
ቀን:
ከሁለት ዓመት በፊት በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የፌዴራል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯና የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልና የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት፣ የቀድሞ የፌዴራል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ የተከሰሱበትን ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ብይን በመስጠቱ ነው፡፡የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሩታ አድማሱ፣ ወ/ሪት ቤተልሔም አድማሱ (የወ/ሮ ሩታ እህት)፣ አቶ መርሐዊ ምክረ፣ ወ/ሮ ራሔል ብርሃኔ፣ ወ/ሮ ፀሐይ ደሜና አቶ ጌታቸው ደምሴ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9/1(ሀ) እና (3) ድንጋጌን በመተላለፍ፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ተቋም አሠራርን በጣሰ ሁኔታ፣ አስፈላጊው የደኅንነት ይለፍ ያልተደረገለትንና ለቦታው ብቁ የሚያደርገው የትምህርት ዝግጅት የሌለውን አቶ አቤል ጌታቸው የተባለን ግለሰብ፣ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የተደራጁና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የሚደግፉ ወንጀሎች ፍተሻና ትንተና ከፍተኛ ኤክስፖርት ሆኖ እንዲሠራ መመደባቸውን የዓቃቤ ሕግ ያስረዳል፡፡ክሱ እንደሚያስረዳው፣ ሕግ በጣሰ ሁኔታ የተመደበው ግለሰብ የተቋሙ የፋይናንስ መረጃ ክትትልና ቅበላ ቡድን መሪ ሆኖ ሲሠራ፣ የተቋሙን የቀደመ የመረጃን ሚስጥራዊነት የጠበቀና ተጠያቂነትን ያማከለ የመረጃ ቅበላና ትንተና አሠራር በመለወጥ፣ ተከሳሹ (አቶ ቴዎድሮስ) ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት ሠርተዋል፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ አቶ ቴዎድሮስ የመደቡት አቶ አቤል ባለሀብቶችንና ድርጅቶቻቸውን የባንክ ሒሳብ ቀድሞ በማጥናትና መረጃዎችን በመውሰድ፣ ባለሀብቶቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ እንዲጠይቅና የማይከፍሉ ከሆነ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው ላይ ምርመራ በማድረግ፣ ጉዳዩን ለፖሊስ እንዲያስተላልፍና የወንጀል ምርመራ እንዲጀመርባቸው እንዲያደርግ ጫና መፍጠራቸውን ያስረዳል፡፡በመሆኑም አቶ አቤል ጌታቸው፣ አቶ ተስፋ ሚካኤል ገብረ መስቀል የተባሉ ግለሰብን ቢሮ ድረስ በመጥራትና በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ጉዳዩን እያጣሩ እንደሆነ በመንገር ሌሎች ከሕገወጥ ግብይት ጋር በተያያዘ በንግድ ወንጀል እንደተሰማሩ በመግለጽ፣ ጉዳዩ ሊጣራና የግልና የድርጅታቸው የባንክ ሒሳብ ሊታገድ መሆኑን በመንገርና በማስፈራራት 1,500,000 ብር ፉፋ ዳባ ዱቤሳ በተባለ ግለሰብ አካውንት እንዲያስገቡ ማድረጉ በክሱ ተብራርቷል፡፡በተጠቀሰው የባንክ ሒሳብ ገንዘቡ ከገባ በኋላ፣ ከላይ ለተጠቀሱት ሰዎች በማከፋፈል በየግለቸው አካውንት ገቢ እንዲደረግ ማድረጉንም ክሱ ያብራራል፡፡ግለሰቡ (አቶ አቤል) አቶ ወላይ ፍሰሐ ለተባሉ ግለሰብ (ተበዳይ) ስልክ በመደወልና ቢሮው ድረስ በመጥራት፣ ‹‹የንግድ ፈቃድህ ያልታገደው በእኛ ጥረትና ልፋት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ችግር እንዳይደርስብህና ገንዘብህ እንዳይታገድ 1,400,000 ብር ክፈል›› በማለት ማስፈራራቱም ተጠቁሟል፡፡ ተበዳዩ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ እንደሌላቸው በማስረዳት 1,000,000 ብር በፉፋ ዳባ አካውንት ማስገባታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ መሐሪ ተስፋዬ የተባሉ የግል ተበዳይንም ሕወሓትን በገንዘብ እንደሚረዱና መረጃ እንደደረሰው በመግለጽ፣ ገንዘብ እንዲከፍሉ፣ የማይከፍሉ ከሆነ ‹‹ሽብርተኛን በገንዘብ መርዳት ወንጀል›› እንደሚታሰሩ በማስፈራራት 1,000,000 ብር በፉፋ ዳባ አካውንት እንዲገባ በማድረግና ለተጠቀሱት ተከሳሾች የግል አካውንት እየተቀናነሰ እንዲገባ ማድረግ፣ በአጠቃላይ 3,470,000 ብር መቀበላቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡በአጠቃላይ አቶ ቴዎድሮስ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በኃላፊነት የሚመሩትን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ተቋም፣ የግለሰቦችን የባንክ ሒሳብ ለተወሰነ ጊዜ አግዶ ማቆየት፣ ዕግዱ እንዲነሳ የማድረግ፣ የፋይናንስ ትንተና መሥራትና ውጤቱን ለፍትሕ አካላት የማስተላለፍን ሥልጣን አላግባብ መጠቀማቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ሌሎቹም ተከሳሾች በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕገወጥ መሆኑን እያወቁ በመጠቀማቸውና በመደበቃቸው ክስ እንደተመሠረተባቸው የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ተከሳሾች ድርጊቱን እንዳልፈጸሙና ወንጀለኛም እንዳልሆነ በማስረዳት የእምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠት፣ የተወሰኑትም የክስ መቃወሚያ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ተከሳሾቹ ከአቶ ጌታቸው ደምሴ (በሌሉበት የተከሰሱ) በስተቀር ወንጀሉን ክደው ቢከራከሩም፣ ዓቃቤ ሕግ ሰባት የሰው ምስክሮችንና 12 የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ‹‹ዓቃቤ ሕግ ክሱን አስረድቷል? ተከሳሾች ሊከላከሉ ይገባል? ወይስ አይገባም?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ መዝገቡን ከመረመረ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረባቸው የሰዎች ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች፣ አቶ ቴዎድሮስ አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1ሀ) እና (2) ድንጋጌ መሠረት ማስረዳት በመቻሉ እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱን ብይኑ ያስረዳል፡፡ሌሎች ተከሳሾችም በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ድንጋጌን መተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በማስረዳቱ፣ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ በሌሉበት የተከሰሱት አቶ ጌታቸው ደምሴ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1ሀእናለ) እና (ሐ)ን እንዲሁም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 163(3) ድንጋጌ መሠረት፣ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ጥፋተኛ መባሉን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡በመሆኑም አቶ ቴዎድሮስ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ በፈረንሣይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚሊተሪ አታሼነት የሚሠሩ ጄኔራል አህመድ ሀምዛና ሌሎች የመከላከያ ምስክሮችን ቆጥረዋል፡፡ፍርድ ቤትም ለወ/ሮ ሙፈሪያት በመሥሪያ ቤታቸው በኩል መጥሪያ እንዲላክላቸው፣ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኩል ጥሪ እንዲደርሳቸው፣ ፈረንሣይ ያሉት ጄኔራል መሐመድ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የቨርቹዋል ሲስተም እንዲዘጋጅላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ሌሎች መከላከያ ምስክሮች በቀጠሮ ቀን እንዲገኙ ትዕዛዝ በመስጠት ለየካቲት 19 እና 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