
ከ 8 ሰአት በፊት
የየመን ታጣቂ ኃይል የሆኑት ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት በመሸሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መርከቦች በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ በኩል መንገዳቸውን እንዲያደርጉ እየተገደዱ ነው።
ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ወሳኝ ጭነቶች የሚያዘዋውሩትን የዓለማችንን ትልልቅ መርከቦች የጉዞ አቅጣጫ መቀየር ምን ያህል ቀላል ነው?
በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ንብረት የሆነችው ኤምቪ ጄንኮ ፒካርዲ የተሰኘች የንግድ መርከብ ቀይ ባሕር ላይ በሁቲ አማፂያን የድሮን ጥቃት ደርሶባታል። ይህ በአንድ ወቅት በዓለማችን መርከበኞች የሚመረጠው የባሕር መስመር አሁን አደገኛ ተብሎ ለመሰየም በቅቷል።
ከኅዳር ወር ወዲህ የየመን የሁቲ አማጺያን ቡድን ባብ አል-ማንዳብን ኢላማ አድርገዋል። ይህ 32 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሰርጥ ሰሜን-ምሥራቅ አፍሪካን ከየመን የሚለይ ነው።
ለዚህ ጥቃትም የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ምክንያት ሆኗል። የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ ታጣቂዎቹ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ዒላማ አድርገናል ይላሉ።
እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ጠላፊዎችን ጨምሮ ሚሳኤሎችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጭምር ለጥቃት ውለዋል።
በዚህ ሁሉ ሁከት ውስጥ ለተያዙ መርከቦች እና መርከበኞች ሁኔታው አስፈሪ ነው። የነዳጅ መርከብን ለምሳሌ ብንወስድ አንድ ሚሊዮን በርሜል ተቀጣጣይ ነዳጅ ሊይዝ ይችላል።
ፎስፌት ሮክን የጫነው የኤምቪ ጄንኮ ፒካርዲ መርከበኞች ምንም ጉዳት ባይደርስባቸውም፣ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቱ በመርከቧ ላይ እሳት ተነስቶ ማጥፋት ችለዋል።
በጣም አደገኛ ወደ ሆነው የቀይ ባሕር መስመር የገቡ ከ300 ያላነሱ መርከቦችን መቁጠራቸውን ሚሼል ዊስ ቦክማን ገልጻ፣ ይህ ግን ማንም እንዲገጥመው የሚመኘው አይደለም ስትል ትናገራለች።
የሎይድ ሊስት ኢንተለጀንስ ዋና ተንታኟ “እነዚህ 300 መርከቦች እያንዳንዳቸው ከ15 እስከ 25 ሠራተኞች አሉት። ተሳፋሪዎችን ጭኖ የሚሄድ አውቶቡስ ወደ ጦር ቀጠና እንደመግባት ይቆጠራል” ብላለች።
- በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን ለምን ከአሜሪካ እና አጋሮቿ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባትን መረጡ?28 ጥር 2024
- ቀይ ባሕርን ያወከውን የሁቲዎች ጥቃት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ይሳካ ይሆን?23 ጥር 2024

በየዓመቱ 12 በመቶ የሚሆነው የዓለም ንግድ በቀይ ባሕር በኩል ያልፋል። የዚህም ዋጋ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ነው። በርካታ የመርከብ ድርጅቶች ይህንን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ መቀጠቀም እያቆሙ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ግዙፍ የእቃ ጫኝ መርከቦች (አንዳንዶቹ ከ300 ሜትር በላይ የሚረዝሙ ናቸው) ከእስያ ወደ አውሮፓ በሚደርጓቸው ጉዞዎች በቀይ ባሕር በኩል ወደ ሱዩዝ ካናል ከማለፍ ይልቅ በደቡብ አፍሪካ በኩል ረጅም ጉዞን እየመረጡ ነው።
እንደነዚህ ዓይነት ትላልቅ መርከቦችን የጉዞ አቅጣጫ ማስቀየር ቀላል ሥራ አይደለም። የሚያስፈልገው ሎጂስቲክስ ብዙ ሲሆን፣ ረዥም ጊዜም የሚወስድ ሊሆን ይችላል።
