January 29, 2024 – Konjit Sitotaw
በኢትዮጵያ ከ77 ሺ የሚጠጋ የካንሠር ህሙማን 12 ሺ ያህሉ ብቻ ሕክምናውን እንደሚያገኙ ተገለፀ።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመዘገበው 77 ሺህ የሚጠጋ የካንሠር ህሙማን 12 ሺህ ያህሉ ብቻ ሕክምናውን እንደሚያገኙ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
ወደ ሕክምና ከሚመጡት 75 በመቶዎቹ ህመሙ ውስብስብ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ የሚመጡ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ይህም የታማሚውን ታክሞ የመዳን ዕድል በመቀነስና ሕክምናውንም የበለጠ ውድ የሚያደርገው መሆኑ ተገልጿል።
የመሠረተ ልማትና የማኅበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት፣ በሚፈለገው ልክ የሕክምና ባለሙያ አለመኖር፣ ለሕክምናው የሚውሉ ዕቃዎች ከውጭ ሀገር የሚገቡ መሆናቸውና ለግዥ ረዥም ጊዜ መውሰዱ፣ ብልሽት ሲያጋጥምም መለዋወጫ በቀላሉ አለመገኘቱ የሕክምናውን ተደራሽነት ውስን ማድረጋቸው ተመላክቷል።
ሁለንተናዊ የካንሠር ሕክምና አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ በሐዋሳ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ በአይደር ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በሐሮማያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከእነዚህ መካከል ጥቁር አንበሳ፣ ጅማና ሐሮማያ የጨረር ሕክምና እየሰጡ መሆኑ ሲገለፅ በሌላ በኩል የማህጸን በር ካንሠር ቅድመ ልየታና ሕክምና ከ1 ሺህ 300 በላይ የመንግሥት ጤና ተቋማት እንደሚሰጥ ኤፍቢሲ ዘግቧል።