EthiopianReporter.com 

እኔ የምለዉ ትናንት ከጠፉት የዓለም ባህላዊ ቅርሶች ተምረን ያሉንን እንጠብቅ

ትናንት ከጠፉት የዓለም ባህላዊ ቅርሶች ተምረን ያሉንን እንጠብቅ

አንባቢ

ቀን: January 28, 2024

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ባህላዊ ቅርስ ምንድነው?

ባህላዊ ቅርሶች የሚባሉት በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደ ባህላዊ ቅርስ የሚታዩ ከጥንት አያት፣ ቅድመ አያቶች ሲተላለፉ የመጡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ሲሆኑ እነዚህም በዘልማድ የሚሠሩ፣ የሚተገበሩ፣ ወይም ተለይተው የሚታወቁ ሥፍራዎች፣ ቁሳቁሶች፣ የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነሱም ተጨባጭ ወይም ረቂቅ ቅርሶች ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይህም ሲባል በተጨባጭ የባህል ቅርስ ውስጥ ረቂቅነት፣ በረቂቅ ቅርስ ደግሞ ተጨባጭነት የለም ማለት አይደለም፡፡ ይሁንና ተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ ብሎ መለየት ሐሳብን በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ፣ ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን ለማሳየት ስለሚረዳ ባህላዊ ቅርሶችን ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶች (Tangible and Intangible Cultural Heritage) በማለት እንደሚከተለው ተተንትነው ተቀምጠዋል፡፡ ተጨባጭ ባህላዊ ቅርስ ዓይነቱ በዚያ ያለ ቢሆንም  ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ በማለት በሁለት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ተንቀሳቃሽ ቅርስ (የሥዕል፣ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ በጠረጴዛ ላይ፣ በጓሮ፣ በበረንዳ ላይ የሚቀመጡ የሐውልት፣ የሳንቲም፣ የጽሑፍ ሥራዎች)፣ ሲሆኑ እነዚህ ተጨባጭ ባህላዊ ቅርሶች የሚገኙባቸው ቦታዎች፣ እነዚህን ሥራዎች ዕውን ለማድረግ የተጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች፣ ቀለሞች፣ ሥፍራዎች ሁሉ የዚሁ አካል ናቸው፡፡

የማይንቀሳቀስ የባህል ቅርስ በብዙ መንገድ ከፋፍለን የምንመለከተው ሲሆን፣ እንደአክሱም ያሉ ታላላቅ ሐውልቶች፣ በከርሰ ምድር ቁፋሮ የተገኙ ታሪካዊ ሥፍራዎች ለምሳሌ ሉሲና ሌሎች ቅሪተ አፅምና ቅርስ የተገኘባቸው በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሥፍራዎች፣ በዋሻ ውስጥ የተሣሉ ሥዕሎች ለምሳሌ በጌዲኦ፣ በሐረርና በሌሎችም ሥፍራዎች የሚገኙ፣ እንደ ጥያና ኢማም አህመድ ኢብራሂም ያሉ ትክል ድንጋዮች፣ እንደንግሥት ፉራ መቃብርና የንግሥት ፉራን ታሪክ የሚያስታውሱ ቦታዎች፣ በቤተ ክርስቲያን ትይዩ እንደ ሚከመሩና ጦርነት የተካሄደባቸው ሥፍራዎች መሆናቸውን የሚያመለክቱ ቁልል ድንጋይዎች፣ በዳውሮ ውስጥ 175 ኪሎ ዙሪያ ጥምጥም ከሁለት እስከ አምስት ውፍረት እንዲሁም ከሁለት እስከ 3.8 ከፍታ ያለው ሜትር ስፋት የቃዎ ሐላላ ካብ፣ ተራራ ላይ የተሠሩ ለየት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ለምሳሌ የላሊበላ፣ የውቅሮ፣ የአዳዲ ማርያም ወዘተ ቅርሶች፣ እንደ ይሓ ያሉ ጥንታዊው ሕንፃዎች፣ በደሴት ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ እንደ ሐረር ጁገል ያሉና በደቡብ ክልል በዳውሮ የሐላላ የድንጋይ ካብ አጥር፣ በሐይቆችና በውቅያኖሶች ሥር የሚገኙ (የጀልባ፣ የመርከብና የከተማ ፍርስራሾች፣ የአባ ጅፋርና የሸኽ ኦጀሌ ቤት ወዘተ. ጥንታዊና የቅርብ ተጨባጭ የሕንፃ ቅርሶች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ረቂቅ ቅርሶች (Intangible Cultural Heritage) የሚባሉት ደግሞ፣ ሥነ ቃሎች፣ ትውፊቶች፣ ተረቶች፣ አፈ ታሪኮች፣ እስክስታ፣ ጭፈራ፣ ዘፈኖች፣ እንጉርጉሮዎች፣ ቀረርቶዎች፣ ሽለላዎች፣ የእምነት መገለጫ እንቅስቃሴዎች ቅዳሴዎች፣ ውዳሴዎች፣ መንዙማዎች፣ የአዶ ከርቤ ዜማዎች፣ ወዘተ ያጠቃልላል፡፡

የተፈጥሮ ቅርስ እንደ ሰብስቤና ሶፍ ኦመር ዋሻ ያሉ ከእምነት ጋር የተያያዙ ተራራዎች፣ በድሬ ሸሕ ሑሴን እንደሚገኙ ዋሻዎች፣ ተክሎች፣ በወንዝ ውስጥ የሚገኙ የመስገጃ ሥፍራዎች፣ በተፈጥሮ ሰው ወይም እንስሳ ወይም ዛፎች መስለው የተሠሩ መልክዓ ምድሮች፣ በሥነ ሕይወት ዘርፍ ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ዛፎች ለምሳሌ ዋርካ፣ ተክሎች (ብዝኃ ሕይወት)፣ እንስሳት ለምሳሌ ዘንዶ፣ እንደ አርትአሌ በእሳተ ገሞራ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በመሬት መንሸራተት የተፈጠሩ ሥነ ምድራዊ ቅርሶች፣ ባህላዊ እምነት የሚፈጸምባቸው ወንዞች፣ ኢሬቻ የሚከበርበት የቢሾፍቱ ሆራ፣ የመስቀልና የጥምቀት በዓል የሚከበርባቸው ቦታዎች ወዘተ ያጠቃልላል፡፡ የተፈጥሮ ቅርሶችን ጥበቃ በሚመለከት ዩኔስኮ ልዩ ልዩ የጥበቃ መመርያዎችና ዕርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ1972 በተካሄደው ጉባዔ መሠረት በ153 አገሮች ከመዘገባቸው 936 ቅርሶች ውስጥ 725ቱ ባህላዊ ቅርሶች፣ 183ቱ የተፈጥሮ ቅርሶች፣ 28ቱ ቅልቅል ባህሪ ያላቸው እንደሆኑ በ2011 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የወታደራዊ ግጭት ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ የባህላዊ ቅርስ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህም ረገድ በአገራችን የሚጠቀሱ ብሔራዊና ክልላዊ ሥፍራዎች ሲኖሩ ከብሔራዊዎቹ መካከል ዓድዋ፣ ማይጨው፣ ፍኖተ ሰላም፣ ወልወል፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በክልል ደረጃም በሐረሪዎች የሚከበረውን የጨለንቆ ጦርነት ሥፍራ ማውሳት ይቻላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የጦርነት ቦታዎች ሲኖሩ ከእነዚህ መካከል በዓረቢያ የኡሑድና የበድር ጦርነት ሥፍራዎች፣ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የፋይዳ ያላቸው፣ ሕዝቦች ታሪክ የሠሩባቸው ቀናት ለምሳሌ ዓለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን፣ ዲ ደይ እየተባለ በአውሮፓ፣ በእንግሊዝ የጋራ ልማት አገሮችና በፈረንሣይ፣ በቤልጂየም፣ በዴንማርክ፣ በሆንግኮንግ፣ በአየርላንድ፣ በኢጣሊያ፣ በኖርዌይ፣ በፖላንድና በሌሎች ተባባሪዎቻቸው አገሮች የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያስከተለው ጥፋት የሚዘከርበት ቀን፣ በልዩ ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ የተሠሩ ሐውልቶች፣ ከባህላዊ ቅርሶች ጋር ይደመራሉ፡፡

ይሁንና ተጨባጩንም ሆነ ረቂቁን የባህል ቅርስ ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ስለቅርሱ ጠቃሚነት እንደ ሚበላ ምግብ፣ እንደ ልብስ፣ እንደ ቅመም፣ እንደ መድኃኒት፣ ሁሉ የታወቀ እንደሆነ ነው፡፡ ስናውቀው ዋጋ እንሰጠዋለን፣ ዋጋ ስንሰጠው ልንንከባከበው እንችላለን፣ ስንንከባከበው ሰዎች ስለራሳቸው ማንነት በመገንዘብ ደስታን ያገኙበታል፣ እነሱ ሲደሰቱበት ሌሎች የማያውቁት እንዲያውቁት ያደርጋሉ፡፡ እንዲያውቁት ሲያደርጉት በዝና የሰሙትን ለማየት ይመጣሉ፡፡ ሲመጡ እንደማንኛውም ሀብት የገቢ ማስገኛ ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ ታሪክ መሥራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዓለም ሥልጣኔ የተንፀባረቀባቸው፣ ነገር ግን አንድም በባህርና በአሸዋ የሰመጡ፣ ወይም በከርሰ ምድር ላይ የተቀበሩ ቢኖሩም በትርፍራፊነት የሚዘከሩ ቦታዎች አሉ።

ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸው የባህል ቅርስ ማዕከላት

ባህላዊ ቅርስ ከቱሪዝም ጋር ከፍተኛ ትስስር ያለው እንደመሆኑ በዓለማችን 300 ሚሊዮን የሚሆኑ ቱሪስቶች የባህል ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ይኸው ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ 800 ሚሊዮን ከፍ እንዲል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት አስታውቋል፡፡ በዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዘገባ መሠረት በአውሮፓ ብቻ በባህልና በባህል ቅርስ መስክ የተሳተፉት ስምንት ሚሊዮን ሠራተኞች ሲሆኑ 12 ሚሊዮን ሠራተኛ በአውቶሞቢል፣ 1.7 ሚሊዮን ሠራተኞች በኬሚካል ኢንዱስትሪው ከተሠማራው ሠራተኛ ጋር ሲነጣጠር ምን ያህል ከፍተኛና ጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በአደጉ አገሮች የታሪክ ማስታወሻዎችን መፈለግና ሲያገኝም አልምቶ ለበለጠ ዕድገት ሲጠቀምባቸው ባላደጉ አገሮች ደግሞ የነበራቸውን የታሪክ ቅርስ አንድም አፍርሰው ወይም ቸል ብለው ትንሽ ለማግኘት ብዙ ጥፋት ያደርሳሉ። ለምሳሌ በአገራችን እንደቁልል ድንጋይ፣ ትክል ድንጋይ፣ መቃብር፣ ለየት ያሉ የመኖሪያ መንደር ፍራሾች ያሉ ታሪካዊ ምልክቶችን ድራሻቸውን በማጥፋት እርሻ ያደርጓቸዋል።

በመሠረቱ አንዳች የጥፋት ምክንያት ሲኖር የሚጠፋው ቅርስ ብቻ አይደለም። ቋንቋ ይጠፋል። ባህል ይጠፋል። ጎሳና የዘር ግንድ ሁሉ ይጠፋል። በገሃድ የነበረው የሰው ልጅ የአንድ አካባቢ ሥልጣኔ ቀስ በቀስ እንደጀመረና ቀስ በቀስ እንዳደገ ሁሉ፣ በአንዳች ምክንያት ይጠፋል። ሆነም ቀረ አንዳንዶቹ ምልክት ያላቸው የሥልጣኔ ሥፍራዎች የጽሑፍ መረጃ ሲኖራቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ የጽሑፍ መረጃ ቢኖራቸውም ቦታዎቹ የሉም። ስለቅርሶቹ ባለቤቶች ማንነት (ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ጎሳቸው)  ጠፍቷል። ይህን ሀቅ የተረዱ አገሮች የጠፉትን እየፈለጉ፣ ያሉትን እየተንከባከቡ፣ አንድ በጥፋት ላይ ቋንቋን ልዩ ትኩረት ሰጥተው ከጥፋት እየታደጉና እያሳደጉ ወደፊት በመገስገስ ላይ ናቸው። 

ጥንታዊና ባህላዊ ቅርሶች ምንነትና በቅርሶች ስለሚደርስ ጥቃት

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ. በ1972 በተቋቋመው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስምምነት ላይ እንደተገለጸው፣ ባህላዊ ወይም የተፈጥሮ ቅርሶች አስፈላጊ ናቸው። የባህል ቅርስ ሐውልቶችን (እንደ የሥነ ሕንፃ ሥራዎች፣ ሐውልታዊ ቅርፃ ቅርሶች ወይም ጽሑፎች)፣ የሕንፃ ዓይነቶችና ቦታዎች (በአርኪኦሎጂ ቁፋሮ የተገኙትንም) ያካትታል። ከዚህም በተጨማሪ፣ የተፈጥሮ ገጽታዎች (አካላዊና ባዮሎጂካል ቅርፆችን ያቀፈ)፣ የጂኦሎጂካልና የፊዚዮግራፊያዊ ቅርሶች (አደገኛ የእንስሳትና የዕፅዋት ዝርያዎች መኖሪያን ጨምሮ) እና ከሳይንስ፣ ጥበቃ ወይም የተፈጥሮ ውበት አንፃር አስፈላጊ የሆኑት የተፈጥሮ ቦታዎች ያጠቃልላል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ጁላይ 6 ቀን 1977 የተቀበለችው የተፈጥሮ ቅርስ ኮንቬንሽንም ይህን መሠረታዊ ስምምነት መሠረት ያደረገ ነው።

እ.ኤ.አ. በ1978 በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ሁለተኛ ጉባዔ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ ከድንጋይ የተፈለፈሉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲሆኑ፣ በቅርቡም የጌዴኦ ትክል ድንጋዮች፣ የሰሜንና የባሌ ተራሮች የዓለም ቅርስ በመሆን ተመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2013 እና ከ2019 እስከ 2023 ባለው ጊዜ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ አባል ሆና ሁለት ጊዜ አገልግላለች፡፡

ባህላዊ እሴት ምንድነው?

ምንም እንኳን ባህል፣ እሴት፣ ልማድ (‘Culture,’ ‘Values,’ and ‘Customs’) የሚባሉት ቃላትን ሰዎች እያለዋወጡ የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ሰፊ ትንታኔ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ባህልና ባህላዊ ቅርስ ስንል ቀደም ሲል ለመተንተን እንደተሞከረው ሁሉ በረቂቅና በተጨባጭ ባህላዊ ቅርስነት የሚገለጽ ሲሆን ባህላዊ እሴት በሚባልበት ጊዜ ደግሞ በባህል ውስጥ ሥር ሰዶ ሰዎች ‹‹የእኔ ባህል ነው፣ የእኔን ማንነት ይገልጻል፣ ሁለንተናዬን ያንፀባርቃል፣ ባህላዊ ቅርሴንና ሀብቴን ያጠቃልላል፤›› ብለው የሚቀበሉትና በልዩ ልዩ መልኮች የሚገልጹት ነው፡፡ የባህል እሴትን በተግባር የመግለጽ ሁኔታም ልማድ ተብሎ ይጠራል፡፡ ለምሳሌ የገና በዓል አንድ የባህል ቅርስ ቢሆን፣ ሰዎች የገና በዓልን በውስጣቸው የእኔ ነው፣ እኔን ይገልጸኛል፣ እምነቴን ያንፀባርቃል ብለው እንደ እሴት የወሰዱት ሲሆን፣ የገና በዓልም በልዩ ልዩ ልማዶች ማለትም ገና በመጫወት፣ የገና ለገና በዓል የሚሆን ንፁህ ልብስ በማዘጋጀት፣ ራስም ንፁህ ሆኖና ተኳኩሎ በመውጣት ይገለጻል፡፡ ጉዳዩን በምግብ ስንመስለውም ኢትዮጵያውያን የእንጀራ ምግብ መመገብ ባህላቸው ነው፡፡ ለእንጀራ ምግብም ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡታል፡፡ በወጥ ወይም በሌላ ማጣፈጫ የመብላት ልማድም አላቸው፡፡ ስለዚህም ባህል፣ የባህል እሴትና ልማድ የአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ግንድና ቅርንጫፍ ወይም የሰው ልጅ ተጨባጭና መንፈሳዊ ባህሎች መገለጫ ባህሪ አካል ናቸው በጥቅሉ ማለት ይቻላል፡፡

ይሁንና ሁሉም ባህላዊ ቅርሶች እኩል ተቀባይነት አላቸው ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በህንድ ላም አርዶ መብላት በባህሉ የተከለከለ ነው፡፡ ከፍተኛ ረሃብ እንኳን እነሱም፣ ላሞቻቸውም ይሞታሉ እንጂ አይበሉም፡፡ ስለሆነም ‹‹ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው፣ ጅብ ከሚበላህ፣ ጅብ በልተህ ተቀደስ፤›› እንዲሉ ላሞቻቸውን በልተው ሕይወታቸውን አያድኑም?›› ከቶ ልንላቸው አንችልም፡፡ በአንዱ ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ባህላዊ ቅርስና ባህላዊ እሴት በሌላው ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ በአንዱ ኅብረተሰብ ጠቃሚ የሆነ ባህልና ባህላዊ እሴት በሌላው ጥቅመ ቢስ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንዳንዱ አካባቢ ሊሠራ የሚችል ልማድ በሌላው ሥፍራ ላይሠራ ይችላል፡፡

ባህላዊ እሴት እንዴት ይለካል?

እሴቶች ሀ. ግንዛቤ ወይም እምነት ለ. አስፈላጊ ባህሪያቸው ሐ. ከሌሎች የተለዩ ሁኔታዎች ላቅ ብለው የሚታዩ፣ መ. ባህሪያትን ወይም ሁነቶችን ለመገምገም የሚያስችሉ ሠ. አንፃራዊ በሆነ ቅደም ተከተል ፋይዳቸውና ጠቃሚነታቸው ተለይቶ የሚታወቅ፣ ሊሆኑ እንደሚገባ ሽዋርዝና ብሊስኪ የተባሉት ማኅበራዊ ተመራማሪዎች (Schwartz & Bilsky (1987, p. 551). ያስረዳሉ፡፡ ባህላዊ እሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡል የሆኑትን ሥርዓቶች የሚያንፀባርቁ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህም ባህላዊ እሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ በዕለት ተዕለት ሕይወት ማለትም በሰዎች አስተሳሰብ፣ በተቋማዊ ሥራዎቻቸው መንፀባረቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንዱ እሴት ስኬታማነት ቢሆን በፍትሐዊና በትምህርት ሥርዓቱም መታየት ይኖርበታል፡፡

እርግጥ ነው፣ ባህላዊ እሴትን በሚመለከት ጥናታዊ ሥራዎቻቸውን ለኅትመት ያበቁ በርካታ ሊቃውንት አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ Inglehart, 1977, 1990; Triandis, 1990; Hofstede, 1980, 1990; Bourdieu, 1972; Markus & Kitayama, 1994; Williams, 1970; Schwartz, 1994 የተባሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን እያንዳንዱ ሊቅ ባህላዊ እሴትን በሚመለከት ጥናታዊ ግኝቱን ያቀረበ ቢሆንም የየራሱ የሆነ ውስንነት እንዳለው የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን የተደረገ ጥናት፣ የተጻፈ መጽሐፍ፣ ለማግኘት ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እንደ ኤስ ሽዋርዝ ያሉ ሊቃውንት ጥናታቸውን ሁለንተናዊ የባህል እሴትን በሚመለከት በመመራመር ለንባብ ያቀረቡ ስለሆነ ከእነሱ መማር ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡

ባህል የምንለው የጋራ የሆነ እሴት ያለው ሲሆን ይህም የጋራ መግባባትን፣ ውብና መጥፎ ነገሮች፣ አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶችን፣ አዝናኝና አሰልቺ ሒደቶችን፣ ለይቶ ለማወቅ ያስችላል፡፡ ይህን የበለጠ ለመገንዘብ እንችል ዘንድ በወቅታዊና በአካባቢ ምሳሌ በጥቅሉ እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡

