
29 ጥር 2024, 12:16 EAT
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 192016 ዓ.ም. በጣሊያን መዲና ሮም በተከናወነ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተባባሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ትልቁ ሽልማት የሆነውን አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የፋኦን ሜዳሊያ ከድርጅቱ ዳይሬክተር ጄኔራል ኪዩ ዶንግዩን እጅ ተቀብለዋል።
የአግሪኮላ ሜዳሊያ ድህነትን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትና እና የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ለሠሩ ታዋቂ ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ትልቁ የፋኦ ሽልማት ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ የተበረከተላቸው “በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት” እንዲሁም “. . . በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ነው” ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማቱን ከተረከቡ በኋላ በማኅብራዊ ድረ-ገጻቸው “ፋኦ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት የከበረውን አግሪኮላ ሜዳልያ ስላጎናፀፈን ምስጋናዬን ለመግለፅ እወዳለሁ” ብለዋል።
የፋኦ ዳይሬክተር ጄኔራል ኪዩ ዶንግዩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተከበረ የፋኦ ሽልማትን በመረከባቸው እንኳን ደስ ያልዎ ያሏቸው ሲሆን፣ ሽልማቱ የተበረከተላቸው ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ በኢትዮጵያ የገጠር እና የምጣኔ ሃብት ልማት ሥራዎቻቸው እና የአረንጓዴ አሻራ የግል ጥረታቸው ነው ብለዋል።
- ወደፊት ሊከሰት የሚችለው ‘ወረርሽኝ ኤክስ’ ምንድነው? ከኮቪድ የበለጠ ሕዝብ ሊጨርስ ይችላል?29 ጥር 2024
- የኢትዮጵያው አምባሳደር የሶማሊያን ሕዝብ እና መንግሥት ይቅርታ ጠየቁ29 ጥር 2024
- የአፍሪካ ዋንጫ፡ የራስዎን ምርጥ 11 ይምረጡ27 ጥር 2024
ከሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በኋላ ፋኦ ባወጣው መግለጫ የፋኦ ዳይሬክተር ጄኔራል ባለፉት 5 ዓመታት አስቸጋሪ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ባሉበት ሁኔታ በጠቅላይ ሚንስትሩ “ውጤታማ፣ ተጠያቂነት ያለው እና የተረጋጋ አመራር” የኢትዮጵያን አስደናቂ ዕድገት ተመልክተናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት 5 ዓመታት በኢትዮጵያ የእርሻ መሬት በ50 በመቶ እንዲጨምር መደረጉን እና ይህም በተለይ የስንዴ እና የሩዝ ምርት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማስቻሉን መግለጻቸውን ፋኦ አስነብቧል።
ከዚህ በተጨማሪም በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ሲረከቡ ኢትዮጵያ የውስጥ ፍላጎቷን ለማሟላት ስንዴ ከውጪ ስታስገባ መቆየቷን እና አሁን ግን አገሪቱ ፍላጎቷን አሟልታ ከእአአ 2023 ጀምሮ ስንዴ ለውጭ ገበያ መላክ መጀመሯን ስለመናገራቸው በፋኦ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፋኦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ሽልማቱን ከሰጠ በኋላ የተቃውሞ ድምጾችም ተሰምተዋል።
በርካታ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የማኅብረሰብ አንቂዎች “በሚሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ላላት አገር መሪ ይህ ሽልማት አይገባም” ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
እንደ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) አሃዝ ከሆነ በኢትዮጵያ ከ28 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ይፈልጋል።
በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭት፣ በበሽታ፣ በምግብ እና በሸቀጦች ዋጋ ግሸበት ምክንያቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በርካታ ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ኦቻ ይገልጻል።
አንድ አስተያየት ሰጪ ፋኦ ይህን ሽልማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መስጠቱ የረሃብ አደጋ የተጋረጠባቸውን ዜጎች ፊት መንሳት ነው ብለዋል።
ይዘቱን Twitter ይፈቅዳሉ?
ይህ ጽሑፍ በTwitter. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የTwitter ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continueየቪዲዮ መግለጫ,ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።
የ Twitter ይዘት መጨረሻ
ብዙዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው ባልተረጋገጠበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱን መስጠት አግባብ አይደለም ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አገሪቱ የአገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎቷን ከማሟላት ባሻገር ከ30 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ወደ ውጭ የመላክ አቅም መፈጥሯን ሲገልጽ ቆይቷል።
እአአ 1945 የተቋቋመው የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት- ፋኦ በመላው ዓለም ረሃብን ለማጥፋት፣ የተመጣጠን ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚመራ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ ነው።
ይህን አግሪኮላ የተባለ ሜዳሊያን ከዚህ ቀደም በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ የአገራት መሪዎች እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ወስደዋል።
የፋኦ ዳይሬክተር ጄኔራል ኪዩ ዶንግዩን እአአ 2019 ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማቱ የተበረከተላቸው የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም የአግሪኮላ ሜዳሊያን ከተረከቡት መካከል የቀድሞ የታይላንድ ንጉሥ ባሁሚቦለ አዱለያዴጅ፣ የቀድሞ ፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ፣ የቀድሞው የቻይና ፕሬዝዳንት ጂያንግ ዜሚኒ ይገኙበታል።
በተጨማሪም በሞት የተለዩት የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ፣ የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ፣ የቀድሞ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆዜ ማሪያ አዝናር እንዲሁም የቀድሞ የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮሐነስ ራኡ ይገኙበታል።