
ከ 4 ሰአት በፊት
በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን አያያዝ የሚቃወሙ ሁለት ሴቶች በፈረንሳይ ሙዚየም ውስጥ በሚገኘው የሊዎናርዶ ዳቪንቼ የሥዕል ሥራ በሆነችው ሞና ሊዛ ላይ ሾርባ ደፍተዋል።
ተቃዋሚዎቹ በመስታወት በተሸፈነው ስዕል ላይ የዱባ ሾርባ ከደፉ በኋላ ጤናማ እና ዘላቂ የምግብ አቅርቦት ይኑር የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተሳለችው እና በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኘው ዘ ሉቭ ሙዝየም የምትገኘ ሞና ሊዛ በዓለም ላይ እጅግ እውቅ ከሆኑ የሥነ ጥበብ ሥራዎች መካከል አንዷ ናት።
ክስተቱን ተከትሎ ሙዚየሙ በሰጠው መግለጫ የጥበብ ሥራው በጠንካራ መስታወት ስለተከለለ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።
ሞና ሊዛ ሥዕል ላይ ሾርባ የደፉት ሁለት ሴቶች፤ “ጠቃሚው የቱ ነው? ጥበብ ወይስ ጤና እና ዘላቂ የምግብ አቅርቦት?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ቀጥለው “የግብርና ሥርዓታችን ታሟል። ገበሬዎቻችን እየሞቱ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
‘ሪፖስቴ አልሜንቴር’ የተሰኘ ቡድን ለድርጊቱ ኃላፊነት እንደሚወስድ ገልጿል።
ቡድኑ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ሞና ሊዛ ላይ ፈሳሽ መድፋት ያስፈለገው የምግብ አቅርቦት የማኅበራዊ ዋስትና አካል እንዲሆን የሚደረገው ጥረት ክፍል ነው ብሏል።
ቀጥሎም አሁን ያለው የምግብ አቅርቦት ሥርዓት “መሠረታዊ የሆነውን የምግብ መብት” አያካትትም ሲል ወቅሷል።
ይህ ቡድን ለዜጎች በየወሩ 150 ዩሮ የሚገመት የምግብ ‘ኩፖን’ እንዲሰጥ ጠይቋል።
- ወደፊት ሊከሰት የሚችለው ‘ወረርሽኝ ኤክስ’ ምንድነው? ከኮቪድ የበለጠ ሕዝብ ሊጨርስ ይችላል?ከ 6 ሰአት በፊት
- ግብጽ ከአፍሪካ ዋንጫ ውጭ ሆነችከ 5 ሰአት በፊት
- የሜክሲኮ አየር መንገድ ተሳፋሪ የአውሮፕላን በር ከፍቶ ክንፉ ላይ ተራመደከ 5 ሰአት በፊት
የፈረንሳይ ባሕል ሚኒስትር ራቺዳ ዳቲ ምንም አይነት ምክንያት ሞና ሊዛን ዒላማ ማድረግን ትክክል አያደርገውም ብለዋል።
ይህንን መልዕክት በኤክስ ገጻቸው ያሰፈሩት ሚኒስትሯ “ቅራስችን ለመጪው ትውልድ ሊቀር ይገባል” ሲሉ አክለዋል።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በፈረንሳይ ገበሬዎች ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ። ተቃውሟቸውም የነዳጅ ዋጋ መናር እንዲቆም እና የሚደረግባቸው ቁጥጥር እንዲላላ የሚጠይቅ ነው። በዚህም ምክንያት የፓሪስ መግቢያ እና መውጫ መንገዶችን ዘግተው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1950 አንድ ጎብኚ ሞና ሊዛ ላይ አሲድ ደፍቶ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ሥዕሉ መስታወት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል።
ከአራት ዓመት በፊት ደግሞ ሥዕሉን የመጠበቂያ መስታወትን ጥንካሬ በማሳደግ ጥይት የማይበሳው ሆኖ ተዘጋጅቷል።
በ2022 “ስለ ምድራችን እናስብ” ያሉ ተሟጋች ሞና ሊዛ ሥዕል ላይ ኬክ ወርውረው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1911 ደግሞ ሞና ሊዛ ተሰርቃ ነበር። የሙዚየሙ ሠራተኛ የነበረ ቪንሴንዞ ፔሩጊያ የተባለ ግለሰብ ሥዕሉን ቁም ሳጥን ውስጥ በመደበቅ ይዟ ተሰውሯል።
ሆኖም ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ጣልያን ውስጥ ጥንታዊ ቅርሶችን ለሚገዛ ግለሰብ ለመሸጥ ሲሞክር ተይዟል።