ከባድ ድርቅ በፓናማ ካናል ላይ ያደረሰው ጉዳት እና በጥቁር ባሕር በኩል የእህል ጭነትን ያስቀረው የዩክሬን ጦርነትም ሌላው ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለትን አንቆ የያዘ ጉዳይ ነው።
በዚህ ምክንያት የጉዞ አቅጣጫ መቀየር ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። ይህ ግን ከባድ የገንዘብ እና የአካባቢ ጉዳት መዘዞችን ሊያስከትልም ይችላል።
ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ሁቲዎች አንዲት የመኪና ማጓጓዣ መርከብን ጠልፈው ሂደቱን የሚያሳይ ቪዲዮ ለዓለም ይፋ አድርገዋል። አውዳሚ የጦር መሳሪያቸው ጭነት መርከቦችን መትቷል። በስህተትም አጠገቡ የነበረ የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ለጥቂት አምልጧል።
መርከቦችን ለመጠበቅ እና የሁቲዎችን ጥቃት ለመከላከል የታቀዱ ወታደራዊ ዘመቻዎችም በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ወታደሮች እየተከናወኑ ነው።
በሕይወት እና በአካል ላይ ሊደርስ ከሚችለው ጉዳት በተጨማሪ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ የኢንሹራንስ አረቦን፣ ሕጋዊ ጉዳዮችን እና ያልተጠበቁ መዘግየቶችን ሊያስከትል ይችላል።
እነዚህ መርከቦች የተሸከሙት ጭነት እስከ መቶ ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ የመርከብ ኩባንያዎቹ የመርከቦቻቸውን የጉዞ መስመር ለመቀየር መወሰናቸው ምንም አያስደንቅም።
አቅጣጫ በመቀየር ከቀይ ባሕር፣ በኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ረዥም ጉዞ ማድረጋቸው እያንዳንዱን ጉዞ በ6 ሺህ 500 ኪሜ እና ከ10 እስከ 12 ቀናት ያራዝመዋል። ለጉዞውም ተጨማሪ ነዳጅ ያስፈልጋል (በአንዳንድ ግምቶች መሠረት የዚህ ነዳጅ ዋጋ አንድ ሚሊዮን ዶላር ይሆናል።)
ምናልባትም አማራጭ ወደቦችን መፈለግ፣ የጊዜ ሰሌዳ ማስተካከያ ወጪ መጨመርን ያካትታል። በርካታ ኩባንያዎች የሚሳዔል እና የአጋቾች ሰለባ ከመሆን ይህንን ረዥም ጉዞ ምርጫቸው እያደረጉ ነው።

የኮንቴይነር ድርጅቶች መርከቦቻቸው በቀይ ባሕር በኩል እንዳይሄዱ ለማስቀረት፣ ለረዥሙ ጉዞ በቂ መርከቦችን ለመከራየት እየተሽቀዳደሙ ነው። የሸቀጦች የዋጋ ንረት እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ለማጓጓዝ የሚፈጀውን ጊዜ በመጨመር ይህ ቀውስ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የሎይድ ሊስት ኢንተለጀንስ ባልደረባዋ ሚሼል ቦክማን ሁቲዎች መርከቦችን መለየት አቁመዋል ትላለች። ይህንን ሃሳብ የአሜሪከ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤትም አስተጋብቶታል።
በማሳቹሴትስ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚስት የሆኑት አና ናጉርኒ ጉዳዩን በቅረበት በመከታተል ላይ ይገኛሉ። ፓስፊክ ውቅያኖስን ከአትላንቲክ ጋር የሚያገናኘው የፓናማ ካናል በድርቅ ምክንያት ለጉዞ የማይመች በመሆኑ የዓለም ንግድን አስተጓጉሎታል።
“በርካታ የቻይና መርከቦች ፓናማ ካናልን በመተው የሱዩዝ ካናልን መጠቀም ጀምረው ነበር። አሁን ግን ይኼኛውም መንገድ ችግር ገጥሞታል” ብላለች።
በደቡብ አፍሪካ በኩል ረዥም ጉዞ ማድረግ በጣም የተጋነነ ቢመስልም የመርከብ ኩባንያዎች ይህንን መንገድ በተለያየ ምክንያት ተጠቅመውበታል። አሁን ካለው ግዙፍ ጭነት አንጻር ምንም ዓይነት አማራጮች የላቸውም ትላለች ናጉርኒ።
በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የመርከብ ማጓጓዣ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የሜርስክ ቃል አቀባይ፣ ጭነት መርከቦች ሊሸከሙት በሚችሉት ከፍተኛ መጠን ምክንያት በባቡር እና በአየር መጓጓዝ የማይችሉ ጭነቶች እንዳሉ አጥብቀው ይናገራሉ።
