ኬኔት ዩጂን ስሚዝ

ከ 9 ሰአት በፊት

የሞት ቅጣት የተፈረደበት ወንጀለኛ ከዚህ በፊት ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፍርዱ ተፈፅሞበታል።

የአላባማ ባለሥልጣናት ይህን መሣሪያ መጠቀም የፈለጉት ለምን ይሆን? አከራካሪ የሆነውስ ለምንድነው?

ኬኔት ዩጂን ስሚዝ መጀመሪያ የሞት ቅጣቱን እንዲቀበል የታቀደው መርዛማ በሆነ መድኃኒት ነበር። ቅጣቱ ደግሞ ኅዳር 2022 እንዲፈፀም ነበር ዕቅዱ።

ነገር ግን ቅጣቱን እንዲፈፅሙ አደራ የተጣለባቸው ሙያተኞች በሁለት ገመድ መድኃኒቱን ለመስጠት ሞከሩ።

ቢሆንም ከብዙ ትግል በኋላ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው የሞት ቅጣቱ ለጊዜው እንዲሰረዝ ተወሰነ።

ያም ሆነ ይህ ስሚዝ የሞት ቅጣቱ አልቀረለትም።

በአውሮፓወያኑ 1988 የአንድ ሰባኪን ሚስት የገለደው ቅጥረኛ ገዳዩ ስሚዝ በናይትሮጂን ጋዝ የሞት ቅጣቱን እንዲወስድ ተደርጓል።

የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት በዚህ መልኩ የሞት ቅጣት ሲቀጣ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ምንም እንኳ የሞት ቅጣት ከጊዜ ጊዜ እየቀረ ቢመጣም ምን ዓይነት መሣሪያ ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚለው አከራካሪ ርዕስ እንደ አዲስ መነጋገሪያ ሆኗል።

ገዳይ መድኃኒቶች

ከአሜሪካ ግዛቶች ግማሽ ያህሉ አሁንም የሞት ቅጣት ሕግ አላቸው።

አንዳንዶቹ ግዛቶች አሁንም በስቅላት፣ አሊያም በጥይት ወይ ደግሞ በኤሌክትሪክ ወንበር የሚለውን ሕግ ይፈቅዳሉ።

የሞት ቅጣት መረጃ ማዕከል የሆነው ዲፒአይሲ የሞት ቅጣት መንገዶች የሚከታተል ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ እንደሚለው አንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች የተወሰኑ የሞት ቅጣት መንገዶችን መጠቀም አቁመዋል።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግዛቶች ፊታቸውን ወደ ገዳይ መድኃኒቶች አዙረዋል። ይህ መንገድ አንድን ሰው አደንዝዞ ከደቂቃዎች በኋላ የሚገድል ነው።

ከአሜሪካ ግዛቶች ገዳይ መድኃኒት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው ቴክሳስ ስትሆን ጊዜው ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1982 ነበር።

ባለፈው ዓመት ብቻ 24 ሰዎች በገዳይ መድኃኒት የሞት ቅጣታቸውን የተቀበሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ ፍሎሪዳ እና ቴክሳስ ግዛት የተፈፀሙ ናቸው።

በገዳይ መድኃኒቶች የሚተገበሩ የሞት ቅጣቶችን መፈፀም ቀላል አይደለም።

የስሚዝ የሞት ቅጣት ሳይሳካ ቀርቶ እንዲቋረጥ ከመደረጉ ከወራት በፊት አለን ሚለር የተሰኘ ግለሰብ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞት ነበር።

ይህ የሆነው አይቪ የሚባለውን መርፌ ማስገባት እጅግ አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ ነው።

ሌሎች በሞት ቅጣት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ወንጀለኞችም መርፌውን መውጋት አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ ፍርዳቸው ዘግይቶ ያውቃል።

ሌላው ለግዛቶች እክል የሆነው ጉዳይ ገዳይ መድኃኒቶችን በቀላሉ ማግኘት ነው።

በአንዳንድ ግዛቶች መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች እኒህን መድኃኒቶች በቀላሉ አይሸጡም አሊያም ማምረት አቁመዋል።

ዩኬ እና የአውሮፓ ሕብረት እኒህን ኬሚካሎች ወደ ውጭ መላክ ክልክል ነው ያሉት በአውሮፓውያኑ 2011 ነው።

የአሜሪካው ግዙፉ መድኃኒት አምራች ኩባንያ ፋይዘር ደግሞ ለሞት ቅጣት እንዲውሉ አምቼ አላቀርብም ሲል ወስኗል።

ቴክሳስ ገዳይ ኬሚካሎችን ያገኘችው ሚስጥራዊ ከሆነ የግል ኩባንያ መሆኑ ተዘግቦ ነበር።

የኤሌክትሪክ ወንበር

ናይትሮጂን ሃይፖክሲያ ምንድነው?

