ኮሜዲያንና ተዋናይ ጆን ኦካፎር በይበልጥ (ሚስተር ኢቡ) በሚለው ቅጽል ስም ነው የሚታወቀው
የምስሉ መግለጫ,ኮሜዲያንና ተዋናይ ጆን ኦካፎር በይበልጥ ሚስተር ኢቡ በተሰኘው ቅጽል ስም ነው የሚታወቀው

28 ጥር 2024, 09:31 EAT

የዝነኛው ናይጄሪያዊ ኮሜዲያንና ተዋናይ ጆን ኦካፎር ሁለት ልጆች ታሠሩ።

ልጆቹ የታሰሩት ለአባታቸው ሕክምና የተዋጣን ገንዘብ ሰርቀው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ነው።

ጆን ኦካፎር የጤና እክል ገጥሞት ለሕክምና ከፍተኛ ገንዘብ የተዋጣለት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ነበር።

የ62 ዓመቱ ተዋናይና ኮሜዲያን በይበልጥ ‘ሚስተር ኢቡ’ በሚለው ስሙ ነው የሚታወቀው።

‘ሚስተር ኢቡ’ ባለፈው ኅዳር ወር አንድ እግሩ ከተቆረጠ በኋላ አድናቂዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለው ነበር።

ይሁንና ወንድ ልጁ ዳንኤል ኦካፎር እና ያሳደጋት ልጁ ጃስሚን ቺዮማ የአባታቸውን ስልክ ሰርስረው በመግባት መተግበሪያ ከጫኑ በኋላ የተዋጣውን ገንዘብ ቀስ በቀስ ወደራሳቸው ሲያስተላልፉ እንደነበር ተደርሶበታል።

በዚህ ጥበብ በተሞላበት ዘረፋ በድምሩ 60ሺህ 700 ዶላር መውሰድ ችለዋል ይላል ፖሊስ። ከዚህ በኋላ ነው የተደረሰባቸው።

ልጆቹ በሌጎስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን ለጊዜው ለሚዲያ የሰጡት አስተያየት የለም።

ተጠርጣሪዎቹ ልጆች ሐሙስ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን የዋስ መብታቸው በ17ሺህ ዶላር እንደሚከበርላቸው ፍርድ ቤት ነግሯቸዋል።

ይሁንና አሁንም ታስረው ነው ያሉት።

መርማሪ ፖሊስ እንደሚለው ገንዘቡን በቀላሉ ሊዘርፉ የቻሉት አባታቸው ስልክ ላይ ልዩ የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ መጫን በመቻላቸው ነው።

ይህ መተግበሪያ ገንዘቡን በቀላሉ ወደራሳቸው እንዲያስተላልፉ ማድረግ የሚያስችላቸው ነው።

የዝነኛው ናይጄሪያዊ ተዋናይና ኮሜዲያን ኢቡ የጤና ሁኔታ የታወቀው ባለፈው ዓመት ልጆቹ ሆስፒታል ሆነው በማኅበራዊ ሚዲያ አባታቸው ስላለበት ሁኔታ ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው።

በዚያ ቪዲዮ ላይ ሚስተር ኢቡ የሆስፒታል ወጪው ከፍተኛ በመሆኖ ወዳጅ አድናቂዎቹ የአቅማቸውን እንዲያግዙ ይማጸናል።

ተዋናዩ የዛሬ 20 ዓመት “ሚስተር ኢቡ” የሚል የተሳካለት ኮሜዲ ከሠራ በኋላ ይኸው ሥም መጠሪያው ሆኖ ዘልቋል።

ኢቡ በዓመት ቢሊዮን ዶላሮችን እንደሚያስገባ በሚነገርለት የኖሊዉድ ፊልም ኢንዱስትሪ በበርካታ ፊልሞች ላይ ተውኗል።

ናይጄሪያዊ ኮሜዲያንና ተዋናይ ጆን ኦካፎር (ሚስተር ኢቡ) 13 ልጆች እንዳሉት ከዚህ ቀደም ከአንድ የአገር ውስጥ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሮ ነበር