አንዳንድ ጊዜ በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚጓዙ መርከቦች በሚያጋጥማቸው አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት ይህ መንገድ በራሱ አደጋ አለበት ብላለች።
በማጓጓዣ እና በሎጂስቲክስ ላይ የተሠማሩ ኩባንያዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጭነትን ወደ ሚፈልግበት በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፣ የዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥም በጣም ጠንካራ ናቸው ብለላች ቦክማን። አሁን ያለው የቀይ ባሕር ችግር ለመርከብ ኢንዱስትሪው “እንደ አርማጌዶን” መታየት የለበትም ትላለች።
በምሳሌነት የሚጠቀሰው ዩክሬናውያን በጥቁር ባሕር ላይ ያሉት የሩሲያ የባሕር ኃይል መርከቦች በእህል መርከቦቻቸው ላይ ያደረሱትን ስጋት እንዴት እንደተወጡት ነው።
ናጉርኒ እና ባልደረቦቿ ለዚህ ችግር የሚሰጠውን ያልተለመደ ምላሽ አጥንተዋል። በዚህም ዩክሬን በሚሊዮን የሚቆጠር ቶን እህል በዳኒዩብ ወንዝ በኩል ወይንም በየብስ ወደ ሩሜኒያ የባሕር ወደቦች በማድረስ ተለዋጭ መስመሮችን ተጠቅማለች።

የእነዚህን ግዙፍ የጭነት መርከቦች የጉዞ አቅጣጫን ማስቀየር ከባድ መዘዝ የለውም ማለት ግን አይደለም። የተጠቃሚዎችን ኪስ የሚጎዱ ተጨማሪ ወጪዎች መኖራቸው ሪፖርት እየተደረገ ነው።
በለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር ፕሮፌሰር የሆኑት ኤዲ አንደርሰን እንደተናገሩት የማጓጓዣ ዋጋዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የደረሱበት ደረጃዎች ላይ አይደርሱም። ከፍተኛ ክፍያ መኖሩ አምራቾች ምርቶቻቸውን በአየር ከመላክ እንቅፋት አይሆንባቸውም።
ዋናው ጥያቄ የቀይ ባሕር ቀውስ ለምን ያህል ጊዜ ይቀጥላል የሚለው ነው። የማጓጓዣ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች ለወራት ሊቆይ እንደሚችል አስቀድመው ጠቁመዋል።
“በእርግጠኝነት ስለ ወራት እያወራን ነው። ለዓመታት ይቆያል ብዬ ግን አላስብም” ብለዋል አንደርሰን።
ሊታሰብበት የሚገባው የአካባቢ ተፅእኖም አለ። የመጓጓዣ አቅጣጫ መቀየር እና ድንገተኛ የጭነት መርከቦች እንቅስቃሴ መጨመር የውሃ ውስጥ ድምጽ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ይህም በአካባቢው በሚገኝ የዓሣ ክምችትን እና የባሕር ውስጥ ሕይወትን ሊጎዳ ይችላል።
መርከቦች ቀደም ሲል ከሚጓዙበት በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን ስለሚጓዙ ብዙ ነዳጅ ይጠቀማሉ። በመሆኑም ተመሳሳይ ጭነት ለማድረስ ብዙ በካይ ካርቦን ወደ ከባቢ አየር ይለቃሉ።
ዓለም አቀፉ የባሕር ድርጅት እአአ በ2023 ባወጣው ዕቅድ በ2050 የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ዜሮ ለመድረስ እና በ2030 ደግሞ ቢያንስ 20 በመቶ ልቀት ለመቀነስ ግቦችን አውጥቷል።
“ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ በተቀመጠው ግብ ላይ መድረስ አይችልም” በማለት የትራንስፖርት ኢኮኖሚስቱ ሪኮ ሉማን ይናገራሉ።
ሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ምክንያት ብዙ የመርከብ መንገዶችን እንዲቀይሩ በማድረጉ መርከቦች ረዥም መንገዶችን እንዲጠቀሙ አድርጓል። ስለዚህ አንዳንድ መርከቦች ቀድሞ ከነበረው በላይ አማቂ ጋዞችን እየለቀቁ ነው።
ግልጽ የሆነው ነገር ግን የሁቲዎች ጥቃት በዓለም አቀፍ የአቀርቦት ሰንሰለትን አለማሰናከሉን ነው። ከሁሉም በላይ ከባድ ስጋት የሚሆነው ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠባቸው የባሕር ተጓዦች ጉዳይ ነው።