የአላባማ እሥር ቤት ባለሥልጣናት የስሚዝ ፊት ላይ ጭምብል አጥልቀው ነው ያልተቀላቀለ ናይትሮጂን ጋዝ የለቀቁት።

ጋዙ በራሱ መርዛማ አይደለም። ከመሬት ከባቢ አየር ከሶስት ገሚሱ በላይ የሚሆነው ናይትሮጂን ነው።

ነገር ግን የተጣራ ናይትሮጂን መሳብ ኦክሲጂን ወደ ጭንቅላት እንዲሄድ ያደርጋል። ይህ ሂደት ናይትሮጂን ሃይክሲያ ይባላል።

የሞት ቅጣት በናይትሮጂን ጋዝ እንዲሰጥ እስካሁን የፈቀዱ ግዛቶች ሶስት ብቻ ናቸው።

አላባማ ይህ የሞት ቅጣት መንገድ በግዛቷ እንዲተገበር የፈቀደችው በአውሮፓውኑ 2018 ነበር።

ለምን አከራካሪ ሆነ?

ስሚዝ በናይትሮጂን ጋዝ በሞት እንዲቀጣ ከመወሰኑ በፊትም ቢሆን ጉዳዩ አከራካሪ ነበር።

የአሜሪካ ኮሌጅ ኦፍ ኮሬክሽናል ፊዚያሽንስ ፕሬዝደንት የሆኑት ዶክተር ጄፍ ኬለር “ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ” ይላሉ።

የሞት ቅጣት መንገዶችን የሚያጠኑት ዴቦራህ ዴኖ ደግሞ “ቅጣቱ ስቃይ አልባ መሆን አለበት” የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

“ነገር ግን ትኩረት እንዲሰጠው የምፈልገው ጉዳይ – ስቃይ አልባ ያልኩት በፅንሰ-ሐሳብ ደረጃ ነው” ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ስሚዝ ሊያስመልሰው ይችል ነበር አሊያም ተርፎ የጭንቅላት ጉዳት ሊደርስበት ይችል ነበር።

የሞት ቅጣቱን የሚደግፉ ሰዎች ደግሞ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ሰዎች አደጋ ሲያጋጥማቸው ናይትሮጂን ሃይፖክሲያ ይደርስባቸዋል፤ ነገር ግን የሚያውቁት ነገር የለም ሲሉ ይከራከራሉ።

ለኦክላሆማ ግዛት የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው “ኦክሲጅን ሳይኖር ናይትሮጂን ጋዝን 12 ጊዜ መሳብ ሰዎች በድንገት አእምሯቸውን እንዲስቱ ያደርጋል።”

የአላባማ ግዛት አቃቤ ሕግ ጄኔራል ስቲቭ ማርሻል ናይትሮጂን ጋዝ “እስካሁን ከተጠቀምንባቸው መንገዶች ሰብዓዊው ነው” ይላሉ።

ነገር ግን የስሚዝን የሞት ቅጣት የተከታተሉ አንዳንድ ሰዎች ስሚዝ በጥቂት ሰከንድ ውስጥ ራሱን አልሳተም፤ ለደቂቃዎች ጋዙን እየሳበ ሲንገላታ ነበር ይላሉ።

በአሜሪካ በርካታ ሰዎች በሞት ቅጣት የተገደሉት በ1999 ነበር። ቁጥራቸው ደግሞ 98።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን ግዛቶች የሞት ቅጣቶችን ከመፈፀም እየተቆጠቡ መጥተዋል።

ጋለፕ የተሰኘው የሕዝብ አስተያየት ሰብሳቢ ድርጅት 53 በመቶ አሜሪካዊያን ወንጀለኞች በሞት ቅጣት መቀጣት አለባቸው ይላሉ ይላል።

ከ30 ዓመታት በፊት የሞት ቅጣትን የሚፈቅዱ አሜሪካዊያን 80 በመቶ ነበሩ።