በመሠረቱ ጥሩ ባህላዊ እሴት የምንለው የኅብረተሰቡ ተግባብቶ፣ ተስማምቶ፣ ተቻችሎ መኖር ቢሆን ይህም ባህላዊ እሴት እንዲሁ የተፈጠረ ሳይሆን ከረጅም ዘመናት በፊት ኅብረተሰቡ ሥር እንዲሰድ አድርጎ ኮትኩቶ ስላሳደገው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቤተሰብ ልጆችን ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ ጥሩና መጥፎ ሥነ ምግባራትን ለይተው እንዲያውቁ በልዩ ልዩ መንገዶች፣ ልምዶች፣ ትውፊቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ ዘፈኖች፣ እንዲያድጉ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉ እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ጉዳዩን በሌላ ቀላል ምሳሌ ለመረዳት እንችል ዘንድ ባህላዊ ሠርግን እንውሰድ፡፡ በአንድ ሠርግ ውስጥ ኅብረተሰቡ ያዳበራቸው እሴቶችና ልማዶች ተሟልተው ይገኙባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ የሠርግ ቀን ይቆረጣል፣ በወንድና በሴት ቤት ሲደገስ ይሰነበታል፡፡ ተጋባዦች ይታደማሉ፡፡ የሰርጉ ዋዜማ ዘፈን አለ፡፡ ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ሲመጣ የሚዘፈን ዘፈንና የሚዘፍን ቡድን አለ፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ወደቤቱ ሊወስድ ሲል የሚዘፈን ዘፈን አለ፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ወደቤቱ ሲደርስ የሚዘፈን ሌላ ዘፈን አለ፡፡ ይህ በየእርከኑ የሚዘፈን ዘፈን እስክስታ ይታጀባል፡፡ ሙሽሪትና ሙሽራው ትዳር መጀመራቸው፣ አዲሱን የሕይወት ምዕራፍ ‹‹ሀ›› ብለው መጀመራቸውና ልጅ ወልደው መሳም ወላጆቻቸውን ማስደሰት እንዳለባቸው ይነገራቸዋል፡፡ ሌሎችም ከዚህ ጋር የሚሄዱ ባህላዊ እሴቶችና ባህላዊ እሴቶቹ የሚገለጡባቸው ልማዶች አሉ፡፡

ዳሩ ግን የአገራችንን ባህልና እሴቶቹን ከግምት ባለማስገባት ሠለጠንን ብለው እንደፈረንጆቹ ለመሆን ሙሽራውን አዳራሽ እንዲጠብቅ አድርገው ሙሽሪትን አባቷ ይዟት በመምጣት ለሙሽራው የማስረከብ ነገርን ስንመለከተው ጋሪው ከፈረሱ የቀደመ ሆኖ ይገኛል፡፡ ሲጀመር ለዚህ የተዘጋጀ ዘፈን የለም፡፡ ‹‹አናስገባብ በሩን፣ ሙሽራውን፣ መሄዷ ነው መሰናበቷ ነው፣ ሙሽሪት ልመጂ…›› የሚሉት ዘፈኖች ከፈረንጅኛው ጋር አብረው አይሄዱም፡፡ የራሳቸው ባህላዊ እሴትና ልማድ ስላላቸው አይገጣጠሙም፡፡ ይህ ወግ አጥባቂነት አይደለም፡፡ ባለፉት መቶ ዓመታት ጋቢና ነጠላ በካባና በባርሜጣ ተቀይረዋል፡፡ ካባና ባርኔጣ ደግሞ በኮት፣ በሸሚዝ፣ በሱሪና በከራቫት ተቀይረዋል፡፡ ጥልፍ ቀሚስ፣ ነጠላና ካባም በቬሎ ተቀይረዋል፡፡ ፈረስ በፊት በጋሪ ኋላም በመኪና ተቀይረዋል፡፡ ሞሰብ በጠረጴዛና በሰሃን ተተክተዋል፡፡ ነገር ግን ሴት ልጅን ለባል ለመስጠት አብረው የሚሄዱ ልምዶች መጎዳኘት አለባቸው፡፡

የሆነ ሆኖ መልካም ባህላዊ እሴቶቻችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከሁሉ አስቀድሞ ወላጆች በቤት ማስተማር አለባቸው፡፡ ልጆች መልካም ሥነ ምግባራቸውን በትምህርት ቤት ሊያጎለምሱ የሚችሉት በቤተሰባቸው አስፈላጊው የሥነ ምግባር ክብካቤ አግኝተው ሲያድጉ ነው፡፡ ከትምህር ቤት ጎን ለጎን የሃይማኖት ተቋማት ስለመቻቻል፣ ተፋቅሮ ስለመኖር፣ የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን፣ ወዘተ በማስተማር ጥሩ ባህላዊ እሴት ያላቸው ሆነው እንዲያድጉ ሊረዷቸው ይችላሉ፡፡ ልጆች ከኅብረተሰቡ ከሚያገኟቸው የባህል እሴቶች መካከል ትልልቅ ሰዎችን፣ አዛውንቶችን፣ ሴቶችን፣ ሊቃውንትን፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ከኅብረተሰቡ ላቅ ብለው የሚታዩ ለምሳሌ ደራሲያን፣ አትሌቶች፣ ማክበር ጥቂቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እሴት ማኅበራዊ ተቋማት (ለምሳሌ ለተቋም መሪዎች፣ ለፖሊሲ አውጭዎች፣ ለግለሰቦች) ተገቢ ዕርምጃ ለመፈጸም፣ ሰዎችንና ሁኔታዎችን ለመገምገምና ተመልሶም የወሰዱትን ድርጊትና ግምደማ ለማብራራት የሚጠቀሙበት አስፈላጊ የሆነ መርህ (Kluckhohn, 1951; Rokeach, 1973; Schwartz, 1992) የተባሉት የማኅበራዊ ኑሮ በሰሎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ትንታኔ መሠረት እሴት በሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ የግምገማ ወይም ለማኅበረሰቡ ደኅንነት፣ ደስታ፣ እርካታ፣ በራስ መተማመን፣ ልዕልና ወዘተ የሚበጀውን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል፣ በቅድመ ሁኔታና በጠቃሚነቱ ቅደም ተከተል የተመሠረተ መርህ ነው፡፡

