በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሲያካሂድ (ፎቶ ፋይል)
የምስሉ መግለጫ,በፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሲያካሂድ (ፎቶ ፋይል)

29 ጥር 2024, 11:58 EAT

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ማምሻውን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ሊመክር መሆኑ ተሰምቷል።

ይህ በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብን በፈጠረው ጉዳይ ላይ የሚካሄደው ውይይት በዝግ የሚከናወን ሲሆን ስብሰባ “የአፍሪካ ሠላም እና ፀጥታ” በሚል ርዕስ እንደሚካሄድ ታውቋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሀና ስርዌ ቴተ ቀርበው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አንድ ወር ሊሞላው የተቃረበው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት የድርጅቱን ቻርተር ጥሷል በሚል ምክር ቤቱ ስብሰባ እንዲቀመጥ ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት ጥያቄ አቀርባ ነበር።

የወሩ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ፈረንሳይ የዛሬውን ስብሰባውን መጥራቷ ታውቋል።

ፈረንሳይ ‘ኤ ፕላስ ዋን’ ከሚባለው እና አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሴራ ሊዮን እና ጉያናን ካቀፈው ቡድን ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በተደጋጋሚ ውይይት አድርጋለች።

እነዚህ አገራት ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ ጋር በተናጠል ውይይት ማድረጋቸውም ታውቋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. በመሪዎቻቸው መካከል በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ በበኩሏ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ ስምምነት ደርሰዋል።

ይህም ሶማሊላንድን የግዛቱ አንድ አካል እንደሆነች የሚገልጸው የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱን አጥብቆ በመቃወም፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ድርጊት ነው በማለቱ በአካባቢው ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት በቀጣናው ላይ ውጥረት ከፈጠረ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

በአንድ ወር ውስጥ ይፈጸማል በተባለው በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለወታደራዊ እና ንግድ አገልግሎት የሚውል የባሕር በር ታገኛለች።

ኢትዮጵያ በምላሹ ሶማሊላንድን እንደ አገር የሚያስቆጥራትን እውቅና ለመስጠት መስማማቷን የሃርጌሳ ባለሥልጠናት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ስምምነት የፈጸመው ጉዳዩን በጥልቀት አጢኖ አቋም ለመያዝ መሆኑን አስታውቋል። ከዚህ ባሻገር ግን ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖራት የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጹ ይታወሳል።

ሞቃዲሾ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጻፈችው ደብዳቤ ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት “የሚጥስ ነው” ብላለች።

“ያለ ሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት ፍቃድ ወይም ዕውቅና የተደረሰው ስምምነት የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት የሚጥስ ነው” ከማለት ባለፈ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሠላምን እና ደኅንነትን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ምክር ቤቱ “የኢትዮጵያን ግልጽ ጥሰቶች በፍጥነት እንዲያወግዝ” እና የዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያስከበር ጠይቃለች።

ኢትዮጵያ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ እንዳይሰበሰብና ችግሩን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በፃፈችው ደብዳቤ አሳውቃ ነበር።

ኢትዮጵያ የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራመችው ከዓለም አቀፍ ደንቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ መሆኑን እና ባሕር በር ለማግኘት መንገድ እንደሚከፍትላት አስታውቃለች።

በሁለቱ አገራት መካከል ንግግር እንዲያመቻቹ በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በተሾሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኩል ለመነጋገር መዘጋጀቷን በመጥቀስም የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እንዳይመከር ጠይቃለች።

በስብሰባው ለምክር ቤቱ አባላት በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ሀሳብ እንዲለዋወጡ እና ቀጠናዊ ሠላምን፣ መረጋጋትን እና ደኅንነት በሚጠበቅበት መንገድ ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የአረብ ሊግ በተናጠል ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ያልተሳታፈችበት የኢጋድ ስብሰባ አገራቱ ውጥረቱን በማርገብ ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ፣ የአረብ ሊግ ደግሞ ኢትዮጵያን በማውገዝ ለሶማሊያ ድጋፉን ገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ እና የሰሜን ሶማሊያ ግዛት (ሶማሊላንድ) የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰበው አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉም የኅብረቱ አባል አገራት “ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ነጻነት” እንዲጠበቅ “ጠንካራ ቁርጠኝነት እና ድጋፍ” እንዳለው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ተወካዮች በተገኙበት ውይይቱን ያካሄደው ምክር ቤቱ፤ ሁለቱ አገራት የተፈጠረው ውጥረት ግንኙነታቸውን ሊያበላሽ ከሚችሉ ተጨማሪ ድርጊቶችን ከመፈጸም እና እርምጃዎችን ይፋ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

ቻይና፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካን እና የአውሮፓ ህብረት ጨምሮ በርካታ አገራት በሁለቱ ወገኖች መካከል እየጨመረ ያለው ውጥረት እንዳሳስባቸው ገልጸዋል። የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የማክበርን አስፈላጊነትንም አስምረውበታል።

በተባበሩት መንግሥታት በሚካሄደው ስብሰባ ላይ በርካታ አባላት በቀጠናው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን እንደሚያሳስባቸው እና ሁለቱም ወገኖች ጉዳዩን በውይይት እና በመተባበር እንዲፈቱት ያሰምሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።