
ከ 5 ሰአት በፊት
በሜክሲኮ አንድ ተሳፋሪ የአደጋ ጊዜ መውጫ በርን ከፍቶ የአውሮፕላኑ ክንፍ ላይ ከተራመደ በኋላ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ግለሰቡ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ከፍቶ የአውሮፕላኑ ክንፍ ላይ የተራመደው ከሜክሲኮ ወደ ጓቲማላ ሊበር የነበረው አውሮፕላን በቴክኒክ ችግር ለሰዓታት መዘግየት ካጋጠመው በኋላ ነው።
የሜክሲኮ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በክስተቱ ምክንያት በሰው ላይም ይሁን በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቆ ግለሰቡ ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል ብሏል።
ይሁን እንጂ በኤሮሜክሲኮ አየር መንግድ አውሮፕላን ላይ ተሳፍረው የነበሩት ተሳፋሪዎች ድጋፋቸውን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩን ለከፈተው ግለሰብ ሰጥተዋል።
ተጓዦቹ መዘግየት ባጋጠመው አውሮፕላን ውስጥ ያለ አየር ማቀዝቀዣ እና ምግብ ለረዥም ሰዓት በአውሮፕላን ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸው ለሕይወታቸው አደገኛ ሁኔታን ፈጥሮ እንደነበረ ገልጸዋል።
- ወደፊት ሊከሰት የሚችለው ‘ወረርሽኝ ኤክስ’ ምንድነው? ከኮቪድ የበለጠ ሕዝብ ሊጨርስ ይችላል?ከ 6 ሰአት በፊት
- እንደተወለዱ ተሰርቀው የተሸጡት መንትዮች እንዴት በቲክቶክ አማካይነት ተገናኙ?ከ 6 ሰአት በፊት
- የአቶ ደመቀ ስንብት እና የሁለት አስርታት ሚናቸው27 ጥር 2024
ይህ ክስተት ያጋጠመው ባሳለፍነው ሐሙስ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 11፡30 አካባቢ ላይ ነው። ከሜክሲኮ ሲቲ ወደ ጓቲማላ ሊበር የነበረው አውሮፕላን በጥገና ምክንያት መቀየር ስለነበረበት ተጓዦች ቢያንስ ለሦስት ሰዓታት ያክል በአውሮፕላን ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል።
በስም ያልተጠቀሰው የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩን የከፈተው ግለሰብ ለፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል ይባል እንጂ አሁንም በቁጥጥር ስር ውሎ ስለመገኘቱ አልያም ደግሞ ክስ ተመስርቶበት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
በበረራው መዘግየት እጅግ ተበሳጭተው የነበሩት ተጓዦች ግን በሌላ አውሮፕላን ጉዟቸውን ቀጥለዋል።
ተሳፋሪዎቹ በማሕበራዊ ሚዲያ ባሰራጩት በእጅ የተጻፈ ጽሑፍ ግለሰቡ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩን የከፈተው “በሁሉም ሰው ድጋፍ ለሁሉም ተሳፋሪዎች ደኅንነት ሲባል ነው” ብለዋል።
ተሳፋሪዎቹ ለሰዓታት በአውሮፕላኑ ውስጥ እንዲቆዩ በመደረጋቸው በአየር እጥረት “አደገኛ የጤና ሁኔታ” ተከስቶ ነበር ብለዋል።
“ሕይወታችንን ታድጓል” ሲሉ ተሳፋሪዎች ስም እና ፊርማቸው ያረፈበትን ጽሑፍ በስፋት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አሰራጭተዋል።