አዲስ አበባ ተዘዋሩአቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ዶ/ር ካሳ ተሻገርየምስሉ መግለጫ,

አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ዶ/ር ካሳ ተሻገር

29 ጥር 2024, 17:31 EAT

ከወራት በፊት በፀጥታ ኃይሎች ተይዘው አዋሽ አርባ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ማዕከል ውስጥ በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል የምክር ቤት አባሎች እና አንድ ጋዜጠኛ ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸው ተነገረ።በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውለው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለወራት ከቆዩት ታሳሪዎች መካከል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።በተጨማሪም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እንዲሁም ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውም በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን ቢቢሲ ለታሳሪዎቹ ቅርበት ካላቸው ምንጮች ማረጋገጥ ችሏል።ስድስት ወራት ሊሞላው የተቃረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የታሰሩት አቶ ክርስቲያን እና አቶ ዮሐንስ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የተዘዋወሩት ትላንት እሁድ ጥር 19/2016 ዓ.ም. መሆኑን ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሦስት የተለያዩ የቢቢሲ ምንጮች አረጋግጠዋል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰነዝሯቸው ትችት እና አስተያየቶች የሚታወቁት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባሉ አቶ ክርስቲያን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ነበር።የገዢው ብልጽግና ፓርቲ አባል እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ በነሐሴ ወር የተያዙት በአማራ ክልል ዋና ከተማ ከባሕር ዳር ከተማ ነበር።

ፖለቲከኞቹ በተለያዩ ከተማዎች ቢያዙም ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 24/2015 ዓ.ም. ባሉ ቀናት አፋር ክልል አዋሽ አርባ አካባቢ ወደሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ መወሰዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ነሐሴ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።ላለፉት አምስት ወራት በወታደራዊው ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የቆዩት የምክር ቤት አባላቱ “ሰውነታቸው እንደከሳ እና እንደተጎሳቆለ” ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች በትላንትናው ዕለት ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሲገቡ በቦታው የነበሩ አንድ ምንጭ “ሁሉም ሌላ ሰው ነው የሚመስሉት” ሲሉ በታሳሪዎቹ የሰውነት ገጽታ ላይ የተመለከቱትን ለውጥ ገልጸዋል።አቶ ዮሐንስ እግራቸው ላይ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ከሁለት ወራት ገደማ በፊት ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንደነበር ያስታወሱ አንድ ምንጭ፤ በወቅቱ ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ “ህክምናቸውን ሳይጨርሱ” ወደ ወደ አዋሽ አርባ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት አሁንም ይህ በሽታ እያገረሸባቸው መሆኑን አክለዋል።በአሁን ወቅት ፖለቲከኞቹ በምን ምክንያት ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ እንደተደረገ እስካሁን ድረስ እንዳልተገለጸላቸው ምንጮቹ ገልጸዋል።በተመሳሳይ መልኩ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለአምስት ወራት ገደማ ታስረው የቆዩት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ እና ጋዜጠኛ በቃሉ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ አረጋግጧል።እንደ ምንጮቹ ገለጻ በአዋሽ አርባ የነበሩት ዶ/ር ከሳ እና ጋዜጠኛ በቃሉ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነው። ሁለቱም ታሳሪዎች በመዲናዋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ መሆኑ ተነግሯል።የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ በአዋሽ አርባ ካምፕ ውስጥ 53 ታሳሪዎችን መጎብኘቱን ገልጾ ነበር። ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው ታሳሪዎቹ ወደ አዋሽ አርባ እንዲታሰሩ የተደረገው በአዲስ አበባ ያለው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ “በመጣበቡ ነው” የሚል ማብራሪያ ከፌዴራል ፖሊስ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር።በአዋሽ አርባ ታስረው አሁን ወደ አዲስ አበባ የተዘዋወሩት ፖለቲከኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ለረጅም ጊዜም ከቤተሰብ እና ጠበቃ ጋር መገናኘት አልቻሉም ነበር።በአማራ ክልል እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን ለስድስት ወራት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚቀጥለው ሳምንት ስድስት ወር የሚሆነው ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያበቃ ወይም እንዲራዘም ሊያደርግ ይችላል።