
ከ 9 ሰአት በፊት
በጋዛ እርዳታ በማስተባበርና በማሰራጭት ከፍተኛ ሥራ የሚሠራው የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ (በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ UNRWA) ለጋዛ ድጋፍ ያቆሙ አገራትን አወገዘ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ውሳኔውን “አስደነጋጭ” ብለውታል።
ይህ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ከ2 ሚሊዯን ለሚልቁ የጋዛ ነዋሪዎች ምግብና መጠለያን በዋናነት ሲያቀርብ ቆይቷል።
አሁን ዋንኛ የገንዘብ ድጋፍ ለኤጀንሲ ይሰጡ የነበሩት ዩኬና ሌሎች የምዕራብ አገራት መለገስ አቆመዋል።
ይህም የሆነው ሐማስ በፈጸመው መብረቃዊ ጥቃት የዚህ ኤጀንሲ ሠራተኞች ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት እሰራኤል በማውጣቷ ነው።
የኤጀንሲው ኃላፊ ፊሊፔ ላዛሪኒ “ሁለት ሚሊዮን ሰው ሕይወቱ የተመሠረተው በዚህ እርዳታ ነው” ሲሉ የአደጋውን ስፋት ለማሳየት ሞክረዋል።
እርዳታ መስጠት ያቆሙት ዩኬን ጨምሮ ስምንት አገራት ሲሆኑ እነሱም አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና አሜሪካ ናቸው።
ኤጀንሲው በበኩሉ በሐማስ ጥቃት እጃቸው አለበት የተባሉትን ሠራተኞች ኮንትራት ማቋረጡንና ምርመራም እንዲጀመር ማድረጉን አውስቷል።
በፈረንጆቹ 1949 የተመሠረተው የተባበሩተ መንግሥታት የተራድኦና የሥራ ኤጀንሲ በምህጻሩ UNRWA በጋዛ ትልቁን የእርዳታ ሥራ የሚሠራ ተቋም ነው።
በጋዛ ብቻ ሳይሆን በዌስትባንክ፣ በሊባኖስ፣ በዯርዳኖስ እና ሶሪያ የስደተኞች ካምፕ ለፍልስጤማዊያን ሰፊ እርዳታ አቅራቢ ነው።
ኤጀንሲው በጋዛ ብቻ 13ሺህ ሠራተኞች አሉት።
- አዋሽ አርባ፡ በኢትዮጵያ ከጅምላ እስር ጋር ስሙ የሚነሳው ‘የበረሃው ጓንታናሞ’24 ጥር 2024
- ናይጄሪያ፡ የአባታቸውን ሕይወት ለማትረፍ የተዋጣ 70ሺህ ዶላር የዘረፉ ታሰሩ28 ጥር 2024
- የአፍሪካ ዋንጫ፡ ናይጄሪያ እና አንጎላ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜው ተሸጋገሩ28 ጥር 2024
እስራኤል የዚህ ኤጀንሲ ሠራተኞች ለሐማስ ጥቃት ድጋፍ ሰጥተዋል ካለች በኋላ ነው ኤጀንሰው ፈተና ውስጥ የወደቀው።
ለጋሾቹም በድንገት የእርዳታ እጃቸውን ሰብስበዋል።
እስራኤል ይህን ኤጀንሲ ብቻ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታትንም በጸረ ሴማዊነት ትከሳለች።
የኤጀንሲው ኃላፊ ሚስተር ላዛሪኒ ሲናገሩ፣ “ጥቂት ሠራተኞች ከሐማስ ጋ አብረዋል በሚል ክስ የ2 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል ስሜት አይሰጥም” ይላሉ።
በተለይ በዚህ እጅግ አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ በጥቂት ሠራተኞች ምክንያት ሚሊዮኖችን የዕለት ጉርስ መከልከል አስደጋንጫ ውሳኔ ነው ብለዋል።
የቤኒያሚን ናታንያሁ አማካሪ ዐርብ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኤጀንሲው ሠራተኞች በሐማስ መብረቃዊ ጥቃት ‘እጃቸው አለበት’።
ይህ ብቻ ሳይሆን ለዚሁ ኤጀንሲ የሚሠሩ መምህራንም ሐማስ የፈጸመው ጥቃት አስቦርቋቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የሐማስ መብረቃዊ ጥቃት 1ሺህ 300 ሰዎች የተገደሉበት ሲሆን 250 ሰዎች ደግሞ በእገታ ተወስደዋል።
ያን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ላለፉት 12 ሳምንታት በወሰደችው መጠነ ሰፊ ጥቃቶች ከ26ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።
የሚበዙት ደግሞ ሴቶችና ሕጻናት ናቸው ይላል በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር።