እንግሊዛዊው ኮስሞሎጂስት እና የጠፈር ተመራማሪ በያዝነው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ምድራችን ትጠፋለች ወይስ ትቆያለች ለሚለው ጥያቄ ምላሹ 50/50 ነው ብሎ ነበር።

እርግጥ ነው ይህን ግምት በማስቀመጥ ይህ ሳይንቲስት ብቻውን አይደለም። ነገር ግን ሳይንስቲስቶቹም እንደሚያምኑት ይህ ግምት ነው እንጂ እውነታ አይደለም።

አንዳንዶች ደግሞ ሰዓቱን የሚያነቡበት መነፅር ይለያል። ሰዓቱ ምን ያህል ቀረን ሳይሆን፣ ላለብን ስጋት ምን እያደረግን ነው የሚለውን ማሳያ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

በ1962 (እአአ) የኩባ የሚሳዔል ቀውስ ዓለማችን ወደ ኒውክሌር ጦርነት የተቃረበችበት ወቅት ነበር። በ1963 የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ በስምምነት ሲታገድ ሰዓቱ አምስት ደቂቃ ወደኋላ ቆጠረ።

ለምሳሌ በ2017 በአሜሪካ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል የነበረውን ውጥረት፤ እንዲሁም ኢራን ከኑክሌር ስምምነት መውጣቷን ተከትሎ ብዙዎች ፊታቸውን ወደ ሰዓቱ አዙረው ነበር።

ነገር ግን የሳይንስቲስቶች ስጋት ይህ አይደለም። እንደውም መሰል ውጥረቶች በአገራት መካከል የሚጠበቁ ክስተቶች ናቸው።

ሳይንቲስቶቹን የሚያሰጋቸው ጉዳይ የኑክሌር ቦምቦቹ መኖር፣ ቀጥሎ ደግሞ መሪዎች በቀውስ ወቅት እኒህን መሣሪያዎች ለመጠቀም ያላቸው አዝማሚያ ምን ያህል ነው የሚለው እና ከዚህ የሚያግዳቸው ነገር አለመኖሩ ነው።

በአውሮፓውያኑ 1987 እና 1991 መካከል በነበሩት አራት ዓመታት ሰዓቱ 14 ደቂቃ ወደ ኋላ ቆጥሯል። ይህ የሆነው የቀዝቃዛው ጦርነት መገባደድን ተከትሎ አገራት የኑክሌር ጦር መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ነው።

በ2007 ቡሌቲኑ የአየር ንብረት ለውጥን ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ስጋት ጋር ደምሮ ለሰው ልጆች ኅልውና ስጋት መሆኑን አውጇል።

እርግጥ ነው ሁለቱ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የኒውክሌር ጦርነት በደቂቃዎች ውስጥ ሊጀመር ይችላል። የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ደግሞ ዓመታትን የሚወስድ ነው።

አልፎም የኑክሌር ጦር መሣሪያ ጉዳይ በጥቂት ሰዎች እጅ ውስጥ ያለ ሲሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ግን የሁላችንም ኃላፊነት ነው።

ቢሆንም ሁለቱም የሚያመጡት አደጋ ቀላል የሚባል አይደለም።

ከኑክሌር ጦር መሣሪያ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለፈ ቴክኖሎጂ ማለትም ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ባዮሎጂካል መሣሪያዎች እና ናኖቴክኖሎጂም የጥቅማቸውን ያህል ጉዳታቸው ለሰው ልጆች ኅልውና አደጋ ተደርጎ ይቆጠራል።

እኒህ ከላይ የተጠቀሱት ስጋቶችን ጨምሮ ሌሎች የሰው ልጅ እየተጋፈጣቸው ያሉ አደጋዎች ሰዓቱን ወደ ዕኩለ ሌሊት የበለጠ እንዲቀርብ አድርገውታል።

አሁን ለዕኩለ ሌሊት 90 ሰከንድ ቀርቶናል። ያለንበት ዓለም ምን ያህል ነውጥ የበዛበት መሆኑን ማሳያም ነው። ኃያላን የሚባሉ አገራት የሚገቡትን ስምምነት እያከበሩ አይደለም።

የምጽአት ቀን ሰዓቱ ወደ ኋላ እንኳ ቢቆጥር ልንዘናጋ አይገባም። ኮቪድ-19 አገራት ተባብረው ልክ እንደ ኩባው የሚሳዔል ቀውስ ችግሮችን የሚፈቱበት ክስተት በሆነ ነበር። ግን አልሆነም።

ሰዓቱ መቁጠሩን ቀጥሏል። እንደምንም ጠምዝዘን ወደኋላ እንዲቆጥር ካላደረግነው በቀር የዕኩለ ሌሊት መዳረስን የሚያሰማው ደወል ከመጮህ የሚመለስ አይመስልም።

የኑክሌር አረሮች ብዛትን የሚያሳይ ሰንጠረዥ