ባህላዊ እሴት በጥቅሉ ወይም በተናጠል (አንዱን ነገር ነጥሎ በመውሰድ) ማኅበረሰቡ በጎ ነው፣ ትክክል ነው፣ አስፈላጊ ነው፣ ብሎ በጋራ የሚጠቀምበት ረቂቅ የሆነ መርህ መሆኑን በመተንተን የማኅበራዊ ኑሮ ባለሙያዎቹ በተጨማሪ ያብራራሉ (Williams, 1970)፡፡ በእነዚህ ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች ትንታኔ መሠረት ነፃነት፣ ብልፅግናና ደኅንነት፣ በተግባር ለሚገለጹ እንደ ቤተሰባዊ፣ ትምህርታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እምነታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወዘተ ልማዶች ሁሉ ዋነኛዎቹ የባህላዊ እሴቶችና መሠረቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግለሰቦች ታላቅ ነገር ለማግኘት የመፈለግና ፍላጎቱንም ማሳካት የባህል እሴት በሆነበት አካባቢ የኢኮኖሚውና የፍትሕ ሥርዓቱ ይንን ተግባር ለማከናወን የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ የኅብረተሰቡ ደኅንነት የተመሠረተ እንዲሆን ካስፈለገም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቱና የፍትሕ ሥርዓቱ አብሮ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል፡፡

ብዙ ሰዎች በባህልና በልማት መካከል ያለው ግንኙነት ማየት ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ባህላዊ እሴት ይለወጣል? ብለን ስንጠይቅ በቀጥታ በባህልና በልማት መካከል ያለውን ተደጋጋፊነት ማስተዋል እንችላለን፡፡ ልማት የኅብረተሰብ ጤናማ ዕድገት ማለት ሲሆን፣ ባህል ደግሞ ማኅበራዊ ሕይወት ማለት ነው፡፡ ይህም በተባበሩት መንግሥታት ማኅበራዊ ምክር ቤት ከ50 ዓመታት በፊት ጀምሮ (1962 ዓ.ም.) ተቀባይነት ያገኘ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም ልማት ስንል ማኅበራዊ ለውጥ ማለት ሲሆን ይህም ማኅበራዊ ለውጥ ሁሉንም ሰዎች ከላይ እስከ ታች ይነካል፡፡ እርግጥ ነው በዚህ የለውጥ ሒደት ውስጥ የአሮጌውና የአዲሱ ለውጥ ግጭት ሊኖር ይችላል፡፡ የልማት ለውጥ ቢኖርም ‹‹ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ባይኖሩ ኖሮ የበለጠ ማልማት ይቻል ነበር፤›› ወይም ከቀዳሚው የተሻለ ፍትሕና ርትዕ ቢኖርም ‹‹የአመራር ድክመት ነው እንጂ የተሻለ ሊሆን ይችል ነበር፤›› የሚሉ እንደሚኖሩ የታወቀ ነው፡፡ ልማት ሲኖር አሮጌው አስተሳሰብ በአዲስ መተካቱ የግድ ስለሆነ የአመለካከት ልዩነቶች ጎልተው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ውካታም፣ ግጭትም ይኖራል፡፡ አዲሶቹ ባህላዊ እሴቶች በሚገባ ሥር ከመስደዳቸው በፊት ነባሮቹ ባህላዊ እሴቶች የሚቀሩበት ሁኔታም ይፈጠራል፡፡ በተለይም እንደ በጎ ተደርገው ይወሰዱ የነበሩ የግለሰብና በአጠቃላይም የኅብረተሰቡ ሞራላዊ እሴቶች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡

እዚህ ላይ አዲስ ቴክኖሎጂና ሳይንሳዊ ልማት ከውጭ አስገባን ሲባል ከባህሉ፣ ከባህላዊ እሴቱና ከተግባሩ ጋር እንጂ ብቻውን ሊመጣ እንደማይችል ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ አካባቢ መኪና መንገድ ቢዘረጋ ሰዎች በእግራቸው ሲጓዙ በነበረበት ሁኔታ አይጓዙም፡፡ በበቅሎና በፈረስ ላይ ወጥቶ መጓዝና በመኪና መጓዝ አንድ ስላልሆነ ያንን አዲስ ዘዴ መላመድ አለባቸው፡፡ አንዱ ተራራ ላይ ሆኖ ወደ ሌላው ተራራ ድምፁን በማሰማት ሲጣራ የነበረ ገጠሬ በስልክ ሲናገር መጮህ አያስፈልገውም፡፡ የኤሌክትሪክ መብራት ሲያበራ እንጨት መማገድ በግዜው እፍ ማለት፣ በጭስ መታፈን የመሳሰሉት ሁሉ ይቀሩና እንዴት ራሱን ከኤሌክትሪክ አደጋ ጠብቆ ማብራትና ማጥፋት እንዳለበት ልማዱን ማዳበር አለበት፡፡ ለዘመናት በሬ ጠምዶ ሲያርስ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ ሲኖር የነበረ ገበሬ በትራክተር ማረስ ሲጀምርና አግሮ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ሲቀጥል የብቸኝነት ማኅበራዊ ኑሮው እያበቃ፣ የከተማ ኑሮ እየበለፀገ ይመጣል፡፡ በዚያው ልክም ባህላዊ እሴቱ ይለወጣል፡፡ ይሁንና ደግሞ አዲሱ ክስተት ከማኅበረሰቡ ጋር እስኪዋሃድ ድረስ በነባሩ ባህል ውስጥ ማደግ ይኖርበታል፡፡ አንዳንዶቹ ከልማት ጋር የሚመጡ የእሴት ለውጦች ሥልጠና ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን ነፃ ኢኮኖሚውንና ከነፃ ኢኮኖሚው ጋር የተያያዙትን ለማስተዋወቅ ቢፒአር፣ ካይዘን፣ ኳሊቲ ማኔጅመንት እየተባለ ሥልጠና መሰጠቱ እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ስለሆነም ባህላዊ እሴት ከልማት ጋር እየተዋጠ የሚሄድ ሲሆን ልማቱ የበለጠ እንዲፋጠን ነባሩን ባህላዊ እሴት ማስተዋል፣ ነባሩን ከድንበር ተሻጋሪው ባህል ጋር ለማጣጣም ጥረት ማድረግ፣ በየጊዜው መገምገም፣ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ 

የባህል ቅርሶችን ጠብቆ ማቆየት

ምንም እንኳን ቀደም ሲል ለማቅረብ እንደተሞከረው በልማት የሚለወጡ የባህል እሴቶች ቢኖሩም የማይለወጡ፣ የማይተኩና፣ ምንም ዓይነት መተመኛ ዋጋ የማይገኝላቸው፣ የአንድ አካባቢ ኅብረተሰብ ማንነት መለያ የሆኑ ወይም ሁሉ አቀፋዊ የሆነ ነገር ግን በአንድ አካባቢ የሚገኙ የባህል ቅርሶች እንዳይበላሹ ወይም እንዳይሰረቁ መጠበቅና ክብካቤ ማግኘት ያለባቸው የባህል ቅርሶች አሉ፡፡

 እነዚህ የባህል ቅርሶች የምንላቸው ሁሉ፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተያያዙና በጠንካራና በማያጠራጥር ረቂቅና ተጨባጭ ቅርሶች ላይ የተመሠረቱ ከመሆናቸውም በላይ የአንድን ሕዝብ ማንነት የሚያሳውቁ ከመሆናቸውም በላይ ላለውና ለመጭው ትውልድ ምን እንደሆነና ምንስ መደረግ እንዳለበት ሐሳብ የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ያለፈውን ዘመን ወደኋላ መለስ ብለን ለማየት ሰዎች በነበሩበት ዘመን በአካባቢያቸው አንዳች ለውጥ ለማምጣት ያደረጉትን ጥረት የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡ 

የባህል ቅርሶች ካለፈው ትውልድ ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችም በመሆናቸው የፈረሱት ተጠግነው፣ ለአደጋ የተጋለጡት ከጥፋት የሚያድን መከላከያ ተሠርቶላቸው ለመጭው ትውልድ መተላለፍ አለባቸው፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ ባህላዊ ቅርሶች በውስጣቸው በሚካሄድ ኬሚካላዊ ውህድ ምክንያት ሊጠፉ እንደሚችሉ በመገንዘብ ከዚህ ጥፋት እንዲድኑ ዘዴ መፈለግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ አደጋ ከሚዳረጉት በርካታ የባህል ቅርሶች መካከል በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶችና በሌሎችም የሚገኙ መጻሕፍትና ውስጣቸው የሚገኙ ጽሑፎችና ሥዕሎች፣ የሥነ ሕይወት ቅርሶች፣ ተክሎች፣ ሕንፃዎች፣ ፍልፍል ዋሻዎች ይገኙባቸዋል፡፡

በተፈጥሮ ለውጥ ምክንያት ሊከተል ከሚችለው ጥፋት በተጨማሪ በግዴለሽነት፣ በራስ ወዳድነት፣ በስርቆት ወዘተ ሊጠፉ የሚችሉ የባህል ቅርሶች ስላሉም በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥበቃና ክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በጦርነት ምክንያት መተኪያ የሌለው ልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርሶች የወደሙ ቢሆንም ወደፊት ጦርነት ሲካሄድ ባህላዊ ቅርሶች እንዳይወድሙ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢስላም የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች እንዳይጠፉ፣ በእርሻ ያለ ሰብል፣ ከብትና ንብ የመሳሰሉት እንዳይነኩ አጥብቆ የሚያስገነዝብ ሲሆን ይህን ግንዛቤ ለማዳበር ኅብረተሰቡን በሰፊው ማስተማር ይገባል፡፡

