ከጎጃም ዕዝ ፋኖ የተሰጠ መግለጫ!
እንደሚታወቀው በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር እልቂትና የሕልውና ስጋት ለመቀልበስ የአማራ ፋኖ አይተኬ ዋጋ በመክፈል ትግሉን በድል እየተወጣ ይገኛል። የጠላት ሃይል ከትላንት የከፋ ወረራውን በሕዝባችን ላይ እየፈፀመ ቢገኝም ፅናትን ውርሱ ያደረገው የፋኖ ሃይል ውድ ህይወቱን አስይዞ ለክብርና ነፃነት የሚደረገውን ጉዞ እያሳለጠ ይገኛል።
ይህ ትግል አሁን ካለበት በተሻለ ፍጥነት እንዲጓዝ፣ ሁሉን አካታች እንዲሆን፣ በሕዝባችን የማጥቃት አቅም ልክ ጠላት ለአፀፋ እንዲቸገር ለማድረግ ደግሞ ‘አንድ አማራዊ’ የሆነ ወታደራዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን። በመሆኑም የጎጃም ዕዝ ፋኖ የቀጠናችንን ትስስር በማስተባበር እርሾነቱን እንዳሳዬ ሁሉ ከቀጠናችንም በመውጣት ለአንድ ወታደራዊ አደረጃጀት መወለድ ሁሉንም አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ይገደዳል።
በዚህም የወሎን እዝ መመስረት በጠንካራ ጎን የምናየው የምስራታችን ሲሆን ዕዛችን በአባይ በረሃማ ሸለቆ በሚያዋስነን ማንኛውም ቦታዎች ላይ የነበረንን ወታደራዊ መተጋገዝ ከትላንቱ በተሻለ ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው ያደርጋል።
ከዚህም በተጨማሪ የጎንደር ዕዝን ለመመስረት ከሰሞኑ የወጣውን መግለጫ የጎጃም ዕዝ በአዎንታዊ መልኩ ይመለከተዋል። የጎንደር አንጋፋ አባት፣ አርበኛ ፋኖዎችና የምንጊዜም ምልክታችን የሆኑት ታላላቆቻችን የጎንደር ዕዝን ለመመስረት በሚደረገው ሂደት ላይ የአመቻችነትና አማካሪነት ሚናን በመወጣት የጀመራችሁትን ሂደት መስማት እጅጉን አስደስቶናል።
በዕዝ ምስረታቹህ ወቅትም ዘመኑን የዋጀና አዲስ የኃይል አሰላለፍ ይዛችሁ በመውጣት ልክ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም የጠላት ሃይልን በማዛባት የትግሉ አብሪ ኮከብ ትሆኑ ዘንድ የጥሪ አደራችንን እናቀርባለን። የጎንደር ዕዝ መመስረት እዛችን በመተከልና ቋራ፣ አቸፈርና አለፋ፣ ደራና ባህርዳር እንዲሁም ሞጣና አንዳቤት በኩል የሚያደርገውን መተጋገዝ አጠናክረን ለማስቀጠል አስቻይ ሁኔታን ይፈጥርልናል።
በሌላ በኩል አባቶቻችን “ሸዋ ባላመጠ ይዉጣል በዓመቱ እንዲሉ” …ሸዋ አባ መላ፣ ሸዋ አባ ደፋር፣ ሸዋ አባ ዳኘው.. የአራት ኪሎን ጉዞ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት የምናደርገውን ጉዞ በቅርብ ርቀት ያላችሁ ደጀኖቻችን መሆናችሁን ስናስብ እንኩራራለን። በትግሉ አክራሞታችንም የጠላትን ሃይል ልኩን እንዲያውቅ በምታደርጉት ተጋድሎ ልባችን ሲሞቅ ከርሟል።
የአንድ ወታደራዊ ክንፍ መወለድ ይዞት ለሚመጣው ዘላቂ መፍትሄ ሲባል የሸዋን ዕዝ መመስረት በጥብቅ እየጠበቅን ይገኛል። ባለፉት ጥቂት ወራት ህዝባችን አንድ የተማረው ሀቅ ቢኖር የተከበርነው በኃይላችን መሆኑን ነው። ስለሆነም የአንድ አማራ ወታደራዊ አደረጃጀት መመስረት ይዞት የሚመጣው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ለእናንተ ለወንድሞቻችን ማስረዳት ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብናል።
በሁሉም የአማራ ጠቅላይ ዕርስት የምትገኙ ውድ ፋኖ ወንድሞቻችን በምትመሩትም ሆነ በምትመሩበት ተቋም ውስጥ የትህትናና ቅንነት መንፈስ በማሳየት ለሚመሰረቱ ዕዞች ሁሉ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ‘የአንድ አማራ ወታደራዊ አደረጃጀትን’ መወለድ እንድናፋጥን ስንል ጥሪ እናቀርባለን። በአንድ ተቋም መመስረት ውስጥ ሶስት ነገሮች አሉ። አንደኛው የትግሉን ግብ የሚያስቀጥሉ ሁለተኛው ተልዕኮ የተቀበሉ ሰላዮችና ሶስተኛው የትግሉን ውጣውረድ በመጠቀም ለማምለጥ የሚፈልጉ የገንዘብና ስልጣን ሞጭላፊዎች ናቸው።
እኛም ራሳችንን የአንደኛው ረድፍ ላይ ብቻ በማድረግ ማለትም የትግሉን ግብ በማስቀጥልና ፀንተን በመቆም ከሁለተኛና ሶስተኛ ረድፍ በመውጣት መዋቅራዊ ጥቃት ለሚደርስበት ህዝባችን መዋቅራዊ ምላሽ እንድንሰጥ ስንል ጥሪ እናቀርባለን።
ድል ለተገፋው የአማራ ህዝብ!
ድል ለፋኖ!
ጎጃም ዕዝ ፋኖ
ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም