

ትግራይ ኢሮበ ወረዳ
ዜና በትግራይ ክልል የኢሮብ ነዋሪዎች ‹‹በሁለት መንግሥታት መካከል ተከፍለን ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠናል›› አሉ
በትግራይ ክልል የኢሮብ ነዋሪዎች ‹‹በሁለት መንግሥታት መካከል ተከፍለን ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠናል›› አሉ
ቀን: January 28, 2024
- የወረዳው አስተዳዳሪ ብሔረሰቡ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ብለዋል
በትግራይ ክልልና ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚኖረው የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሁለት በመከፈላቸው ማኅበረሰቡ ለድርቅ፣ ለስደትና ለተለያዩ በደሎች መጋለጡን ተናገሩ፡፡
መድኅን ኣውዓላ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ አሁንም ድረስ ከብሔረሰቡ ስምንት ቀበሌዎች ውስጥ እንዳልገዳ፣ ወርዓትስ፣ ዓገረለኩማና ዳያዓሊቴና በተባሉ አራት ቀበሌዎች የኤርትራ ሠራዊት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢሮብ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ምሥግና በበኩላቸው፣ ‹‹ወደ 60 በመቶ የሚሆነው የብሔረሰቡ ግዛት በኤርትራ ሠራዊት ሥር ነው። ሁለቱን ቀበሌዎች ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሯቸው የሚገኝ ሲሆን፣ የተቀሩት ሁለቱ ውስጥ ደግሞ በከፊል ሰፍሮ ይገኛል፤›› ብለዋል።
Video from Enat Bank Youtube Channel.
ነዋሪዎቹ ኢሮብን በአዲግራት በኩል ከተቀሩት የትግራይ ክልል ከተሞች ጋር የሚያገናኘው መንገድ አገልግሎት እንደማይሰጥ ገልጸዋል።
አስተዳዳሪው ከአዲግራት ወደ ኢሮብ የሚወስደው መንገድ በኤርትራ ሠራዊት ከመውደሙም ባሻገር አሁንም በሠራዊቱ ተዘግቶ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ‹‹ይህ ዋና መንገድ በመዘጋቱ ትራንስፖርት ተቸግረናል፡፡ ቀበሌዎችን ውስጥ ለውስጥ ለማገናኘት ከጦርነቱ አራት ዓመታት በፊት ቀድሞ ግንባታቸው ተጀምሮ ባልተጠናቀቁ መስመሮች ነበር የምንሄደው። አሁን ይኼም አስቸጋሪ እየሆነብን ነው፤›› ብለዋል።
ፍሱህ ወልዳይ የተባሉ ነዋሪ ደግሞ በወረዳው ከባድ ረሃብ መኖሩን ገልጸው፣ ‹‹የዕርዳታ እህል ለማግኘት ምዝገባ አለ። ግን በስንት አንዴ የምግብ ድጋፍ ቢገኝም የተወሰነ እንጂ የሰውን ሕይወት ሊያተርፍ የሚችል ነገር አይገኝም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ኢያሱ በበኩላቸው ኢሮብ ወረዳ ዘንድሮ ከባድ ድርቅ ያጋጠመው መሆኑን፣ እስካሁን ድረስም ምንም ዓይነት ዝናብ አላገኘም ብለዋል። የምግብና የውኃ እጥረት በሰውና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዕርዳታ በሰብዓዊ ድርጅቶችና አልፎ አልፎ በመንግሥት ይቀርብ እንደነበር ገልጸው፣ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የምግብ ዕርዳታ ከቀረበ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነው አስታውሰዋል፡፡
‹‹በወቅቱ ድጋፉ ለአራት ሺሕ ሰዎች ነበር የቀረበልን። መንግሥትም አልፎ አልፎ የሚልክልን የአደጋ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ነበር፡፡ እሱም ከጊዜው ቆይታ አንፃርና ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን አልነበረም፤›› ብለዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎችና አስተዳዳሪው ከምግብ ድጋፍ ባሻገር በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር በሚገኙት አራት ቀበሌዎች ትምህርት መቋረጡን፣ በተቀሩት የኤርትራ ሠራዊት ተቆጣጥሯቸው ባሉት አራቱ ደግሞ ሕፃናት በኤርትራ ካሪኩለም እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አቶ ኢያሱ የመድኃኒት እጥረት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹በረሃብ አደጋ ውስጥ ወድቀው ያሉ ብዙ ታማሚዎች የመድኃኒት ዕጦቱ ተደምሮ ሕይወታቸውን እያሳጣቸው ነው፤›› ብለዋል።
ዝክተ ሓድጉ የተባሉ ነዋሪ፣ ‹‹ከጦርነቱ በፊት የብሔረሰቡ ቁጥር 32 ሺሕ ነበር። አሁን ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ ወደ ስደት እየሄደና ብሔረሰቡም በተደራረቡበት ችግሮች ምክንያት ቁጥሩ እየተመናመነ እየጠፋ ነው፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
መድኅን ኣውዓላ በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ በተለይ ከድንበር ጉዳዩች ጋር በተያያዘ ትልልቅ ታሪካዊ ውሳኔዎችን አልፎ ዛሬ ድረስ የቆየው ማኅበረሰብ፣ በሁለት አገሮች መካከል ተከፍሎ በእጅጉ እየተጎዳ ያለ ብሔረሰብ ነው፤›› ብለዋል።
የኢሮብ ወረዳ አስተዳዳሪ የነዋሪዎቹን አስተያየት ተጋርተዋል። ‹‹የኢሮብ ብሔረሰብ የድርቅ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን እንደ ብሔረሰብ እየጠፋ ነው። ቋንቋው፣ ባህሉና ወጉ ተጠብቆ በራሱ አካባቢ መኖር ሲገባው በስደት፣ በረሃብ፣ በድርቅና በጠላት ተበታትኖ እንዳይጠፋ ዓለም አቀፍ ሕግጋት መተግበር አለባቸው፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም መከበር አለበት፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ በአጠቃላይ የሚመለከታቸው ሁሉ ብሔረሰቡ እንዳይጠፋ መታደግ አለባቸው ብለዋል።