ሁሉም ኅብረተሰብ በግልጽ ሊገነዘበው የሚገባው ሌላው ዓብይ ጉዳይ ቢኖር ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነውን ቅርስ ለልጅ ልጆቻችን አጠናክረንና ጠብቀን ልናቆየው እንጂ ለወቅታዊ ፍላጎታችን ስንል ልናጠፋው የሚገባው አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የሚመለክባቸው ዛፎች፣ ወይም መቃብሮች፣ ወይም ሕንፃዎች፣ ወይም ሐውልቶች ቢኖሩ ማስተማሪያ አድርገን መጠቀም እንጂ የማውደም ሥልጣንና ሀብት ስላለን ብቻ ልናወድማቸው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜ በአገራችንና በሌሎች አገሮች በመጥፋት ላይ ያሉትን የጥንታዊ ዛፎች፣ መቃብሮች፣ ሕንፃዎች፣ ቅርሶች፣ በቅርሶቹ መውደም ምክንያት የሚከተለውን መዘዝ አውስቶ በሰፊው መነጋገር እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ለማውሳት እወዳለሁ፡፡ ለምሳሌ በኩነባ ውስጥ በሱሐባዎች መቃብር አካባቢ ሱሐባዎች ተከሉት ተብሎ የሚነገረው ዛፍ ተቆርጦ መጣሉ፣ ወይም ክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት ሲገባ በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ ከምድረ ገጽ መጥፋቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ መገንዘብ የሚኖርብን በአንዱ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ቅርስ ተብሎ የሚታሰብ በሌላው ትውልድ የማይጠቅም ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም ነቃፊውን በመንቀፍ ቀዳሚውን ትውልድ የሚያደንቅ ሌላ ተተኪ ትውልድ ሊመጣ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም አያት ቅድመ አያቶቻችን ትተውልን የሄዱ ቅርሶችን ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ እንጂ የማውደም መብት የሌለን መሆናችንና መጭው ትውልድ ሊጠይቀን የሚችል መሆኑን ተገንዝበን ልንንከባከበውና ልንጠብቀው ይገባል፡፡

 ይህም ሆኖ ቅርስን ለመጠበቅ የሚቻለው ከሁሉ አስቀድሞ ቅርሶች መሆናቸውንና ጥቅማቸውን ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ማለትም እንደ ባህልና ቱሪዝም፣ እንደ ኢኮኖሚ ልማት፣ እንደ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ሚዲያዎች፣ የታሪክ፣ የሥነ ምድር ወዘተ ምሁራን ያልተቆጠበ ጥረት ማድግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ባህላዊ ቅርሶችን መንከባከብ

ቀደም ሲል ባህላዊ ቅርስን የመጠበቅ አስፈላጊነት በመጠኑም ቢሆን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ስለእነዚሁ ባህላዊ ቅርሶች ክብካቤና የክብካቤው ሥልት ለማቅረብ ይሞከራል፡፡ ባህላዊ ቅርሶችን የምንንከባከበው፣ በወንዝ፣ በሐይቆችና በባህሮች ዳር ወይም መሀል የሚገኙ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ በዝናብ፣ በጎርፍና በማዕበል እንዳይወሰዱ መከላከያ በማድረግ፣ የቆሙ ሐውልቶች እንዳይወድቁ ድጋፍ በማድረግ፣ ሥዕሎች ቀለማቸው ጠፍቶ እንዳልነበሩ እንዳይሆኑ በነበረ መልካቸው ማደስ፣ መጻሕፍት በውኃ፣ በብል፣ በኬሚካላዊ ለውጥ እንዳይበላሹ በየጊዜ በመፈተሽ፣ የአየር ብክለትን በማስወገድ፣ ደኖችን በመንከባከብና በመተካት፣ የሚንከባከብና የሚከታተል አካል በማቋቋም፣ ኅብረተሰቡ የባህል ቅርሶችን ጠቃሚነት ተገንዝቦ እንዲንከባከባቸው በማድረግ፣ ባህላዊ ቅርሶች እንዲጠበቁና ክብካቤ እንዲያገኙ የሚያግዙ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን በማውጣት፣ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መጭው ትውልድ ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ጥቅም እንዲዳብር፣ እንዲሁም ተግባራዊ ዕርምጃ የሚወስድ ዜጋ እንዲሆን ማብቃት፣ የአንድ አካባቢ ኅብረተሰብ በአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶች ከባቢያዊ፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተረድቶ እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከባቸው ማድረግ፡፡ ሌሎችም በርካታ የክብካቤ ሥልቶችን በመቀየስ ባህላዊ ቅርሶች እንዳይበላሹ፣ እንዳይወድቁና እንዳይጠፉ ማድረግ ይቻላል፡፡

እርግጥ ነው ባህላዊ ቅርሶች እንዳይጠፉና ክብካቢ አግኝተው እንዲጠበቁ ማድረግ ከባድ ሥራንና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ከባድ ሥራና ኃላፊነት የሚጠይቅ ሥራ ግን ቀስ በቀስም ቢሆን የምንጀምረውና የምናዳብረው እንጂ በጭፍን የምንተወውና ከአቅም በላይ ነው ብለን የምንተወው አይደለም፡፡ ስለሆነም ባህላዊ ቅርሶችን ተጠብቀው እንዲቆዩና ክብካቤ እንዲያገኙ የማድረግን ሥራ መጀመርና እስከ መጨረሻው መቀጠል ይኖርብናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